ሕፃን ተወልደ ለነ ወልድ ተውኅበ ለነ፤ ሕፃን ተወለደልን ወንድ ልጅም ተሰጠን፡፡ ኢሳ 9፣6 (ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ)

ዲ/ን ውብዓለም ደስታ

ታኅሣስ ፳፰ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.

lidet-2005

አዳም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ተላልፎ አትብላ የተበለውን ዕፀ በለስ በልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፤ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈርዶበት ከገነት ከወጣ በኋላ፤ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፤ ገነትን ታህል ቦታ አጥቼ ቀረሁን እያለ ሲያዝን፤ ጌታ ኀዘኑን አይቶ ልመናውን ሰምቶ ‹‹በኀሙስ እለት ወበመንፈቃ ለእለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ፣ ወእትቤወከ በመስቀልየ ወበሞትየ፤በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ በሞቴ አድንሀለሁ›› መጽሐፈ ቀለሜንጦስ፤ ብሎ ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ጊዜውም ሲደርስ አውጉስጦስ ቄሳር ዜጎቹን ለመቁጠር ፈልጎ ወደ ትውልድ አከባቢያቸው ሂደው እንዲቆጠሩ አዘዘ፡፡ መጽሐፍ ‹‹ወወጽአ ትእዛዝ እምኀበ አውጉስጦስ ቄሣር ከመ ይጸሐፍ ኩሉ ዓለም›› (ሉቃ 2፡1) እንዲል፡፡ ጌታም ከዘመኑ ዘመን፣ ከወሩ ወር፣ ከዕለቱ ዕለት ሳያሳልፍ በጽኑ ቀጠሮው ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ፤ በኅቱም ድንግልና በቤቴልሔም የእንግዳ ማረፊያ አልነበራቸዉምና በከብቶች በረት ተወለደ፡፡

ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንዳለ ቅዱስ ዳዊት፤ እግዚአብሔር ለሚሠራው ሥራ ጊዜ አለው፡፡ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ በድንገት የሚሠራ አምላክ አይደለምና ሁሉንም በጊዜው ያከናውነዋል፡፡ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ቀድሞ ለአባቶቻችን በምሳሌና በትንቢት የገለጸውን ይፈጽም ዘንድ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በተዋሕዶ ጌታ ተወለደ፡፡ አምላክነቱ ሰውነቱን ሳያጠፋው ሰውነቱ አምላክነቱን ሳያሳንሰው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆን ተገለጠ፡፡ “ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀንሽ ተወሰነ”፡፡ እንዳለ አባ ሕርያቆስ (ቅዳሴ ማርያም ቁ. 46)

ብዙ ምስጢር ያለውን የጌታ ልደት ልዩ  ከሚያደርጉት እጅግ ብዙ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ፤

1. በሴቶች ልማድ የተወለደ አለመሆኑ፤

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን የወለደችው በሴቶች የሚደርሰው ሳይደርስባት፣ ሕማም፣ ምጥ ሳይሰማት፣ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ነው፡፡ ልደቱን ያለዘር ያለሩካቤ ያደረገው፤ በዘር በሩካቤ ያላደረገውን ቀዳማዊ/የመጀመርያ ልደቱን/ ለመግለጽ ነው፡፡ ድኅረ ዓለም/ዓለምን ከፈጠረ በኋላ/ ከእመቤታች ያለ አባት መወለዱ፡ ቅድመ ዓለም/ዓለምን ሳይፈጥር/ ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያጠይቃልና፡፡ ‹‹ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ ልደት›› ሃይማኖተ አበው ዘሱኑትዬ፡፡

