ቅድስት
በዲያቆን መስፍን ኃይሌ
የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም
የቤተክርስትያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶ አጠናክሮ ያስተላለፈልን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዓቢይ ጾም ለሚገኙትን እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል ። በዚህም መሰረት የዚህ ታላቅ ጾም ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ተብሎ ተሰይሟል። ቅድስት የሚለው ቃል ግሱ“ቀደሰ” ሲሆን ለየ አከበረ መረጠ የሚል ትርጉም ይይዛል። ቅድስት ማለት የተየች የተመረጠች የከበረች ማለት ነው። ቅዱስ የሚለው ቃል እንደ የአገባቡ ለፈጣሪም ለፍጡርም ያገለግላል። ለፈጣሪ ሲነገር እንደ ፈጣሪነቱ ትርጉሙ ይሰፋል ይጠልቃል ለፍጡር ሲነገር ደግሞ እንደ ፍጡርነቱ እና እንደ ቅድስናው ደረጃ ትርጉሙ ሊወሰን ይችላል። እግዚአብሔርን ቅዱስ ስንል የባህሪይው የሆነ ፣ኃጢአት የማይስማማው ፣ለቅድስናው ተወዳዳሪ ተፎካካሪ የሌለው፣ ወደር የማይወጣለት ፣ዘለዓለማዊ የሆነ ማለታችን ሲሆን ፍጡራንን ግን ቅዱሳን ስንል ቅድስናቸው የጸጋ የሆነ ፤ከእግዚአብሔር ያገኙት ፤እንደነጭ ልብስ ጽድቁም ኃጢአቱም እንደ ዝንባሌአቸው የሚስማማቸው፤ ለቅድስናቸው ማዕረግ ደረጃ የሚወጣለት እንደ ገድል ትሩፋታቸው መጠን ሊጨምርም ሊጎድልም የሚችል ማለታችን ነው። ከፍጡራን መካከል ለእግዚአብሔር የተለዩ ሁሉ በጸጋ የቅድስናው ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ። መላእክት፣ ሰዎች፣ መካናት፣ ዕለታት ፣አልባሳት፣ ንዋያት ሁሉ ለእግዚአብሔር እስከ ተለዩ ድረስ ከቅድስናው በረከት ይሳተፋሉ እንደ የደረጃቸው ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ።
በዚህ ዕለት ስለ ቅድስና እንዲሁም ዘወትር በዕለተ ሰንበት ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ ለጽድቅ ስራ እንድንበረታ፣ ለቅድስና እራሳችንን እንድንለይ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይሰበካል ይነገራል። የሚዘመረውም መዝሙር ” ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ” ትርጉም፦ “ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደላይ አስቡ፡፡“
በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደ ዘመረልን በተለይ ሰንበት ነገረ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚዘከርባት፤ ኅሊናችን ከምድራዊው ሃሳብ ወጥቶ ወደ ሰማይያዊው የሚነጠቅባት፤ ለቅድስና የተለየች ቅድስት ዕለት መሆኗን ይጠቁማል። በቅዱስ መጽሐፍም “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ዘፀ. 20፥8 ተብሏል የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ እራሱ እግዚአብሔር ነው” እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከውቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና“ዘፍ.2፥3 እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ ” የተባለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የባረከውን የቀደሰውን እኛ ድጋሚ የምንቀድስ የምንባርክ ሆነን ሳይሆን በዕለተ ሰንበት እራሳችንን በተለየ ሁኔታ ለቅዱስ ተግባር እንድንለይ ለሥጋችን ከምንፈጽማቸው ተግባራት ይልቅ ለተግባረ ነፍስ እንድናደላ ያስረዳናል። ምንም እንኳን ለስጋችን ስንባክን ጊዜ ቢያጥረን በዕለተ ሰንበት ግን ቅዳሴ ከማስቀድስ ቅዱስ ቃሉን ከመስማት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ከመቀበል እንዳናስታጉል በስርዓተ ቤተክርስትያን ታዘናል።
ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት «ተጋብኡ ኩሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ፡፡” ትርጉም፦ ” ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፡፡” /ፍትሐ ነገሥት ገጽ 254/ ብለው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ከሌሎች ቀናት በተለየ ሁኔታ ትኩረት የምንሰጥበት የምንቀደስበት ዕለት ቅድስት ሰንበት እንደሆነች ተናግረዋል ። ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስም በቅዳሴው ላይ ሰንበት የተቀደስች እና ሕይወታችን እንዲቀደስባት የተለየች ቀን መሆኗን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል “ወንበል ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሰይ ባቲ” ትርጉም “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ያከበራት ዕለት ናትና በእርሷ ፈጽሞ ደስ ይበለን” ሰንበት ለክርስትያኖች ለመንፈሳዊ ደስታ የተለየች ቀን ናት ። የመንፈሳዊ ደስታ ምንጩ በነፍስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት ነው ። ሰው የኃጢአትን ሸክም በንስሃ ሲያራግፍ፤ ነፍሱ በጸጋ እግዚአብሔር ስትቃኝ የሚሰማውን ደስታ በሌላ በምንም መንገድ ሊያገኘው አይችልም። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ሰንበት ቅድስትና ለቅድስና የተለየች ቀን መሆኗን ያስተማረን አስቀድሞ በነብያት ትንቢት ያናግር የነበረ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ነው ።
ስለ ሰንበት መለየትና መቀደስ እንዲሁም የመንፈሳዊ ሐሴት ቀን ለመሆኗ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት መዝሙሩ እንዲህ ብሎ ነበር “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” መዝ. 117፥24 ቅዱስ ዮሐንስም ራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” ራእ. 1፥10 ሰንበት የእኛ ቀን ሳትሆን ለጌታችን የምንሰራባት የምንለይባት ፣የምንቀደስባት፣ ነገረ እግዚአብሔርን የምንዘከርባት የጌታ ቀን ናት ። ለቅድስና የተለየች ቅድስት ቀን ናት ። በተለይ የክርስቲያን ሰንበት እሑድ “በኵረ በዓላት” ትባላለች በኵር ታላቅ እና መጀመርያ ማለት ነው የመዳናችን መሰረት የተወጠነባት የጌታ የጽንሰቱ ቀን ዕለተ ሰንበት ናት ፤የመዳናችን ማረጋገጫ ፣የእምነታችን መሰረት ፣የበዓላት ሁሉ ዓቢይ ትንሳኤው የተፈጸመው በዕለተ ሰንበት ነው። እንግዲህ በዚች ቅድስት ዕለት፥-ለቅድስና በተለየች ዕለትስ ሥጋውንም ነፍሱንም በሚያርያረክስ ተግባር የተሰማራስ ለነፍሱ ምን ዋስትና ይኖረዋል?
ቅድስት በተባለች በሰንበት እሑድ ማንም በምንም ምክንያት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ከመሄድ እንዳያስታጉል በስርአተ ቤተክርስትያን ተቀምጦልናል። ሌላው ቀርቶ በዕዳ በብድር በቀረጥ በግብር በአስራት በበኩራት ይሉንኝታ ፈርቶ ማንም ቅድስት በምትባል በእሑድ ሰንበት ቅዳሴ እንዳያስታጉል ማንም ማንንም በዚህች ቅድስት ዕለት ምንም አይነት እዳ እንዳይጠይቅ ታዟል። “ወኢይኅሥሥ መኑሂ በይእቲ ዕለት ንዋዮ እምካልኡ ወኢይጽሐቅ አሐዱሂ እምእመናን በእንተ ኃሥሠ ዕዳ ። አው ተጻልኦ አው በዘይመስሎ ለዝንቱ። ወይሑሩ ቦቱ ኩሉሙ ሰብእ ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወይምጽኡ ኲሉ ለለ ፩ ፩ እምእመናን ኅቤሃ በንጽሕ ወበትህትና ዘእንበለ ፍርሃት እምነ መኮንን ወእም በዓለ ዕዳ አው እምፈታሒ አው ዘይመስሎ። ወእመሰ ተሀበለ ፩ሂ ክርስቲያን ምክዕቢተ ይፍዲ ” ትርጉም፦ “ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳ በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት ፤ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት፣ ዋስ መያዝ አይገባውም ። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው ይምጡ እንጂ ። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን ፣ኤጲስቆጶስ ዐሥራት በኵራት ፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ። ከነጋድራሶች አንዱ እንኳ ወደ ቤተክርስትያን ከሚሄዱ ሰዎች ቀረጥ ይቀበል ዘንድ የድፍረት ሥራ የሠራ ቢሆን እጽፍ አድርጎ ይክፈል። ” ፍትሐ ነገሥት ገጽ 258-259።
ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህን ያህል ጥንቃቄ የምታደርገው ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከቤተ እግዚአብሔር እንዳይርቁ ከዛም አልፎ ተበዳይም ሆነ በዳይ ፣በዕዳ የሚጠየቅም ሆነ የሚጠይቅ ሁለቱም በአንድነት ቅዱስ ቃሉን ሲሰሙ ዋሽቶ የሰው ዕዳ ያልከፈለውም ተጸጽቶ ይክሳል ወራት ብሶበት ቀን ጥሎት መክፈል ላልቻለውም ምህረት ይቅርታ እንዲያገኝ ቅዱስ ቃሉ ጸሎቱ ምክንያት ይሆነዋል ። በዚህም የተነሳ ሁለቱም ወገኖች በክፉ ከመፈላለግ ይልቅ የይቅርታ የምህረት ሰዎች ይሆናሉ። እንግዲህ በዚህች በኵረ በዓላት በምትሆን በቅድስት በዕለተ ሰንበት የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይባረካል ይቀደሳል በዚህ ታሳቢነት ዕለቱም ዕለተ ቅድስና መሆኑን ለማጠየቅ ቅድስት ተብሏል ።
ቅድስና የተፈቀደልን ብቻ ሳይሆን የታዘዝነውም ጭምር ነው “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” ዘሌ.19፥2 በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ቅድስና እንደ ፈቃድም እንደ ትእዛዝም ሆኖ ተሰጥቶናል እግዚአብሔር ያልፈቀደውን ነገር አድርጉ ሁኑ ብሎ አያዝም ። የቅድስና ሕይወት መሰረቱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ሆኖ ሳለ ለመቀደስ የእኛ መሻት መፈለግ ዝንባሌም ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው እንዲህ ሲል የጻፈልን “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥” ዕብ 12፥14 ምንም እንኳን ቅድስና የተፈቀደና የታዘዘ ቢሆንም የውዴታ እና የነጻ ፈቃድ ውጤት እንጂ የምንገደድበት አይደለም። እግዚአብሔር ፍቅሩ ገብቶን ወደን እና ፈቅደን በፈቃዱ እና በትእዛዙ ስንመራ ያስደስተዋል እንጂ ተገደን ፈርተን ተንቀጥቅጠን እንድንገዛለት አይወድም ።
ወደ ቅደመ ነገራችን ስንመለስ ዕለተ ሰንበትም ቅድስት መባሏ ከላይ ያብራራነውን መሰረታዊ ሃሳብ በተከተለ መልኩ ነው። ዕለቲቱ ቅድስት መባሏ ዋና ዓላማ በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል ለቅድስና ሕይወት ምልክት ማስታወሻ እንድትሆን ነው። በባህሪው ቅዱስ የሆነ አምላክ ዓለምን የማዳን ስራውን የጀመረበትን ጽንሰቱን እንዲሁም የማዳን ስራውም አጠናቆ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ዘላለማዊ ሕይወትን ያበሰረበትን ትንሳኤውን የምናስብበት በመሆኑ የዕለቱ ቅድስና የፈጣሪን ቅዱስ ተግባር የምናደንቅበት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ ተለይተን የዋለልን ሁለታ ከፍ ከፍ እያድረግን እርሱን የምናመሰግንበት ዕለት ነው። ይህም እኛን ወደ በለጠ የቅድስና ሕይወት የሚያሸጋግረን ከመሆኑም በላይ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር በየጊዜው እንድናስብና በፍቅሩም እንድንኖር ያግዘናል።
ከጾሙ በረከት ያሳትፈን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።