“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ በሰማያት ምስጋና ተደረገ በምድርም እርቅ ተወጠነ ‹‹ሰላም ሆነ፡፡›› (ሉቃ. ፪፥፲፬)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!
ለአዳም የሰጠውን ተስፋ ሊፈጽም በነቢያት አድሮ ያናገረው ትንቢት ሲደርስ ሰው የሆነ አምላክ የተወለደበት ዕለት (የልደት በዓል) እነሆ ደረሰና እኛም በዓሉን አክብረን ከበረከተ ልደቱ እንድንሳተፍ አበቃን፡፡
አምላካችን ለእኛ ላደረገልንና ለሚያደርግልን የቸርነት ሥራው ሁሉ ከምስጋና በቀር ሌላ አቅም ኖሮን መክፈል የምንችለው ነገር የለንም፡፡ ምክንያቱም እንክፈል ብንልም እንኳን ከእርሱ ያላገኘነው ምንም ነገር የለንምና፡፡ ከሕይወታችን ጀምሮ ሁሉንም ነገር ያገኘነው ከእርሱ ነውና፡፡ የሰዎች ልደት የሚከበረው በሕይወት ዘመናቸው ሲሆን ከሞቱ በኋላ የሚከበረው ግን ሙት ዓመታቸው ነው፡፡ አምላካችን ግን ልደቱም፣ ሞቱም ከተወለደበት እስከ ዐረገበት ጊዜ ድረስ ተአምራት ያደረገባቸው ቀናት ሁሉ ሁሌም እንደ አዲስ ይከበራሉ እኛ የምንኖረው ለራሳችን ሲሆን እርሱ ግን ሁሉንም ያደረገው ለሰው ልጆች ደኅንነት በመሆኑ ልደቱን በምናከብርበት ጊዜ ደኅንነታችንን እያሰብን ሲሆን በረከትን እናገኛለን፡፡
ጌታችን ሲወለድ እውነተኛው ሰላም እንደሚገኝና ፍጹም ደኅንነት እንደሚደረግ ነቢያት አስቀድመው በተናገሩት መሠረት በተወለደበት ዕለት መላእክትና እረኞች በአንድነት ሆነው “በሰማያት ምስጋና ይሁን በምድርም እርቅ ተወጠነ ‹‹ሰላም ሆነ›› ብለው አመሰገኑ፡፡ ይህ ብሥራት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ እንደተወጠነ ‹‹ሰላም እንደሰፈነ›› ያስረዳል፡፡ የመላእክትና የእረኞች ምስጋና አምላክ ሲወለድ የተገኘውን ሰላም ታላቅነት ያስረዳናል ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ምንም አይኖርምና፡፡
አንድ አዳም በፈጸመው ስሕተት ምክንያት ፶፻ወ፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት) ዘመናት ያህል የሰው ልጆች ሁሉ ሰላማችን ጠፍቶ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር እንድንኖር ተገደን ነበር፡፡ አምላካችን የተወሰደብንን ሰላማችንን ሊመልስልን ፈቃዱ ሆኖ የእኛን ሥጋ በመዋሐድ ሰው ሆኖ በተወለደባት ዕለት ይህን የምሥራች የሚያበሥር የምስጋና ዝማሬ መላእክትና እረኞች በአንድነት ዘመሩ፡፡
ጌታችን በወንጌል “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም፡፡” (ዮሐ. ፲፬፥፳፯) በማለት እውነተኛው ሰላም የሚገኘው ከእርሱ ብቻ መሆኑን ነግሮናል፡፡ አምላካችን ሰላምን የተወልን ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ነው፡፡ ዛሬ ዓለም ሰላምን ለማምጣት የሚከተለው መንገድ ከዚህ በተለየና በተቃራኒው ነው፡፡ ሌላውን አጥፍቶ እየኖረ ሰላም አገኘሁ ይላል፡፡
ሰላም በሥጋዊ ኃይል የሚመጣ በወረቀት ላይ ብቻ የሚሰፍር በአንደበት የሚለፈፍ አይደለም፡፡ ሰላም ከሰዎች የሚሰጥ ገጸ በረከት ሳይሆን ከውስጣችን የሚገኝ ሕይወት ነው፡፡ ሰላም በመተሳሰብ፣ በመግባባትና በፍቅር የሚመጣ የጤናማ ውይይት ውጤት ነው፡፡ ሰላም የውስጥ እፎይታ የመንፈስ እርካታ የኅሊና እረፍት ነው፡፡ ሰላም በዋጋ የማይተመን ከነገሮች ሁሉ የበለጠ ታላቅ ቁም ነገር ነው፡፡
አምላካችን የሰጠን ሰላም በሰዎች ሥጋዊ አስተሳሰብ ያልሆነና የእግዚአብሔር የሆኑት ብቻ የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ ሰዎች የጠፋ ሰላማቸውን ለማግኘት በራሳቸው መንገድ ብዙ ሲደክሙና መውጣት ለማይችሉባቸው ብዙ አጓጉል ሱሶችም ራሳቸውን አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ ሰላም በራስ ኅሊና ውስጥ በትዳር መካከል በቤተሰብ መካከል በሥራ ቦታ በሀገር ውስጥ ሊታጣ ይችላል፡፡ እግዚአብሔርን የያዘ ግን የትም ቢሔድ ሰላም አለው፡፡ ሰላም የራስ የሆነ ማንም የማይቀማው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሀብት ነውና፡፡
