«መኑ ውእቱ ብእሲ ዘይፈቅድ ሐይወ ወያፈቅር ይርአይ መዋዕለ ሠናያተ »
በመምህር ፍቃዱ ሣህሌ
ጳጕሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም.
ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው ? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው ?
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት እንደ ሰውነቱ በርካታ ጥያቄዎችን ጠይቋል። እንደ መንፈስ ቅዱስ ማደሪያነቱ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ለጥያቄዎችም መልስ ሰጥቷል። ከላይ የተቀምጠው ጥያቃዊ ኃይለ ቃልም በተመሳሳይ ሁኔታ ያቀረበው ጥያቄ ሲሆን ለሁላችንም ጥቅም ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እርሱ ላይ አድሮ መልሱን ሰጥቶናል።
የሰው ሕይወት ሕይወተ ሥጋና ሕይወተ ነፍስ ተብሎ በሁለት መንገድ ተከፍሎ ይታያል የቅዱስ ዳዊት ጥያቄ ሁለቱንም የሚመለከት ነው። እነርሱም፦
- በጎ በጎ ዘመናትን ለማየት የሚወድድ ማነው ?
- በጎ ስራ የሚሰራባቸው ዘመናትን ለማየት የሚሻ ማነው?
- በጎ በጎ ነገሥታት መሪዎች የተሾመባችው ዘመናትን ሊያይ የሚወድ ማን ነው?
የሁለቱም ጥያቄዎች በአንድነት ተጠቃሎ ሲገለጽ ደግሞ
- ሰማያዊውን ክብር ሊያገኝ የሚወድ ማን ነው? የሚል ይሆናል።
ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የምንገኝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችንም ማኅበረ ካህናት ወምዕመናን የምንደክመውና የምንጋለው ይህንን ሰማያዊ ክብር ለማግኘት ነው። ሁልጊዜም ጥያቄው ጥያቄያችን መልሱም መልሳችን ነው። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ላይ አድሮ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ይላል።
፩. አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ የምላስን አመፅኝነት ገልጾ አንደበትን መግዛት (መቆጣጠር) በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጽፎልናል። እግዚአብሔርን በምናመሰግንበት አንደበታችን በእርሱ አርአያና ምሳሌ የተፈጠረውን ሰው የምንረግም ከሆነ እግዚአብሔርን እንደሚያስቆጣ ነግሮናል። ያዕ ፫:፩-፲፫ ቀደም ባለው ምዕራፍም “አንደበቱን ሳይገታ ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያምልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር ፥ የእርሱ አምልኮቱ ከንቱ ነው።” ያዕ ፩:፳፮ በማለት አንደበትን መግታት ዘዓለማዊ ሕይወትን ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል። ሽንገላ ሰውን በሐሰት ማታለል ከእውነት መስመር ማውጣት ነው። ይህም የሰይጣን ሁነኛ መታውቂያው ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በተመለክተ ሲገልፅ “እንግዲህ በሽንገላችው ያስቱ ዘንድ በሚተናኮሉ ሰዎች ተንኮል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ ወዲያና ወዲህ እየተፍገምገምንና እየተንሳፈፍን ሕፃናት አንሁን። ” ኤፌ ፬:፲፬ በማለት የሽንገላን ክፉነት አጉልቶ አሳይቷል። በዚህ መሠረት በሕይወተ ሥጋ ፣ በሕይወተ ነፍስ አብሮ ለመኖር በጎ የሆነውንም ዘመን ለማየት ዛሬም በዚህ ዓለም በአንደበታችን ክፉ ነገርና ሽንገላ እንዳይገኝ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
