በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል (ማቴ. 6፣4).

በዲ.ን ኃይሉ ተረፈ

ኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባዉና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኅቡዕ በምንፈጽማቸዉ ሥራዎች ሁሉ እዉነተኞች ተጠቃሚዎች እንድንሆን ሥራዎቻችን ሁሉ በእርሱ ዘንድ ሚዛን የሚደፉና የሚታዩ እንዲሆኑ “በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከልሃል”  (ማቴ. 6፣4) በማለት ይመክረናል፡፡ እግዚአብሔር ሰዎች ያላዩትን ሁሉ የሚያይ፣ በሰዎች ዘንድ ዋጋ ያልተሰጠዉን እርሱ ግን ዋጋ የሚሰጠዉ፣ ለሁሉም እንደ ሥራዉ የሚከፍል እዉነተኛ ዳኛ ስለሆነ ዛሬ ለምንፈጽማቸዉ ክርስቲያናዊ ሥራዎች በግልጥ እንደሚከፍለን ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ም.25፣31 ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ያለዉን ስንመለከት  ሰዎች ለሠሩት ለበጎዉ ሥራቸዉ የዘላለም ሕይወትን፤ ለክፉ ሥራቸዉ ደግሞ የዘላለም ኩነኔን በግልጥ እንደሚቀበሉ እንገነዘባለን፡፡

እንደ ጻድቁ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ (ዘፍ. 39) የመሳሰሉ ብዙ ቅዱሳን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በአጠገባቸዉ መሆኑን ሳይዘነጉ ስለእምነታቸዉ ፈተናዎችን ታግሰዉ በምድርም በሰማይም ዋጋቸዉን ያገኙትን አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን በመመልከት በስዉር በሚያየን አምላክ ፊት ሥራዎቻችን ምን ያህል ተወዳጆች እንደሆኑ መመዘን ይገባናል፡፡ ጌታችን በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 8፣17 ላይ “የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይወጣ የተሸሸገ የለም፡፡” ብሎናል፡፡ ስለዚህ ጊዜዉን ላናዉቀዉ ብንችልም አንድ ቀን በፊቱ እንገለጣለን፡፡ በዚህ ጊዜ በፊቱ ይዘነዉ የምንቀርበዉ ዋጋ ሊኖረን ይገባናል፡፡ ሳይሰሩ ሽልማት፣ ሳይጋደሉም ገነት፣ መንግሥተ ሰማያትን ማግኘት አይቻልም፡፡ ዋጋ የምናገኝበት የጽድቅ ሥራችንም ሆነ የምንቀጣበት ኃጢአታችን ይከተለናል፡፡

መልካም አገልግሎታቸውን በስውር እየፈጸሙ እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኙ ቅዱሳን ለአብነት እንመለከታለን:- ለሁለት አባቶች በግብጽ ዉስጥ በአንድ ከተማ በትዳር እየኖሩ በስውር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙ እኅወ ክርስቶስ እና ማሪያ የደረሱበትን ደረጃ  እግዚአብሔር ገለጠላቸው። እነርሱም ተነስተው ወደ እነ እኅወ ክርስቶስ እና ሚስቱ ማሪያ መንደር ሄዱ። እርሷንም አገኟትና “ባልሽ የት ነው?” አሏት። እርሷም “እርሱ እረኛ ነው በጎችን እየጠበቀ ነው” አለቻቸው። ወደቤትም አስገባቻቸው። ማታ ሲሆን እኅወ ክርስቶስ በጎቹን ይዞ መጣ፤ አረጋውያን አባቶችን ባያቸው ጊዜ በፊታቸው ማዕድ አቀረበ፤ እግራቸውን ሊያጥብም ውኃ ይዞ መጣ። እነርሱም “መጀመሪያ አጠራርህና አኗኗርህ እንዴት እንደ ሆነ ሳትነግረን ምንም ነገር አንበላም” አሉት። እኅወ ክርስቶስም በየውሀት ልብ “እኔ የበጎች እረኛ ነኝ፤ ይህቺም ሚስቴ ናት” አላቸው። አረጋውያኑ መጠየቃቸውን ቢቀጥሉም እርሱ ግን ምንም ነገር ሊላቸው ፈቃደኛ አልሆነም። እነርሱም “ወደአንተ የላከን እግዚአብሔር ነው” አሉት። ይህን ሲሰማ ፈራና እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህ በጎች የተሰጡን ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ የሚሰጠንን (የሱፍ ፀጉራቸውን)  ከሦስት እንከፍለዋለን፤ አንዱን ክፍል ለድሆች እንሰጣለን፤ ሌላውን ክፍል ለእንግዶች፤ ሦስተኛውን ደግሞ ለራሳችን እናደርጋለን። ሚስቴን ካገባኋት ጊዜ ጀምሮ እርሷም ሆነ እኔ ሰውነታችንን አላሳደፍንም፤ ሁለታችንም ድንግልናችንን ጠብቀን አለን፤ የምንተኛውም ለየብቻችን ነው። በሌሊት ማቅ ደርበን እናድራለን፤ ቀንም ልብሳችን ይሆናል። እስካሁን ድረስ ይህን ነገር ማንም ሰው አያውቅም።” ይህን ሲሰሙ እያደነቁ ወጥተው ሄዱ። (ምንጭ:- ከበረሐውያን ሕይወትና አንደበት በዲን. ያረጋል አበጋዝ፣ ጥር 2003 ዓ.ም.)

ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት፡- “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፣ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ፡፡” መዝ. 138(9)፣ 16 እንዳለ፣ እንኳን ከተወለድን በኋላ የሠራናቸዉ ተግባራት አካላችን  ከመሠራቱ በፊት እንኳን በፈጣሪያችን ፊት የታወቅን ነን፡፡  ስለዚህ ሰዎች ስላደነቁን፣ ስላመሰገኑን የሚጨመርልን ዋጋ፣ ሰዎች ስላላደነቁን ወይም ስላላመሰገኑን የሚቀርብን ዋጋ የለም፡፡ እንዲያዉም ሰዎች እንዲያዩልን ብለን ምንም ነገር እንዳናደርግ ይልቁን እግዚአብሔር ስለሚያየን ብለን ማናቸዉንም ነገሮች በጥንቃቄና በማስተዋል ልናደርግ ይገባናል፡፡ ሰዎች ዋጋችንን ከሰጡን ከእግዚአብሔር የምንቀበለዉ ምንም ዋጋ አይኖረንም፤ “እዉነት እላችኋለሁ ዋጋቸዉን ተቀብለዋል” ማቴ. 6፣5 እንዲል፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር እንኳን የሠራነዉን ያሰብነዉንም ሳይቀር የሚያዉቅ አባት ነዉና የቱንም ያህል ከሰዎች ብንሰወር የሚቀርብን ዋጋ የለም፡፡

በተጨማሪምቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር ልቡናንና ኩላሊትን ይመረምራል፤” መዝ. 7፣9 ይለናል፤  ቅዱስ ጳዉሎስም፡- “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነዉ እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም፡፡” ዕብ. 4፣13 ብሏል፡፡ ዛሬ የዓለሙን ክፋትና ርኩሰት ተገንዝበዉ በስዉር የሚያለቅሱ ቅዱሳን፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲስፋፋ ቀን ከሌሊት በትጋት የሚጋደሉ አገልጋዮች ሁሉ ድካማቸዉን ምንም ሰዉ ባይረዳዉና ባይቆጥርላቸዉ የማይረሳቸዉ አምላክ የከበረ ዋጋቸዉን ብልና ዝገት በማያበላሸዉ በወርቅ መዝገብ ጽፎ የሚያቆያቸዉ መሆኑ እሙን ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ ደግሞ እግዚአብሔር አያይም፣ አይፈርድም ብለዉ የሥጋ ምቾታቸዉን ብቻ እያጣጣሙ መንፈሳዊ ስንቅ ያላከማቹ (ሉቃ. 12፣16-21) በፍርድ ቀን ርቃናቸዉን ሆነዉ የሚያለቅሱ ይሆናሉ፡፡  እንግዲህ ክብራችንና ባለጠግነታችን በሰዉ ፊት ብቻ እንዳይሆን፣ የምንፈጽማቸዉም አገልግሎቶች ለታይታ ብቻ ሆነዉ የዉዳሴ ከንቱ ነቀዝ እንዳያጠፋብን በመጠንቀቅ ልንመላለስ ይገባናል፡፡ ይህች ዓለም የፈተና ዓለም ናት፡፡ ብዙ ጎታቾች አሉ፣ ብዙ የሚያዘናጉ ጉዳዮችም አሉ፡፡ እኛ ክርስቲያን የሆነዉ በዚህ ዓለም ብቻ ለመኖር አይደለምና ለዘለዓለም ስለምንኖርባት መንግሥተ ሰማያትም የሚገባ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ደግሞ ሰዉ ባያየን ዘወትር የሚያየን አባታችን እግዚአብሔር ስለሆነ ሥራችን በፊቱ ያማረ እንዲሆንልን የሥጋን መሻት እየገታን ለነፍሳችን የሚጠቅማትን ለማድረግ መጋደል ይገባናል፡፡

በአጠቃላይም እግዚአብሔር አምላካችን የረሳዉን ለማስታወስ መዝገብ የሚያገላብጥ ወይም ያላየዉን እንዲነግሩት ምስክር የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ሁሉን ያያል፣ ሁሉን ያዉቃል፡፡ የምንኖረዉ በእርሱ ፊት ነዉና፤ ሰዉ ብዙ ጥንቃቄ ሊያደርግ የሚገባዉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢያት እንዳይሰራ፣ ክፉ ነገርንም እንዳይፈጽም ነዉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈዉ ወንጌል ላይ ጌታችን “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ሥራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እዉነትን የሚያደርግ ግን ሥራዉ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡” (ዮሐ. 3፣20) እንዳለን ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቱ የሚያደርግ ሥራዉን ብርሃን ወደ ሆነ አምላኩ ይዞ ይቀርባል፤ ከእግዚአብሔር የሚርቅ ግን ከብርሃን አባቱ ተለይቶ በጨለማ ይኖራል፡፡ በብርሃንም በጨለማም፣ በቀንም በሌሊትም፣ በስዉርም በገሃድም ለተሰራዉ ስራ ሁሉ ዋጋን የሚከፍል እግዚአብሔር ነዉና መልካሙን ዋጋ ለመቀበል እንበቃ ዘንድ በመልካም ሥራ እንበርታ፡፡ በስዉር የሚያይ አባታችን በግልጥ ይከፍለናልና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!