መንፈሳዊ ሕይወትና ስደት
በይበልጣል ጋሹ
የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ በተለያየ ምክንያት በስደት ለምንኖር የቦታ መቀየር ተፅዕኖ ሳያሳድርብን በሃይማኖታችን ጸንተን እስከመጨረሻው በመንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖርና እግዚአብሔር አምላክ ሁልጊዜ ከስደተኞች ጋር መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ተገንዘበን “እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል” መዝ 145፡9 የሚለውን ህያው ቃል በውስጣችን አስቀምጠን የሚመጣብንን ፈተና ሁሉ በእግዚአብሔር እንደምንወጣው ለማስረዳት ነው።
ነብዬ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለው? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፣ እስከ ባሕህር መጨረሻም ብበር በዚያ እጅህ ትመራኛለች ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል ሌሊት በዙርያ ብርሃን ትሆናለች” መዝ 138፡7-11 ብሎ እንዳስተማረን የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ፣ ስዓትና ሁኔታ በምህረቱ፣ በቸርነቱ፣ በይቅርታውና በርኅራኄው እየጎበኘ በመንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር በምንሄድበት ሁሉ ጠብቆቱ አይለየንም።
በተለያየ ምክንያት ከምንወዳት ከአደግንባት አገራችን ወጥተን በባዕድ አገር በስደት በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በአመለካከት ከማይመስሉን ጋር በተለያየ ፈተናና ውጣ ውረድ ኑሮን ለመግፋት በመታገል ላይ ለምንገኝ ሰዎች ሰላማችን፣ እረፍታችን፣ መፅናኛችን፣ መከታችን፣ ሞገሳችንና ኃይላችን እግዚአብሔር ነው። ያለእርሱ ምንም ነገር መስራትና ማድረግ የማንችል ባዶዎች መሆናችንን ተረድተን ወገን ዘመድ በሌለበት እርሱን ተስፋ አድርጎ የስደትን አስከፊነት ታግሶና ተቋቁሞ ሥርዓትና ሕጉን ጠብቆ እግዚአብሔርን ማምለክ መንፈሳዊነት ነው። የስደት አስከፊነት እጅግ ከባድ ቢሆንም የተወለዱበትን፣ ያደጉበትን አገርና ህብረተሰብ ጥሎ መሰደድ እንዲሁም ከማያውቁት ህብረተሰብና አካባቢ ጋር መላመድ በስጋዊ አስተሳሰብ ከአየነው ይህ በራሱ ከባድ ነው። ስደት እስኪለመድና መረጋጋት እስኪገኝ ድረስ በብዙ መከራ፣ፈተናና ውጣ ውረድ ሕይወት ባዶ መስላ እስክትታየን ድረስ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ውስጥ የገባን ይመስለናል ከባድም ነው። ይህንን የስደት አስቸጋሪ ሁኔታ ልንቋቋመው የምንችለው በእምነት ውስጥ ስንኖርና እግዚአብሔር አምላክን በመንገዳችን ሁሉ ስናስቀድም ብቻ ነው። ”በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስለአንተ ያዝዛቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሱኋል” መዝ 90፡11 እንዳለ ቅዱስ መጽሐፍ የቅዱሳን መላእክትን ተራዳይነትና አማላጅነት አምነን ሕይወታችንን በሙሉ ለእግዚአብሔር አስረክበን የምንሄድ ከሆነ ሥራችን የተሳካ ይሆናል። የወጣንበት ዓላማም ከግብ ማድረስ እንችላለን።
ስደትን ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር አያይዞ መሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለው” ዮሔ 16፡33 ብሎ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው በስደቱ ዓለም የሚያጋጥመንን የተለያየ መከራና ችግር ልናሸንፋና ድል ልናደርገው የምንችለው እርሱ ስለኛ የሚጨነቅ አምላክ መሆኑን ተረድተን በሕጉና በስርዓቱ ስንመራ ብቻ ነው። “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ” ማቴ 11፡28 ያለ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ ገና በህፃንነቱ ከእናቱ ከቅድስት ድንግልማርያም ጋር ወደ ግብጽ በርሃ በመሰደድ ስደትም እንዳለ አስተማረን ማቴ 2፡13-23። አዎ ለእኛ ሲል መሰደድ የማይገባው አምላክ ተሰደደ፤ መራብ፣ መጠማት፣ መሰቃየት የማይገባው አምላክ ተራበ፣ ተጠማ ተሰቃየ በቀራኒዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ስለዚህ በክርስቶስ ክርስትያን፤ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን እንደተባልን ክርስቲያናዊ ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ያስፈልጋል። ለመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ መከራ፣ ችግር፣ ፈተና፣ እንግልት፣ ውጣ ውረድ በአጠቃላይ በስደት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች ሁሉ መሰናክል ሊሆኑብን አይገባም። “በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” 2ጢሞ 4፡2 ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ በችግርም በመከራም፤ ሲመቸም ሳይመችም፤ በደስታም በሃዘንም ጊዜ፤ በቦታም ያለቦታም፤ በስደትም በእምነት መጽናትና እግዚአብሔርን ማገልገል እንዳለብን ለመንፈስ ልጁ በጢሞቴዎስ አማካኝነት አስተምሮናል። በተጨማሪም ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ 8፡35 በማለት ምንም ነገር ቢመጣ ከምናመልከው አምላክ መለየት እንደሌለብን በሚገባ ገልጾልናል። ለመሆኑ እኛ የተደረገልንን ነገር ረስተን በዘገየብን ነገር እግዚአብሔርን እያማረርን ነው ወይስ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ከአንተ አንለይም ሁሉም ለበጎ ነው እያልን ምስጋና የባህሪው የሆነውን አምላክ ከልብ እያመሰገነው ነው? መልሱን ለእራሳችን።
ሁላችንም ለዚች ምድር መጻተኞች መሆናችንን ተረድተው ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በስደት በነበሩበት ጊዜ ችግሩን ሁሉ ታግሰው በመንፈሳዊ ሕይወት ይኖሩ እንደነበር ዛሬም እንዳሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል። ይልቁንም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እጅግ ጠንክረውና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው ከመኖርም አልፎ በሃይማኖታቸው ላይ የሚመጣባቸውን ፈተና በጸጋ ተቀብለው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ብዙዎች ናቸው። እስኪ የዮሴፍን ታሪክና የሰለስቱ ደቂቅን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከትና ከሕይወታቸው እንማር።