የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን

መግቢያ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተለያየ ጊዜ ካህናት እና ምእመናን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት በተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባ ድርሻቸውም ምን እንደሆነ ያስተምራቸው ነበር:: ለምሳሌ የመንፈስ ልጁ የሆነ ቅዱስ ጢሞቴዎስን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት ሲኖር ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲህ በማለት መክሮታል:-“በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዐምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው::” (1ጢሞ 3፥15)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ጢሞቴዎስን ብቻ ሳይሆን ሁላችንን እንዴት መኖር እንደሚገባን መክሮናል:: ለአብነት ያህል የሚከተሉትን እንመልከት:- “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ። (1ጢሞ 3 : 2-3) በማለት ኤጲስ ቆጶሳትን የመከረ ሲሆን፤ ዲያቆናትን ደግሞ “እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል:: (1ጢሞ 3 : 8-9) በማለት መክሯል:: ስለ ምዕመናንንም እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፣ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው:: (1ጢሞ 6 : 18-19) ሲል ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል ::

የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የተባለች መጠለያችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጌታችንና መድጛኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተመስርታ ፣ በቅዱሳን ተጋድሎና ሰማዕትነት ከብራ፣ በካህናትና ምእመናን አንድነት ጸንታ ላለንበት ዘመን ደርሳለች:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሥጋ ልደታችን 40ኛ እና 80ኛ ቀን ጀምሮ የምንኖርባትና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልገሎት የምናገኝባት ቤታችን ናት:: በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘንባት ፣ በወንጌል የምንታነጽባት፣ ዝማሬ የምናቀርብባት፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ሕይወት የምናገኝባት፣ በአብርሃምና ሳራ ሕይወት ለመኖር ብንወስን በቅዱስ ጋብቻ የምንከብርባት፣ በእንጦንስና በጳውሊ ሕይወት ለመኖር ብንወስን በምንኩስና እና በብህትውና የምንከብርባት ቤታቸን ናት:: ስለእኛ ከእመቤታቸን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ የተወለደበትን ልደቱን፣ እንዲሁም የከበረ ጥምቀቱን፣ መከራ መስቀሉን፣ ሞቱን እና ትንሣኤውን ፣ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እያዘከርን በረከት የምናገኝባት ቤታችን ናት:: ስለ ስሙ የተጋደሉና ሰማያዊ አክሊል የተቀዳጁ በዘለዓለም ሕይወት የከበሩ ቅዱሳንን ስማቸውን ጠርተን ፣ በታቦታቱ ተማጽነን፣ በሥዕላቸው ተማጽነን ፣ በጸበላቸው ተፈውሰን በማይመረመር መንፈሳዊ በረከት የምንኖርባት የእውነት ቤት ናት:: ከልደት እስከ እርግና ቆይተንባት በሞታችንም ጊዜ ሥጋችን የሚያርፍባት ነፍሳችንም በጸሎተ ፍትሐት ወደዚያኛው ዓለም የምንሸኝባት የመጨረሻ ማረፊያችን ናት:: ከሞት በኋላ ስመ ክርስትናችን እየተወሳ በጸሎት የምንታሰብባት ጽድቅን የምናገኝባት አማላጃችን ሕያዊት የእግዚአብሔር ቤት ናት:: ለዚህ ነው ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት ቤተ ክርስቲያንን “ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት ፤ ወደ እርስዋም ጻድቃን ይገባሉ::” (መዝ 117:20) ብሎ በሚገባ የገለጻት:: ይህ የብዙ ዘመናት የተቀደሰ መንፈሳዊ በረከትን የመቀበል ሕይወት ቀጣይነቱ ዘላቂ እንዲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬ የሆንን ካህናትና ምእመናን ተገቢ ድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል:: እንኳን በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት ይቅርና በየግላችን ጎጆ ስንኖር እንዴት መኖር እንዳለብን ካልተረዳን አወዳደቃችን የከፋ ይሆናል:: ጎጆአችንም በላያችን ላይ ይፈርሳል:: ስለዚህም በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት እንዴት እንኑር እያልን? የመጻሕፍትን ምስጢር መመርመር፣ በቤቱ ጸንተው ለዘለዓለም ሕይወት የበቁትን ቅዱሳን ገድል በማንበብ፣ በመስማትና ከሕይወት ልምዳቸው ትምህርት በመውሰድ፤ እነርሱንም በመምሰል የሚጠበቅብንን ድርሻ በመወጣት ልንኖር ይገባናል::