፪. ከክፉ ሽሽ
ይህ መንፈስ ቅዱስ የሰጠን ሁለተኛው መልስ ነው። ይህን በተመለከተ ብዙም ማብራርያ አያሻንም ክፋትንና ውጤቷን እናውቃለንና። “ክፋትን አትሥራት ክፉም አያገኝህም ከበደል ራቅ እርስዋም ራስዋ ካንተ ትርቃለች። ሰባት እጥፍ አድርገህ እንዳትሰበስባት በኃጢአት ትልም አትዝራ።” ሲራክ ፯፥፩-፬ የሚለው ጥቅስ ርእሰ ጉዳያችንን በሚገባ ያብራርልናል።
፫.መልካምን አድርግ
ይህ ከክፋት መራቅ ነውና አንደበትን መቆጣጠር ብቻውን ዘላለማዊ ሕይወትን (በጎ ዘመንን) ስለማያስገኝ ከክፋት በተለየ ሕዋሳችን በክፉ ፈንታ ጽድቅ የሆነው መልካም ሥራ እንዲተካበት የሚያስብ መልስ ነው። ኃጢአትን የተወ ሰው ጽድቅ መስራት መጀመር አለበት። ይዘፍን የነበረ አንደበት መዘመር ፤ ይቀማ የነበረ እጅ መመጽወት ፤ወደ ክፉ ቦታዎች ይገሰግሱ የነበሩ እግሮች ወደ ቅድስናው ሥፍራ (ቤተ ክርስቲያን) መገስገስ ወዘተ… ይኖርባቸዋል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዛፉን መልካም ፥ፍሬውንም መልካም አድርጉ ፤ ወይም ዛፉን ክፉ፥ ፍሬውንም ክፉ አድርጉ ፤ዛፍ በፍሬው ይታወቃልና።” ማቴ ፲፪፥፴፫። በማለት መልካሞች (ክርስቲያኖች) ነን እያልን ግብራችን ( ሥራችን) ደግሞ ክፉ መሆን እንደማይገባው አስተምሮናል። እውነተኛ ክርስቲያን (ምእመን) አነደበቱ ሥራውና ሕይወቱ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የተወደደና መልካም ዛፍነቱን (ክርስቲያንነቱን ) የሚያሳይ መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ነው፡፡
፬. ሰላምን ፈልጋት ተከተላትም
አስቀድሞ ሕዝብና አህዛብ ፣ ነፍስና ሥጋ ፣ ሰውና መላእክት ፣ ሰውና እግዚአብሔር ተጣልተው ተለያይተው ይኖሩ ነበር። እውነተኛ ሰላም በክርስቶስ ሞት ያገኘነውና ተለያይተው የነበሩት ሁሉ አንድ የሆኑበት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በመካከል ያለው የጥሉ ግድግዳ ፈርሶ አንድነት የተገኘውና ፍቅር የተመሠረተው ፤ ሰላምም የተረጋገጠው በክርስቶስ መስቀል (ሞት) ነው። ኤፌ ፪፥፲፩— ፍጻሜው ዛሬ ይህን ወደጎን ትቶ ምድራዊውን፣ሥጋዊውንና ጊዜያዊውን ጥቃቅን ልዩነት ተጠቅሞ ሰማያዊውን ፣መንፈሳዊውንና ዘለዓለማዊውን አንድነትና ሰላም ማናጋት የዳንበትን የክርስቶስ ሞት ማቃለል ስለሚሆን በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም የሚያሰቀጣ ይሆናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርሰቲያኖች ሁላችንም በዚህ ረገድ ሲመክረን እነዲህ ብሏል።”ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ሮሜ ፲፪፥፲፰ “ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ ” ዕብ ፲፪፥፲፬። በቅዱስ ዳዊት ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ የነገረንም ይህንኑ ነው። የመከረን መጀመሪያ ሰላምን እንድንፈልጋት ከዚያም እንድንከተላት ከእርሷ እንዳንለ ነው። በሕይወተ ሥጋ በሕይወተ ነፍስ ከብሮ ለመኖር ሰላም ያስፈልገናል ይህንንም የምናገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ክርስቲያኖች ከክርስትናቸው ጽኑ ማሰሪያና ከመንፈሳዊው አንድነታቸው በልጦ ሊለያያቸው የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ነገር ሊኖርባቸው አይገባም። በአንዲት ሃይማኖት፣ በአንዲት ጥምቀት፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ያጣመራቸውን እግዚአብሔርን በልጦ የሚከፋፍላቸው ጉዳይ ከተገኘባቸው አደጋ ውስጥ ይሆናሉ። እንዲህ ሆነው ክርስቲያን ነን እያሉ ቢመላለሱ እንኳንስ ሰማያዊውን የእግዚአብሔር መንግስት ሊወርሱ ይቅርና ምድራዊውን በረከት መብላት አይችሉም።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረን “ዕለቱን (ዘመኑን) ክፉ ወይም ደግ እነዲሆን የምናደርገው እኛው ነን ።” ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊትም ሕይወትን እፈቅዳለሁ፤ በጎ ዘመንንም ለማየት እፈልጋለሁ ለምንል ሰዎች ማድረግ የሚገባንን የዘረዘረልን። ዘመናቱ በተፈጥሮዋቸው ክፉና ደግ ተብለው የተዘጋጁ አለመሆናቸውንና የነሱ ማንነት በእኛ ክፋትና ደግነት ላይ የተወሰነ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ያስተምራል። ክፉዎች በበዙበት ዓለም የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እያንዳንዱን ቀናቸውንና ዘመናቸውን መልካምና በጎ ማድረግ ይችላሉ። ይህ በእያንዳንዳችን እጅ ውሰጥ ያለ መልካም ዕድል ነው። እነሆ እሳትና ውሃ በፊታችን ነው እንዳለ ሁሉ ሰው ቤቱን ፣ ትዳሩንና ሕይወቱን ሲዖልም ገነትም ማድረግ ይችላል። መጪውን ዘመንም እንደዚሁ በፈለገው አቅጣጫ መጋለብ ይችላል፤ ዘመን ፈረስ ነውና። ዘመን እንደ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም። ስለ ክርስትና ሃይማኖታችን የምንዋጋ እኛ ነን።
በጎ የሆነውን ዘመንና ዘላለማዊ ሕይወትን ከማየት አኳያ አንደበታችንን እንግታ (እንቆጣጠር)። አንደበታችንን ብቻ ሳይሆኑ ብዕሮቻችንና የማኅበራዊ ድረ ገጾቻችን ሁሉ ክፉ ከሆነው ሁሉና ከሽንገላ የራቁ እንዲሆኑ መታገል አለብን። አንድነትን ፣ ፍቅርንና ፣ ሰላምን የሚሰብኩ እንጂ ራስንም ሆነ ሌላውን በተቃራኒው አቅጣጫ የሚያሰልፉ እንዳይሆኑ መሥራት አለብን። ከላይ እንዳየነው ክፉ የሆነውን ሁሉ መጸየፍ ፤ ላለፈው ሥርየትና ለመጪውም ዕቅበት ራስን ማዘጋጀት። “ አሁንም ቁጣንንና ብስጭትን ክፋትንና ስድብን የሚያሳፍረውንም ነገር ተዉ ከንቱ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ሰው ከስራው ጋራ ተውት እነጂ ወንድሞቻቹን አትዋሹ። ፈጣሪውን ለመምሰል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱት። በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ ግሪካዊ የተገረዘ ያልተገረዘ አረመኔም ባላገርም ቤተሰብና አሳዳሪ ማለት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው።” ቈላስ፫፥፰-፲፪ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረን ከልብ ማስተዋል ይገባል። ፳፻፰ ዓመተ ምህረትን ከነችግሮቹ የኃሊት ትቶ በአዲሱ ዓመት አዲስ በሆነ የንስሐ፣ የይቅርታ ፣ የፍቅር ፣ የሰላምና የአንድነት ልብ መነሣሣት ይኖርብናል። መልካም ምግባራትን በክፉው ቦታ እየተካን የዚህ ዓለሙን ሳይሆን የላይኛውን እያሰብን ለመኖር ማቀድ አለበን። ለዓይን በሚያታክቱት መባዕልትና አልባሳት ሳይሆን ሰውነታችን በጾም ፣ በጸሎት ፣ በምጽዋት ፣ በንስሐ፣ በሥጋ ወደሙ በመልካም ሥራዎች ሁሉ በማስጌጥ አዲሱን ዘመን አዲስ በሆነው ክርስቲያናዊ ሰብእናን ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርብናል። ለዚህም የቅዱሳን ጸሎት የድንግል ማርያም አማላጅነት የእግዚአብሔር ቸርነት ይርዳን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!