2. የተነገረው ትንቢት፤ የተመሰለው ምሳሌም ይፈጸም ዘንድ መወለዱ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ «አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተልሔም ሆይ! …..ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራአልም ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ  ይወጣልኛል፡፡ ስለዚህም ወላጂቱ እስከ ምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡» እንዳለ (ሚክ 5፡2)፡፡ ትንቢት የተነገረለት መድኃኒት (ኢሳ.9: 6-7)፣ መድኃኒትንም ለሕዝቡ ሰደደ (መዝ 110:9፣ 137:7)፣ የሰው ልጆች ጩኸት ተፈጸመ ጌታም በቤተልሔም ተወለደ፣ ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሳም ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ (ኢሳ. 64፡1) ይሉ ለነበሩት ሁሉ ተወለደ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደው ልጁን ላከ» (ገላ. 4፡4) እንዳለ:: ይወለድ ዘንድ የተነገረው ትንቢት ሲፈጸም አምላክ በቤተልሔም ተወለደ፣ ወንድ ልጅም ተሰጠን፡፡ በልደቱም «ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን» በእውነተኛ የምስጋና ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ መላእክትና ሰዎች አንድ መንጋ ሆኑ፡፡ የሰው ልጅ የመኖር ተስፋውም ለመለመ፡፡ ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ፤ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳች» (ኢሳ 7፡14)፤ የተባለው ትንቢት እውን ሆኖ ወንድ ልጅ ከድንግል ተወልዷልና፡፡

በሌላ መልኩ፡ አዳም ከኅቱም ምድር እንደ ተገኘ፣ ሔዋንም ከኅቱም ጎን ተገኝታለች፡፡ ይህም ጌታ በኅቱም ማኅፀን ለመወለዱ ምሳሌ ነው፡፡ (መዝ 131፡6) (ሚክ 5፡2) ያሉት ኃይለ ቃላት ጌታ ቤተልሔምን የሚወለድባት ከተማ አድርጎ ለመምረጡ የሚያሳዩ ትንቢቶች ናቸው፡፡ እስራኤል ዘሥጋን ከሥጋዊ ሞት የታደጋቸው ምድራዊው ንጉሥ ቅዱስ ዳዊት ከቤተልሔም መመረጡ፤ ሰውን ሁሉ በሥጋ በነፍስ የታደገ የሰማይና የምድር ጌታ በቤተልሔም የመወለዱ ምሳሌ ነወ፡፡

3. ለእርቅና ለሰላም የተፈፀመ መሆኑ

ከአዳም ስኅተት በኋላ በዓለም ላይም ይሁን በፍጥረት መካከል ሰላም ጠፍቶ፣ ጥልና ክርክር፤ ተንኮልና ክፋት ነግሶ ለ5500 ዘመናት ቆይቶ ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ዕጣ በሆነች በቤተልሔም ከተማ በመወለዱ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ጠፍቶ የነበረው ሰላም ተመሠረተ፡፡ ጌታም በድንግል ማኅፀን የተጀመረውን ዕርቅ በመወለድ ለመላው ዓለም ገለጠው፡፡ በዚህ የመገለጥ ምስጢር፣ ምስጢረ ሥጋዌ የተገለጸላቸው መላእክት፣ እረኞች፣ እንስሳት ለእግዚአብሔር የምስጋና መስዋዕት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ›› እያሉ አቀረቡ፡፡ ይህንን በጎ ፈቃድም እረኞች ለዓለም ሁሉ አበሠሩ፡፡ ከዚህም ምስጢር ለሚገባው ብቻ እንጂ ለሁሉም የሚገለጥ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡

የሰላም ንጉሥ፣ የሰላም ጌታ፣ የእርቅ ባለቤት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ከተማ ሲወለድ መላእክት፣ እረኞች፣ እንስሳት በሕብረት ምስጋና ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጆች እያሉ መዘመራቸው ተለያይተው የነበሩ ፍጥረታት መታረቃቸውን፣ ዝምድናቸውን አጽንተው በአንድ ማመስገናቸውን ያሳየናል፡፡ የሰው ልጅም ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ከመላእክት ጋር ለማመስገን መብቃቱን እንረዳለን፡፡ (ሉቃ 2፡8-20)