የዚህ መልእክት ዓላማ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ የተሰኘን ምእመናንን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት ያለንን ድርሻ ማሳየት በመሆኑ በዚሁ ላይ ያተኩራል::

የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዓበይት የሆኑትን በዚህ ጽሑፍ እንቃኛለን:-

1. የክርስትና ሕይወት የሚጠይቀውን ምግባር በማከናወን አርኣያ ሆኖ መኖር:-

ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ስር የተሰባሰብን ምዕመናን በውጭ ካሉት የሚለየን ክርስቲያን የሚለው የከበረ መጠሪያ ስማችን ብቻ ሳይሆን ስሙ የሚጠይቀውን ቤተ ክርስቲያን ያቆየችልንን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ወይም ሕይወት መተግበርና መኖር መቻላችን ነው:: ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅነትን ክብር በጥምቀት ወይም ከውኃና ከመንፈስ በመወለድ ያገኘን ምእመናን ልጅነታችንን የሚያረጋግጥ መንፈሳዊ ሕይወትን መኖር ይጠበቅብናል:: አይሁድ የአብርሃም ልጆች ነን በማለት ዋጋ እንዳላገኙ ሁሉ ክርስቲያን ነን ማለታችን ብቻውን ዋጋ አያስገኝልንም:: ለመዳን ከአይሁድ ተሽሎ ከፈሪሳወወያን በልጦ ከአጋንንት ማታለል ወጥመድ ተጠብቆ መገኘት ያስፈልጋል:: የእውነተኛ ክርስትና መገለጫው ሥነ ምግባር ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ምግባር የሌለው ሃይማኖት በራሱ የሞተ ነው:: (ያዕ2 17) እንዳለ:: ስለዚህ ዕለት ዕለት በጸሎት የምንተጋበት፣ ለንስሐ የምንፈጥንበት፣ በአገልግሎት የምንበረታበት፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ታንጸን የምንኖርበት ሕይወት ሊኖረን ያስፈልጋል:: በሥነ ምግባር ያጌጠ የክርስትና ሕይወት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉትን ኢአማንያን በምግባር በመስበክ ወደ ውስጥ ለማስገባት በውስጥ ሆነው የደከሙትን ደግሞ ለማበርታት አርአያነቱ ታላቅ ነውና ቀዳሚ ድርሻችን ይህንኑ ማጠናከር ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን:: (1ጢሞ 4 11-12) እንዳለ ትህትናን እና የዋህነትን ከጥበብ ጋር በመልበስ የፍቅርን ብርሃን በቤታችን፣ በጎረቤታችን፣ በሥራ ገበታችን እንዲሁም ለመንፈሳዊ በረከት በምንሰበሰብባት ቤተ ክርስቲያናችን በማብራት ሌሎች በሕይወታችን ተማርከው በቤተ ክርስቲያን ጥላ ስር እንዲሰባሰቡና ለዘለዓለም ሕይወት እንዲበቁ ምሳሌ መሆን ከእኛ ይጠበቃል::

