በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት”የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ተቋቋመ” ተብሎ እየተናፈሰ ስላለው አሉባልታ መግለጫ ሰጠ።
ሀገረስብከቱ በቅርቡ የተሳካ ዓመታዊ ስብሰባ፣ የትምህርተ ወንጌልና የዐውደ ጥናት ጉባኤ አካሂዷል።
በጀርመን ንዑስ ማእከል
መስከረም 11 ቀን 2008 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሰሞኑን “በጀርመን የሆክስተር ከተማ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ተቋቋመ” ተብሎ እየተናፈሰ ነው ስላለው አሉባልታ መግለጫ አወጣ:: ሀገረ ስብከቱ መግለጫውን ያወጣው የሐሰት መረጃው ለጥቂት ግለሰዎች በኢሜይል እና ዓለሙ አምላኩ በተባለ የብዕር ስም ጎልጉል በተባለ ድረ ገጽ ላይ እየተሰራጨ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ጠቅሶ በተለይም ሀሰተኛው ወሬ በማጠቃለያው “ሦስተኛ ሲኖዶስ ተቋቋመ፤ ዳግመኛ የግብጽ ተገዢዎች ልንሆን ነው፤ ሊቀ ጳጳሱ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎችን በተለይም 30 ዓመት ያስተዳደሩትን ሊቀ ካህናት ሳያማክሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ውስጥ ከተቷት፤ የመንግሥት እጅ አለበት ወዘተ..” የሚል ከእውነት የራቀ አሉባልታ ዘገባ እንደተደረገ ሀገረ ስብከቱ ደረሶበት እንደሆነ ይገልጻል።
በመግለጫው እንደተመለከተው ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ/ም በሆክስተር የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ተቀማጭነታቸው ጀርመን ውስጥ በሆነው በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃነ ጳጳሳት የተፈረመው ስምምነት ቀደም ሲል በ2013 ዓ/ም (ብፁዕ አቡነ ሙሴ ከመምጣታቸው በፊት) ሙኒክ ከተማ ላይ የተቋቋመው “የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ማኅበር“ መርሐ ግብሮች አንድ አካል ነው። ይህም በጀርመን ብቻ የሚገኙ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በመረዳዳት መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጽሙበት እንጂ የኢትዮጵያን ሲኖዶስ አያጠቃልልም። የጋዜጠኛውን ዘገባ በተመለከተ ሲኖዶስ /Synode/ የሚለው ጀርመንኛ ቃል እንደ እንግሊዝኛው ሁሉ ብዙ ፍቺ ያለውና ማንኛውንም የአብያተክርስቲያናት ስብሰባ በዚህ ስያሜ መጥራት የተለመደ በመሆኑ ቢጠቀምበትም እንዲሁም “ቅዱስ ሲኖዶስ“ ተብሎ ቅዱስ ተጨምሮበት ባለመጻፉ የቤተ ክርስቲያናችንን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስን ባያስመስልም ስያሜው አሻሚ ሊሆን ስለሚችል “ኅብረት“ ወይም “አንድነት“ በሚል ስያሜ እንዲታረም ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለአንባ ዳምያን በጀርመን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በተጻፈ ደብዳቤ ተጠይቋል። ብፁዕነታቸውም ጥያቄውን ተቀብለው ያስተላለፉ ሲሆን የተነሱትን ክሶች መሠረተ ቢስነት በዝርዝር የሚያስረዳውን ሙሉ መግለጫ በሀገረ ስብከቱ ፌስቡክ ገጽ ላይ ይመልከቱ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የደ/ም/ም/ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ከነሐሴ 29 እሰከ ነሐሴ 30 2007 ዓ.ም ድረስ አጠቃላይ ዓመታዊ ስብሰባውን የሀገረ ስብከቱ መቀመጫ በሆነው በጀርመን ሀገር በሩሰልስሃይም ከተማ በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል:: በጉባኤው ላይ በሀገረ ስብከቱ ስር ከሚገኙ ከተለያዩ የአውሮፓ ከተማ የመጡ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች እና የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዕለቱም በአስተዳደሪዎች በኩል ያሳለፍነው ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖረትና በ2008 ዓ.ም በአብያተ ክርስቲያናቱ ሊከናወኑ የታቀዱ አገልግሎቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በስብሰባው ሁለተኛ ቀን የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ሪፖርትና የ2008 ዓ.ም ዕቅድ እንዲሁም በጉባኤው ተለይተው በቀረቡና ሌሎች ተጨማሪ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ባሳላፍነው ዓመት እጅግ አበረታች የሆኑ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በጎ አገልግሎቱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አንዳንድ ግለሰቦች የስም ማጥፋትና ሌሎች መሠረት የሌላቸውን አሉታዊ ተግባራት መፈጸማቸውን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በሪፖርቱ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ በፊት በጉባኤው ስምምነት ለሀገረ ስብከቱ ፈሰስ እንዲደረግ የተወሰነውን ውሳኔም አለመፈጸማቸው ተገልጿል፡፡ በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከፍተኛ የሥራና የአገልግሎት አፈጻጸም ውጤት ያስመዘገቡ በየደረጃቸው የተዘጋጀላቸውን ሽልማትና የምስክር ወረቀት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ እጅ ተቀብለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የበርሊን ደ/ገ/ቅዱስ አማኑኤል አስተዳደሪና የሰ/ጉባኤ በጀርመንና ሌሎች ሀገራት የሚገኙ ምእመናን በማስተባበር በአጭር ጊዜ በጀርመን ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ የተሟላ አገልግሎት ማስፈጸም የሚያስችል ሰፊ ቦታ ያለው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን መግዛት በመቻላቸውና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማፋጠን በሚያደርጉት አስደሳች ተግባር በአንደኝነት ለመሸለም በቅተዋል፡፡ እንዲሁም የሙኒክ ደ/ብ/ቅ/ገብርኤል አስተዳደሪና ሰበካ ጉባኤ አጥቢያው የራሱ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረው ለማስቻል በሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረትና እየተከናወነ ባለው ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት በሁለተኝነት ሲሸለም፣ የስዊዘርላንድ አብያተ ክርስቲያናት በመተባበር በሊቢያ በሰማዕትነት ላለፉት ወገኖቻችን ወላጆች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ አስባሰቦ ሀገር ቤት በመላካቸው ላሳዩት አርአያነት ላለው ተግባር በሦስተኛነት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ከሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ጉባኤ ቀጥሎ የትምህርተ ወንጌልና የዐውደ ጥናት ጉባኤ ተከናውኗል፡፡ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በተካሄደው ጉባኤ በመልአከ ሕይወት አባ ዘድንግል የፓሪስ መካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሪ እና ከኢትዮጵያ በመጡት በዲ.ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ከትምህርተ ወንጌሉ በተጨማሪ በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም ምእመናኑ የሀገረ ስብከት አደረጃጀትና ኃላፊነት፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ወረዳ ቤተክነት የሥራ ግኑኝነት እና ተግባርና ኃላፊነት ግንዛቤ እንዳገኙበት ይታመናል፡፡ በተጨማሪም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ያገጠሙ ችግሮች፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው የተዳሳሱበት እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የቤተ ክርስቷያኗ ትልቁ ሀብት ስለሆነው ግዕዝም ቀድመው ስለተከናወኑ ምርምሮችና አሁን ስላለበት ሁኔታ ምእመናን ጥሩ ገንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያው የሆነውን ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ያጠቃለለ ሲሆን ይህ በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር