የግቢ ጉባኤያት በእንግሊዝ ፡ ምዝገባ ጀምረናል!

«የግቢ ጉባኤ» ምንድን ነው?

ማኅበረ ቅዱሳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሰጠችው ኃላፊነት አንዱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መደበኛ ትምህርታቸውን በመማር ላይ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የሚኖራቸውን የተጣበበ ጊዜ እና የአኗኗር ዘይቤያቸውን ያገናዘበ ልዩ መርሐ ግብር በማዘጋጀት መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያገኙና በኋላ በሥራ ዓለም ሲሰማሩ በሃይማኖት ጸንተው፣ በምግባር ታንጸው በመገኘት በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ነው። ይህንን ትምህርት የሚከታተሉበት እያንዳንዱ መንፈሳዊ ጉባኤ ወይም አንድነት ደግሞ «የግቢ ጉባኤ» በመባል ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ከ300 በሚበልጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ120,000 በላይ ተማሪዎችን እንደየትምህርት ቆይታቸው በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት/curriculum/ መሰረት እያስተማረ ይገኛል።ማኅበረ ቅዱሳን ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች ቡራኬ ተማሪዎችን ማስመረቅ የጀመረ ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት ሃያ አመታት ከ200,000 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል። ባለፈው አመት ብቻ ከ40,000 በላይ ተማሪዎች በአባቶች ቡራኬ ተመርቀዋል። ተመራቂዎቹም ዛሬ በመላው ዓለም በያሉበት ቤተ ክርስቲያንን በተቻላቸው ሁሉ  እያገለገሉ ይገኛሉ።

በእንግሊዝ የሚቋቋሙት ግቢ ጉባኤያትስ?

ማኅበረ ቅዱሳን ይህን ወጣቱን የማስተማር አገልግሎቱን በአገር ቤት ብቻ ሳይወስን በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በእስያ እና በአፍሪካ የግቢ ጉባኤያትን አቋቁሞ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማረ ይገኛል። በዚሁ መሰረት በማኅበረ ቅዱሳን የዩኬ ቀጠና ማዕከልም በእንግሊዝ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለአንድ አመት ሲያጠና ቆይቶ በዚህ አመት በለንደን እና በአንድ ሌላ ከተማ የግቢ ጉባኤ ለመጀመር ተማሪዎችን እየመዘገበ ይገኛል። የእነዚህ የግቢ ጉባኤያት መጀመር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመላው ዓለም ለምታደርገው ሐዋርያዊ ጉዞ ከሚያበረክተው ጉልህ አስተዋጽ በተጨማሪ እዚህ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።

የትምህርት አይነቶቹ ምን ምን ናቸው?

ማኅበሩ ወጥነት ያለውና ሁሉም ግቢ ጉባኤያት የሚጠቀሙበት  ሥርዓተ ትምህርት/Curriculum/ ያዘጋጀ ሲሆን  በእንግሊዝ የሚኖሩትም ግቢ ጉባኤያት ይህንኑ ሥርዓተ ትምህርት ይከተላሉ። አጠቃላይ የሚከተሉትን የትምህርት አይነቶች/ኮርሶች/ ያቀፈ ሲሆን ተማሪዎች እንደየቆይታቸው የተመረጡ ኮርሶችን ይወስዳሉ።

የትምህርት አይነት በቅደም ተከተል መለያ ቁጥር የተመደበለት
ሰዓት
የትምህርተ ክርስትና መግቢያ ትክመ111 9
ነገረ ሃይማኖት ነገሃ112 19
ክርስቲያናዊ  ሕይወት እና ሥነ ምግባር ክሕሥ123 23
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መቅጥ211 19
ነገር ማርያም ነገማ222 12
የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት እና ሥርዓት ቤምሥ311 18
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቤክታ322 25
ነገረ ቅዱሳን ነገቅ323 10
ትምህርተ አበው ትምአ411 9
ልሳነ ግዕዝ ልሳግ422

11

ሐዋርያዊ ተልእኮ ሐዋተ423 10

 


(በዩኬ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መጠነኛ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ)

ትምህርቱ ለሁሉም አማካይ በሆነበት በለንደን እና በተማሪዎች ብዛት ታይቶ በሚመረጥ አንድ ሌላ ከተማ ይሰጣል። ለተማሪዎች አመቺ ሆኖ በተገኘ ቀንና ሰአት በየሁለት ሳምንቱ ለሁለት ለሁለት ሰዓት የሚሰጥ ሲሆን ለእያንዳንዱ ኮርስ መጻሕፍት  እና ሌሎች መርጃዎች ይቀርባሉ።

ለመመዝገብ መሥፈርቱ ምንድን ነው?

በእነዚህ የግቢ ጉባኤያት ለመመዝገብ የሚያስፈልጉት:-

  • በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተጠመቀ፣
  • ሁለት አመት እና ከዚያ በላይ ቆይታ ባለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም (ኮሌጅ/ዩንቨርስቲ)  ትምህርት የሚከታተል ሆኖ መገኘት ብቻ ነው።

በመሆኑም የቤተ ከርስቲያንን ዶግማ እና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት አውቆ ፈጣሪን እያስደሰቱ ለመኖር እና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ በመሆኑ እርስዎም በዚህ ጉባኤ እንዲሳተፉ በቤተክርስቲያን ስም ጥሪያችንን እያስተላለፍን መልእክቱን ለሌሎችም በማስተላለፍ እንዲተባበሩን በልዑል  እግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።

እንዴት መመዝገብ እችላለሁ?

ሙሉ ስሞዎን፣ ትምህርቱን ሊከታተሉበት የሚችሉበትን ከተማ(ዎች)፣ የስልክ ቁጥርዎን እና የኢሜል አድራሻዎን በዚህ ቅጽ በመሙላት ይመዝገቡ [የመመዘዝገቢያ ቅጽ]

ለተጨማሪ መረጃ በኢሜይል UK@mkEurope.org ወይም በስልክ ቁጥር 075-0763-0127 ያግኙን።

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

በማኅበረ ቅዱሳን፣ አውሮፓ ማዕከል፣ የዩኬ ቀጠና ማዕከል