2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል:-

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች የሆንን ምእመናን እግዚአብሔር በሰጠን ልዩ ልዩ ጸጋ ቤተ ክርስቲያንን በትጋት ማገልገል ይጠበቅብናል:: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን… አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ:: (ሮሜ 12: 7) በማለት በግልጥ አስተምሮናል::በሰንበት ትምህርት ቤት ፣ በአውደ ምሕረት ጉባኤያትና፣ በሰበካ ጉባኤ ከሚጠበቅብን ሰፊ የአገልግሎት ድርሻ በተጨማሪ ፤ በየተሰለፍንበት የትምህርትና የሞያ ዘርፍ ከዓለም የቀሰምነውን ጠቃሚ ዕውቀት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማዋል ታላቅ በረከት የምናገኝበት ድርሻችን ነው:: አብዛኞቻችን አገልግሎት የሚለውን ቃል ከስብከት እና ከመዝሙር ጋር ብቻ በማያያዝ በየሞያችን የተቀበልነውን መክሊት ቤተ ክርስቲያንን ሳናገለግልበት ቀብረነው እንገኛለን:: በምህንድስና፣ በህክምና፣ በትምህርት፣ በሕግ ፣በሕዝብ አስተዳደር፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በቋንቋዎች ጥናት፣ በሂሳብ ሥራ እና በመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች የሰለጠንን ምእመናን ይህንን ጥበብ ላደለን ለልዑል እግዚአብሔር ምሥጋና የምናቀርብበት፣ የጥበቡን ዐሥራት በማውጣት በረከት የምንቀበልበት፣ ቤተ ክርሰቲያን ከዘመኑ ጥበብ ጋር እንድትጓዝና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድናገኝ የሚኖረው አስተዋጽኦ ታላቅ ነውና ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመቅረብ በሞያችን ድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልጋል:: በገንዘብ ቢተመኑ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ሥራዎች በዕውቀታቸው ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ባሉ ጥቂት ምእመናን እየተከናወኑ ቢሆንም ቤተ ክርሰቲያናችን ካላት በርካታ ምእመናን እና ከምእመናኑ ካላቸው የሞያ ስብጥር አንጻር ምንም አልተሠራም ለማለት ያስደፍራል:: ስለዚህ በእውቀታችንና በሞያችን ቤተ ክርሰቲያንን ለማገልገል የምንነሳበት ወቅት አሁን ነውና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናችን ቀርበን የድርሻችንን እንወጣ::

3. የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የኢኮኖሚ ዐቅም ማጎልበት:-

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላት ወይም የሚኖራት የኢኮኖሚ አቅም የተሟላና ዘላቂ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎትን ያለማቋረጥ በሰፊው መስጠት መቻልዋን ሊያረጋግጡልን ከሚችሉ መለኪያዎች አንዱ ነው:: በሚሊዮኖች የምንቆጠር ምእመናን ከልደት እስከ ሞት ለእኛው ሕይወት የሚቀደሰው ቅዳሴ፣ የሚበራው ጧፍና ሻማ ፣የሚታጠነው እጣን ፣ የምንቀባው ሜሮን፣ የምንጠጣው ጸበል፣ የምንባረክበት መስቀል፣ በአጠቃላይ በውስጥ በአፍአ ለአገልግሎት የሚውሉ ንዋየ ቅድሳት በሙሉ ዘወትር ሊገኙ የሚችሉት በልጅነታችን አምነን ለቃሉ ታዛዥ ሆነን የሚጠበቅብንን ዐሥራት አውጥተን ስንገኝ ነው:: በተጨማሪ በክህነትና በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ባለሞያዎች ወርሃዊ ደመወዛቸውን አግኝተው አገልገሎታቸውን በትጋት እንዲወጡ ለማስቻል ከምናወጣው ዐሥራት በተጨማሪ የቤተ ክርሰቲያኒቱን የገቢ አቅም ማጠናከር በሚያስችሉ ሥራዎቸም ላይ መረባረብ ግድ ይለናል:: በበርካታ ምእመናን ዘንድ ዐሥራት የማውጣት ልምድ የተዳከመ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም በ 21 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደቀደመው ሁሉ ጃንጥላ ዘቅዝቆ ከመለመን ነጻ መሆን አልቻለችም:: ለዚህ የሚጠቀሱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይ ማእከላዊ የፋይናንስ አስተዳደር አለመኖሩ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ደግሞ የአገልጋዮችዋን የዕለት ጉርስ እንኳን መሸፈን የማይችል በመሆኑ በርካታ አገልጋዮች የዕለት ጉርስ ፍለጋ ከአገልግሎት እንዲለዩ እያደረገ ነው:: በአብዛኛው በልመና በሚተዳደሩ የአብነት ትምህርት ቤቶችም ተተኪ የሆኑ ዲያቆናት ካህናትና ሊቃውንትም እንዳይኖሩ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም:: ስለዚህ ዘመናዊ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመፍጠር የቤተ ክርሰቲያነቱን አገልግሎት ዘላቂ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል:: በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የኢኮኖሚ አቅምን የማጠናከር በጎ ጅምር ለምሳሌ ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ዳቦ ቤትና ወፍጮ ቤት ግንባታ፤ የንብ ማነብና የከብት ማድለብ ሥራ፣ የእደ ጥበብ ሥራ ፣ የንዋየ ቅድሳት ሱቆች የመክፈት ሥራ የመሳስሉትን ማጠናከር እና ሌሎችም ልምድ ቀስመው ይህንኑ ሥራ እንዲያከናወኑ ዐቅም ለመፍጠር መረባረብ ያስፈልጋል:: በየዓመቱ አገራችን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ በርካታ አገር ጎብኝዎች(tourists) በአብዛኛው የሚጎበኙት እንደ ቅዱስ ላሊበላ ያሉ ጥንታውያን አብያተ ክርሰቲያናትን እና ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ጠብቃ ያኖረቻቸውን ጥንታውያን መጻሕፍት፣ ሥዕላት እና ሌሎች ንዋየ ቅድሳት ሲሆን ከዚሁ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን የማድረግ ሥራ መሥራትም ይጠበቅብናል:: ለምሳሌ ጎብኝዎቹ ጎብኝተው ሲጨርሱ ሊገዙት የሚገባ ነገር በተመጣጠነ ዋጋ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በእነዚህ ተግባራት እና በሌሎችም አዋጭነት ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች (investments) ላይ መዋዕለ ንዋይ ብታፈስ ሊገኝ የሚችለው የኢኮኖሚ ዐቅም ደመወዝተኛ ሠራተኞችን ከማስተዳደር ባሻገር ቤተ ክርስቲያኒቱን በሁሉም መስክ እንድትጠነክር የሚያደርግ ነውና ትኩረት ሰጥተን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት ያስፈልጋል::

 4. ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ:-

ቤተ ክርስቲያንን ዘወትር ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ፈተና መከላከልና መጠበቅ ከእያንዳንዱ ምእመን ከሚጠበቁ የሥራ ድርሻዎች አንዱ ነው:: ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚታዩ ምንጫቸው የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እጆችና ሀብት የሆኑ በርካታ ፈተናዎች/ችግሮች ሁላችንም ድርሻችንን በተገቢው መንገድ ካለመወጣታችን የተወለዱ ናቸው:: በርካታ ምእመናን ድርሻችን ቅዳሴውን አስቀድሶ፣ በዐለ ንግሱን አክብሮ ወደየጎጆአችን መሄድ ብቻ ስለሚመስለንና የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የካህናት ጉዳይ ብቻ አድርግን ስለምንመለከት በአጭሩ ሊቀጩ የሚገባቸው ፈተናዎች በየቦታው ተስፋፍተው ቤተ ክርሰቲያንን እስከማዘጋት ምዕመናንንም እስከ መከፋፈል ደርሰዋል:: በዚህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የመጠበቅ ሥራ ምእመኑ ያለው ተሳትፎ እጅግ በጣም አናሳ መሆኑን የተረዱ የተሓድሶ አቀንቃኝ መናፍቃንም በቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት እየተገኙ የኑፋቄ መርዛቸውን ለመትፋት ደርሰዋል :: ከእናት ቤተ ክርሰቲያን የተወለድን የተዋሕዶ ልጆች በዚህ ፈተና ወቀት እናታችን ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት ለመከላከል ድርሻችንን መወጣት ሲገባን ወይ ጉድ እንዲህ ሆነ?! እንዲህ ተፈጠረ?! እንዲህ አደረጉ?! በማለት ዳር ሆኖ መመልከት መፍትሔ አያመጣም:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእኔ እናት ናት፤ ለእናቴ ችግር ከእኔ በላይ ማን ቀድሞ ይደርሳል? በማለት በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ባሉ አብያተ ክርሰቲያናት ጉዳይ ላይ ሁላችንም በባለቤትነት ልንንቀሳቀስ ያስፈልጋል:: ዳር ሆነን የምንመለከትበት ጊዜ ከእንግዲህ አብቅቷል::

የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ዳር ሆኖ በመመልከት ያሳለፍነው ጊዜ ስመ ሥላሴ እንዳይጠራ የሚሹ የተሓድሶ አራማጆች በየአውደ ምሕረቱ ሲፏልሉ ለማየት አድርሶናል፣ የአጋንንትን ስም እየጠሩ የሚያሟርቱ አስማተኞች በጸበል አጥማቂነት ስም በየጸበሉና በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ምእመናን ሲዘርፉ ለማየት አድርሶናል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ያልሆኑ አታላዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ ቆብ፣ቀሚስ፣ መስቀልና ጃንጥላ ተከልለው በየጎዳናው የምእመኑን ገንዘብ ሲዘርፉና አመሻሽ ላይ በየመሸታው ሲጨፍሩበት ለማየት አድርሶናል:: በየደብሩ ወደ ግለሰቦች ኪስ የሚገቡ ሙዳየ ምጽዋት ሲሰለፉና ሲዘርፉም ለማየት ደርሰናል:: ከድሀ ምእመናን በንግስ፣ በቅዳሴ ፣በስዕለት የተሰበሰበ ገንዘብ ወርቅና ሌሎችም ውድ ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያን ባለቤት የሌላት እስኪመስል ድረስ ወደ ግለሰቦች ቤት ሲገባ ለማየት በቅተናል:: በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል የተሰየሙ የሰበካ ጉባኤ እና የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴዎች በቡድን በመደራጀትና በመመሳጠር የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ሲዘርፉ ለማየት በቅተናል:: ከሀገር ውጭም አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በዘር ከፋፍሎ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጉራጌ ፣የወላይታ ፣የሰሜን ፣የደቡብ በማለት ምእመኑን ግራ የሚያገባና አንገት የሚያስደፋ ኢክርስቲያናዊ ሥራ ሲሠራ ለማየት አድርሶናል::ሐጢኣት በገንዘብ የሚሰረይ ይመስል እንድንጸልይልሽ፣ ለነዳያን እንድንሰጥልሽ ይህን ያህል ሺህ ብር አምጪ የሚሉ፤ ለዚህ ሓጢአት ንስሐ መስጠት አስቸጋሪ ስለሆነ ይህን ያህል ብር አምጣ በማለት የማይገባ ነውር ሲፈጽሙ የሚገኙም አሉ፡፡ ምእመናንን ከአባቶቻቸው ካህናት ለመለየት ሻሽ ጠምጥመው ቆብ ደፍተው ቄስ መነኩሴ መስለው እየሰከሩ፣አጽዋማትን እየሻሩ ሌላም ጸያፍ እና ክፉ ሥራ በመስራት የተጠመዱ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ተልዕኮ ያነገቡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ መልክ የማፍረስ ሥራ ላይ ተሰማርተዋልና ቤተ ክርስቲያንን ከዚህ እኩይ ተግባር ለመታደግ እያንዳንዱ ምእመን ሊረባረብ ያስፈልጋል:: “በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? (ሐጌ 14) የሚለው ጥያቄ ይመለከተናልና ድርሻችንን እንወጣ::