4. የጌታ ንጉሰ ነገሥትነት፣ ሊቀ ካህናትነትና ስለ ሰው ልጆች ሲል እንደሚሞት በምስጢር የተገለጠበት ቀን መሆኑ

በጌታ ልደት እርቅና ሰላም መስፈኑ፤ እንስሳትና አራዊት ማመስገናቸው ብቻ ሳይሆን የባሕር ውኃ ወተትና ማር፣ ተራሮች እንጀራ፣ እንጨቶችም የበረከት ፍሬ ሆነዋል፡፡ ‹‹በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የእርቅና የሰላም ብሥራት የሆነውን ልደቱን ለማየት፤ የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን ለመረዳት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የዓለም ጠበብት ሁሉ ወደ ቤተልሔም ተጉዘዋል። ከእነዚህም ሰብአ ሰገል የተሰኙት ስማቸው ማንቱሲማር፣ ሜልኩና በዲዳስፋ የሆነ የፋርስ ነገስታት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ጠበብት ልደቱን በኮከብ ተመርተው ከገነት የተገኘውን ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ አምጥተው ገብረውለታል፡፡ ይህንንም እጅ መንሻ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መላእክት፤ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሩፋኤል አምጥተው ሰተውት ነበር፡፡ ንሥዒ ሕጼኪ ብሎ ለሔዋን ሰጣት፡፡ ሔዋን ለሴት ሰጠችው፡፡ ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደረሰ፡፡ ኖኅም ከመርከብ ከወጣ በኋላ ለሴም ሰጠው፤ ሴምም ለመልከጼዴቅ ሰጥቶ አስጠበቀው፡፡ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ሰጥቶት ከአብርሃም ሲወርድ ሲዋረድ በዳዊት በሰሎሞን አድርጎ በአክአዝ ዘመን ቴልጌልፌልሶር የፋርስ ሰው ነው ማርኮ ወሰደውና ከቤተ መዛግብት አኖረው፡፡ የነዚህ የሰብአሰገል የአባታቸው ስም ዥረደሽት ሲሆን ፈላስፋ ነበር፡፡ አንድ ቀን በቀትር ከወንዝ ዳር ሆኖ ሲፈላሰፍ በሰሌዳ ኮከብ ድንግል ሕፃን ታቅፋ አየ፡፡ በሰሌዳም ቀርጾ አስቀመጠ፡፡ ሲሞትም ልጆቹን እንደዚህ አይነት ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ይህን ወስዳችሁ እጅ መንሻ አርጋችሁ ሰጥታችሁ ሰግዳችኁለት ተባረኩ ብሎ ሰጥቷቸው ሞተ፡፡

ጌታ በተወለደ ዕለት ኮከቡ በመታየቱ የጌታን መወለድ ተረድተው፤ አባታችን ያለን ደረሰ ተፈፀመ ብለው ተነሱ፡፡ ምንም እንኳ ሲነሱ ብዛታቸው አስራ ሁለት ቢሆንም፤ ዘጠኙ ጠላት ሲነሳባቸው ከነሰራዊቶቻቸው ተመልሰዋል፡፡ ማንቱሲማር፣ ሜልኩና በዲዳስፋ ግን ኮከቡ እየመራቸው ኢየሩሳሌም ደርሰው፤ ቤተልሔም ጌታ ከተወለደበት የከብቶች ግርግም ተገኝተው ሰግደውለት እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤውን ገብረውለታል፡፡ ወርቅ አመጡለት በባሕርይህ ንጉሠ ነገሥት ነህ ሲሉ፣ ዕጣን አመጡለት የዓለምን ኃጢአት የምታስወግድ ሊቀ ካህን ነህ ሲሉ፣ ከርቤ አመጡለት ስለ እኛ ኃጢአት ተገብተህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፡፡ (ማቴ.2-1-12)፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ የውዳሴ ማርያም ጸሎቱ ‹‹ሎቱ ሰገዱ ሰብአ ሰገል፤ አምጽኡ ዕጣነ ከመ አምላክ ውእቱ፤ ወርቀ እስመ ንጉሥ ውእቱ፤ ወከርቤ ዘይትወሀብ ለሞቱ ማኅየዊ በእንቲአነ ተወክፈ በፈቃዱ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ኄር ወመፍቀሬ ሰብእ፤ ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፤ አምላክ ነውና ዕጣን አመጡለት፤ ንጉሥም ነውና ወርቅ አመጡለት፤ ስለኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነ ሞቱም ከርቤ አመጡለት፤ ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና እንዳለ፡፡ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እመቤታችን የገብስ እንጀራ ጋግራ ሰጥታቸው አገራቸው እስኪገቡ ተመግበውታል፡፡ ቤተልሄም ደርሰው ጌታን አግኝተው ሲመለሱ፤ ሲመጡ ሁለት ዓመት የፈጀባቸውን መንገድ አርባ ቀናት ብቻ ወስዶባቸው ከአገራቸው ገብተዋል፡፡