ዛሬ ዓለም ያልተረዳውና ሊኖርበት ያልቻለው ይህን ዕውቀት ነው፡፡ በዚህ ሰላማዊ ሕይወት ኖረው ያለፉ የቀደሙ ሰዎችን የሃይማኖት ጉዞ እንደ ሞኝነት ዘመን እየቆጠረ ራሱን ሲያሞኝ ይታያል፡፡ዓለማችን ለሰላም የቆመ ይመስል ቆሜያለሁ እርስ በእርሱ የሚጠፋፋበትን ከባድ መሳሪያ በማምረት ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ሰላሙን ማረጋገጥ የሚፈልገውም ባለው የኃይል ሚዛን ሆኗል፡፡ ሰላም በንግግርና በምኞት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ እውነት መሆኑን ረስቶ ተቃራኒውንና የመጠፋፊያውን አቋራጭ መንገድ ተያይዞታል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰው በራሱ ዕውቀት ብቻ በመመራቱ እና የእግዚአብሔርን ቦታ ለመተካት በመፈለጉ ነው፡፡
የሰው ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ሙሉ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር የሌለው ሰው በውስጡ ባዶነት ይሰማዋል፡፡ ስለሆነም ይበላል ይጠጣል ግን አይረካም፣ ይለብሳል ግን አይደምቅም፣ ይናገራል ግን እርስ በእርሱ አይግባባም፣ ይሮጣል ግን ማንንም አይቀድምም፡፡ (ሐጌ. ፩፥፭) የተመኘውን ሁሉ ለማድረግ ይጣደፋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሰላም የለውም፡፡ ይህ የሚሆነው በውስጡ እውነተኛው ሰላም ክርስቶስ ስለሌለው ነው፡፡የጌታችንን ልደት ስናከብር ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠትን፣ ይቅር መባባልን በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ ዓለማችን ያለችበት ሁኔታ አደገኛና እጅግ ፈታኝ የሆነ ወቅት ነው፡፡ ሁሉም የራሱን ጩኸት እንጂ የሌላውን ሐሳብ የሚያዳምጥበት ጆሮ የለውም፡፡ ጌታችን በተወለደበት ዕለት ሰብአ ሰገል (የምሥራቅ ነገሥታት) ከርቀት ቦታ በኮከብ እየተመሩ መጥተው ለጌታችን ከሰገዱለት በኋላ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ (እጅ መንሻ) አቅርበውለታል፡፡ (መዝ. ፸፩፥፱-፲፩)
በሌላ በኩል ደግሞ ሄሮድስ የተባለው ንጉሥ ጌታን ሊገድለው ይፈልገው ነበር፡፡ ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› ሆነና ዛሬ ዓለማችን አንዱ ለመልካም ሌላው ደግሞ ለጥፋት ተልዕኮ የሚጣደፉባት መድረክ ሆናለች፡፡በዓሉን በምናከብርበት ወቅት በዓለም ላሉ መሪዎች ሁሉ እግዚአብሔር እንደ ሄሮድስ ያለውን የድንጋይ ልብ አውጥቶ እርሱን መፍራትና ማስተዋልን እንዲሰጣቸው ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡
የዛሬዋ ዓለማችን ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው በጡንቻቸው የሚመኩ ከወገንና ከሀገር ይልቅ ለራሳቸው ሥልጣንና ዝና ቅድሚያ የሚሰጡ መሪዎች ስለበዙባት የግፍና የሰቆቃ ዓለም ሆናለች፡፡ የሰው ልጅ ኑሮም የተረበሸና መረጋጋት የጠፋበት ሆኗል፡፡ሰላም በድሃውም በሀብታሙም ቤት ባደጉትም በድሆችም ሀገሮች በትንሹም በትልቁም ሕዝብ መካከል ጠፍቷል፡፡ በዓለም ዙሪያ ያለውና በየቀኑ የሚሰማው ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዓለም ለመጠፋፋት የሚያውለውን ጊዜ መልካም ወደማድረግ መለወጥ አለበት፡፡
ሰላም ከሌለ ሕፃናት ወጥተው መግባት፣ ሠራተኛው ሠርቶ መኖር፣ ነጋዴው ነግዶ ማትረፍ፣ ገበሬው አምርቶ መኖር አይችልም፡፡ ሰዎች ሁሉ አምላካችን ወደዚህ ዓለም የመጣው ሰላምን ለሰው ልጆች ለመስጠት መሆኑን ተረድተው ለሰላም በጎ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ለሁሉም መሠረቱ ሰላም ነውና፡፡ሄሮድስም ጌታን ያገኘው መስሎት እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ዐሥራ አራት ሺህ ሕፃናት ልብስና ቀለብ እሰጣለሁ ብሎ ሰብስቦ በጭካኔ በሰይፍ አስገደላቸው፡፡ የእርሱ ሐሳብ ጌታን ገድሎ እንደ ልቡ በሥልጣን ላይ ለመኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታንም አላገኘውም፣ በሥልጣኑ ላይም አልቆየበትም፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ካልፈራ ለጭካኔው ገደብ የለውም፡፡ ሥጋዊ ጥቅም እስካገኘለት ድረስ በእርሱ አስተሳሰብ ሰውን መግደልም ትክክል ነው፡፡
መሪዎች ቆም ብለው ማሰብ ቢችሉ እኮ ሁሉም እንደሚያልፍ መረዳት ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀና መንፈስ እና የተሰበረ ልብ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ስለሆነ እነርሱም ያወቁ መስሏቸው አምላክን ትተው በራሳቸው ዕውቀትና ኃይል በመተማመናቸው ማጣፊያው አጠረባቸው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉንም አውቃለሁ ብሎ ካሰበ መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ ብቻ እንደሆነና ነግሮች ሁሉ የሚከናወኑት በአምላክ ጥበብና ፈቃድ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ባይረዳም ግን ነገሮች እንዲህ ከመሆን አይቀሩም፡፡ ሰው ቢችል ኖሮ በሽታንም፣ ድህነትንም፣ ጦርነትንም፣ የማያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ ማጥፋት ይችል ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ከሰው ልጅ አቅም በላይ በመሆኑ (መድኃኒት የሌለው በሽታ ማቆሚያ የሌለው ጦርነት፣ የሥራ አጥ ብዛትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት) የመሳሰሉ አደጋዎች ውስጥ ገብቷል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሁሉም ነገር በአምላክ ፈቃድ እንደሚደረግ ያለ እርሱ ፈቃድ አንዳችም እንዳልሆነና እንደማይሆን ይናገራል፡፡ ዓለም ደግሞ ለችግሮች ሁሉ መልስ ይሰጣል በሚለው ጥበቡ ስለተማመነ ይህን ቃል ለማዳመጥ ጆሮ የለውም፡፡ ዕውቀቱ ግን ችግሮችን ሲያባብስ እንጂ መፍትሔ ሲሰጥ አይታይም፡፡እግዚአብሔር የሌለበት ዕውቀት… መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ በጌታችን ልደት ዕለት መላእክትና እረኞቹ ሲያመሰግኑ በሄሮድስ ቤተ መንግሥት ግን የጥፋት ሸንጎ ተይዞ ጌታን ስለመግደል ይዶለት ነበር፡፡
እንደዚያ ጊዜው ሁሉ ዛሬም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የልደትን በዓል በዝማሬና በምስጋና ሲያከብሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በመንፈሳዊው በዓለ ልደት ስም ፓርቲ አዘጋጅተው በመጨፈርና በመዳራት ያሳልፋሉ፡፡ ለክብር የተፈጠረውን ሰውነታቸውንና አክብረው ሊከብሩበት የተዘጋጀላቸውን ቅዱስ በዓል ጨፍረውም ሆነ አብደው ለማይረኩበትና የውስጣቸውን ጉድለት እንዲያስረሳቸው እንደማደንዘዣነት ለሚጠቀሙበት ጊዜያዊ ፍላጎታቸው ያውሉታል፡፡ ያም ቢሆን ስላመኑበት ብቻ ያደርጉታል እንጂ ሲረኩበት አይታዩም፡፡
ጌታችን በተወለደበት በረት ውስጥ የነበሩት እንስሳት በትንፋሻቸው አሟሙቀውታል ወቅቱ (ታኅሣሥ ወር) በፍልስጥኤም ምድር የብርድ ወቅት ነበርና፡፡ ጌታችን በዚህ አስቸጋሪ ወቅትና በማይመች ሁኔታ መወለዱ እኛን ለማዳን ባደረገው ጉዞው ሁሉ ፍጹም ፍቅሩን ሊገልጽልንና በእኛ ተገብቶ ባደረገው ሥራውም በአዳም በደል ምክንያት ተጥለን ለነበርን ለእኛ የሰው ልጆች ሁሉ በመካስና ከውድቀታችን በማንሳት ፍቅሩን ሊገልጽልን ስለወደደ ነው፡፡
መላእክትንና እረኞችን ለምስጋና የመረጠ ሰብአ ሰገልን ስጦታ ለማቅረብ ያበቃ አምላክ የእኛንም የምስጋና መዝሙርና አገልግሎት የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ይቀበልልን፡፡ አሜን!! !ወስብሐት ለእግዚአብሔር!