5. ተተኪ ትውልድ ማፍራት:-

ለአንዲት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘላቂነት የተተኪ ትውልድ መኖር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው:: ካለንበት ዘመን ባሻገር በቀጣይ ዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ከነተቀደሰ ሥርዓቷ ሊረከባት፣ ሊያቆያት፣ ሊያገለግላት፣ ሊገለገልባት እና ሊድንባት የሚችል ተተኪ ትውልድ እንዲኖር ምዕመናን ድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልጋል:: ከአብራካችን የተከፈሉ ልጆቻችንን በቤተ ክርስቲያን ይዘን በመገኘት ስርዓቱን ማስተማር፣ ማስባረክ ፣ፍቅሩን ማስረጽ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የእነርሱ መሆኗን እያሳወቁ ማሳደግ ያስፈልጋል:: በሰንበት ትምህርት ቤት እና በቤተ ክርስቲያን በሚዘጋጁጉባኤያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት እንዲከታተሉና ራሳቸውን ከመናፍቃን እንዲጠብቁ በምግባርም እንዲልቁ ማድረግ ከወላጆች ይጠበቃል:: በዘመናችን በአብዛኛው ወላጆች ለራሳቸው መንፈሳዊ ማንነት ብቻ በከፊል በመሮጥ ላይ ሲሆኑ የልጆች መንፈሳዊ ሕይወት ጉዳይ ግን በእጅጉ ተዘንግቷል:: ይህም በአንድ ጎጆ ስር የሚኖሩ የተለያየ እምነት ያላቸው የቤተሰብ አባላት መኖር ፤ ወይም በርካታ እምነት የለሽ ዘር በመብቀል ላይ ያለባቸው ቤተሰቦች መበራከት ከሚጠፉት ነፍሶች ባሻገር የወደፊቱን የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድ ጉዳይ አሳሳቢ ያደርገዋል:: ስለዚህ ምእመናን ዘሮቻችን የወደፊት የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ መሆናቸውን እያስተዋልን ልጆቻችንን በመንፈሳዊ ሕይወት ልንቀርጽ ያስፈልጋል::

ማጠቃለያ:-

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአምላካችን ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባት የጽድቅ ቤት ናት:: በክርስትና ሕይወት የምንኖር የተቀደሰች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን የመንፈስ ቅዱስ ግምጃ ቤት በተሰኘች የመንፈሳዊ በረከት ቤታችን በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንኖር ከሚጠበቁብን በርካታ የቅድስና ሥራዎች መካከል፤ የክርስትና ሕይወት የሚጠይቀውን ምግባር በማከናወን አርኣያ ሆኖ መኖር፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተሰጠን መክሊት ሁሉ ማገልገል፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የኢኮኖሚ ዐቅም ማጎልበት እና በጎ ጅምሮችን ማጠናከር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ሊያፈርሷት እየታገሉ ካሉ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ነቅቶ መጠበቅና መከላከል እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን ከነሙሉ ሥርዓቷ የሚረከብ ተተኪ ትውልድ የማፍራት ሥራን መሥራት እና በትጋት ማከናወን ይጠበቅብናል:: በአጠቃላይ ዘመኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሩቅ ሆነን የምንሳለምበትና ሲሞላልን ብቻ የምንጎበኝበት ሳይሆን ጠጋ ብለን ድርሻዬ ምንድን ነው? ብለን ጠይቀን ለሥራ የምንነሳበት ወቅት ነውና ድንገት ዐረፍተ ዘመን ሳይገታን ወይም ሳይቀድመን ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅብንን ድርሻ ለመወጣት እንትጋ:: ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችንም ጋር ይሁን:: አሜን::