በአጠቃላይ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰይጣንን ሥራ ሊያፈርስ (1ኛ ዮሐ 3፡8)፣ የጠፋውንና የተጎዳውን አዳምን ሊፈልገውና ሊፈውሰው (ሉቃ 19፡10)፣ ለእኛ ለአዳም ልጆች ሕይወት እንዲበዛልን (ዮሐ 10፡10)፣ አዳም ላይ ነግሶ ይኖር የነበረውን ዲያብሎስን ከሥልጣኑ ሊሽር (ዕብ 2፡14-18)፣ ኃጢአተኞችን ሊያድን (1ኛጢሞ 1፡15) ፣ ስለ እውነት ሊመሰክር (ዮሐ18፡37)፣ የዘላለም ሕይወትን ሊሰጠን (ዮሐ 3፡16)፣ ትንቢትን ለመፈጸምና ለመሳሰሉት ተወልዷል፣ ተሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ አማኑኤል ተባለ፤ (ሉቃ24፡24፣ ዮሐ 5፡46)፡፡   በመሆኑም የጌታን መወለድና ወንድ ልጅ ሆኖ መሰጠት ለምናምን ለእኛ ለሁላችን ነፃነት (ገላ 5:1) ፣ ፍቅር (ሉቃ. 2፡1)፣ ሰላም (ሉቃ. 2፣14) ሆነልን፡፡ ለዚህም ነው እረኞች የተሰጣቸዉን ሕፃኑን ፍለጋ «እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሒድ» (ሉቃ.2-15) ያሉት፡፡ እኛም ድኅነትን ለማግኘት ለተወለደው መድኃኒት ቦታና ጊዜ ሰጥተን ቃሉን ለመስማት፣ እርሱን ለመምሰል፣ እንደ ፈቃዱ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡

ሰብዓ ሰገል እንዳረጉት እኛም ሰውን ሳይሆን፤ ለሁሉም እንደ ሥራው መጠን ዋጋ የሚከፍለውን ጌታን እያሰብን ብርዱን፣ ረሃቡን፣ ጥሙን፣ ድካሙን፣ እንግልቱን፣ ነቀፌታውን ታግሰን ወደ ቤተልሔም /ቤተ ክርስቲያን/ ዘወትር ልንገሰግስ ይገባናል፡፡ ይህን በማድረጋችን እንደ ሰብአ ሰገል መድኃኒት የሆነ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር እናገኘዋለን፡፡ ሕይወትም ይሆንልናል፡፡ ዘመናችንም ይባረካል (መዝ.112፡6-8)፡፡

ከሁሉም በላይ ጌታ የተወለደው የእኛን ኃጢአት ሊያስወግድ፣ ሕማማችንን፣ ሞታችንን ወደ ሕይወት ሊለውጥ ነው፡፡ ስለሆነም ልደቱን ስናከብር ዓለም በምታቀርብልን መሸንገያዎችና የጥፋትና የሞት መንገዶች በሆኑት በዘፈን፣ በስካር፣ በመዳራት፣ በዝሙት፣ በስርቆት፣ በቅናት (ገላ 5፡19) ሳይሆን ይልቁንስ እግዚአብሔርን በማመስገን፣ በመዘመር፣ ቃሉን በመስማት፣ በማሰማት፣ የኃጢአት ሥርየት የምናገኝበትን ሥራ በመስራት ማለትም ንስሐ በመግባት መሆን አለበት፡፡ (የሐ. ሥራ 5፡31)፡፡ ቤተልሔም ሔደን እርሱን ማየታችን፣ ማወቃችን ኃጢአትን እንዳናደርግ፣ ይልቁንም ከኃጢአት እንድንርቅ ነው፡፡ «በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላውቀውም» እንዲል። (1ኛ ዮሐ.3፡6)፡፡ «በሄሮድስ፣ በዲያብሎስና በሠራዊቱ ሀውክ ተደረገ፡፡ በጌታ መወለድ በሰውና በእግዚአብሔር መታረቅ ዲያቢሎስ ድል ተነሳ» እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም በሃይማኖተ አበው፤ እኛም ሁል ጊዜ ጠላት ዲያብሎስን ድል አንድንነሳው የተሰጠንን ልጅነት አጽንተን ልንጠብቅና መክሊታችንን ፍሬ ልናፈራበት ይገባናል፡፡

ለሰው ልጅ ሲል የተወለደውን፣ የዲያብሎስን አሠራር ያፈረሰውን አምላክ ትእዛዙን በመፈጸም ሁላችንም ጌታችን በኢየሩሳሌም የሰጠውን ሠላምና እርቅ በማሰብ በቤተክርስቲያናችን፣ በሀገራችን፣ በዓለማችን ሰላምና እርቅ እንዲሰፍን መሻት ብቻ ሳይሆን ለዚህም መሳካት መትጋት ያስፈልጋል ‹‹ቅንዑ ለእንተ ተዐቢ ጸጋ፤ ይልቁንስ ለምትበልጠዋ፣ ለመልካሟ ጸጋ ቅኑ ትጉ›› (1ኛ ቆሮ 12:31) እንደተባለ፡፡ የተጣላ ሊታረቅ፣ የሰረቀ ሊመልስ ይገባል፡፡ ሐዋርያው እንግዲህ የሰረቀ አይስረቅ እንዳለ ልደቱን የሚያከብር ሰው ስርቆትን፣ መለያየትን፣ ክፋትን፣ ተንኮልን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ጥላቻን፣ መገዳደልን፣ መዋሸትን ወዘተ ሊያስወግድ ይገባዋል፡፡ እረኞች ከመላእክት ጋር እንደዘመሩ ሁላችንም የጌታን ልደት በማክበር በፍቅር በደስታ ያለመለያየት ልንዘምር ልናመሰግን ይገባናል፡፡

በዓለም ሰላም እንዲበዛና መራራ የሆነው የሰው ልጅ ኑሮ እንዲጣፍጥ የመድኅን ክርስቶስን ልደት በመንፈሳዊ ስሜት እንድናከብር ያስፈልጋል:: ምክንያቱም በዓለም ላይ ብዙ የደስታ ልውውጦች እንደ ተደረጉ ብናውቅም የክርስቶስ ልደት ግን የሥጋን ብቻ ሳይሆን የመንፈስንም ለውጥ አስተባብሮ የያዘ በመሆኑ ክርስቲያኖች ለሆን ሁሉ አዲስ ለውጥ ሆኖልናል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስን ልደት ስናከብር አዲስ ልብስን በመልበስ ብቻ ሳይሆን በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ልብ ሆነን ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።›› እያልን በአንድነትና በፍቅር ልናመሰግን ይገባናል፡፡

የመድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ልደቱን ሰምተንና አይተን የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድኅነታችን ምክንያት የሆነች  የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