ማኅበሩ ስብከተ ወንጌል በአውሮፓ ሊያካሂድ ነው
ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል በየዓመቱ በምዕራባውያኑ የበጋ ወቅት የሚያካሂደውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀምር አስታወቀ።
የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሩ የፊታችን ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከፍራንክፈርት ከተማ በመነሳት በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የሚቀጥል ይሆናል።
ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ ለዚሁ አገልግሎት ከኢትዮጵያ እንደሚመጡ የታወቀ ሲሆን የዚህ ሰፊ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዋነኛ አላማ ምእመናንን በሃይማኖት እና በምግባር እንዲጸኑ ትምህርት መስጠት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በየሀገሩ ባሉ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ለሚኖሩ ወገኖችም ትምህርተ ወንጌልን የማድረስና የማጽናናት አገልግሎት እንደሚሰጥም ከማዕከሉ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ማዕከሉ ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ጉባኤያትን ከአጥቢያዎች ጋር በመተባበር ማካሄዱ የሚታወስ ነው።