መንፈሳዊ ሕይወትና ስደት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስደትን በመንፈሳዊ ሕይወት ከኖሩ ሰዎች መካከል ወጣቱ ዮሴፍ ታላቅ ምሳሌ ነው። ታሪኩን ከዘፍ 37፡1_ ጀምሮ እንደምናገኘው ዮሴፍን ወንድሞቹ በግፍ፣ በተንኮልና በምቀኝነት ወደ ግብፅ በባርነት አሳልፈው ሸጡት። ዮሴፍ የስደትን መከራና ውጣውረድ የሚቋቋምበት የእድሜ ክልል ውስጥ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍፁም እምነት ያመልክ ስለነበር በስደት ዓለም የሚያመልከው አምላክ እግዚአብሔር ሞገስና ኃይል ሆነው።
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ዓለቴ፣ አምባዬ፣ መድኃኒቴ፣ አምላኬ፣ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፣ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው” መዝ 17፡2 እንዳለ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ኃይል፣ መጠጊያ፣ ረዳትና ጠባቂ ሆነው። እግዚአብሔርን በፍፁም እምነት ካመለክነው በምንሄድበት ሁሉ እንደ ዮሴፍ ጥላችን፣ ከለላችን፤ ጋሻችን ፣ መከታችን፤ ረዳታችንና ጠባቂያችን ነው። ዮሴፍ የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔርን አምኖ ስደትን በጸጋ ተቀብሎ፣ የገጠመውን ፈተና ሁሉ ድል እየነሳ በነበረበት በስደት ሕይወት ውስጥ እያለ ለሥራው ታማኝና ታታሪ ስለነበር ጲጥፋራ በሃብት በንብረቱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። በዚያ ኃላፊነት ተሰጦት በጲጥፋራ ቤት እያለ ታላቅ ፈተና መጣበት፡፡ አዎ ዓለማዊ ስልጣንና ኃላፊነት ካላወቅንበት ፈተናና መከራ ይዞ ነው የሚመጣው፤ ለዮሴፍም የገጠመው ይህ ነበር። ማለትም የጲጥፋራ ሚስት ማንም የሌለበትን ስዓት ጠብቃ ለዝሙት ጋበዘችው። ዮሴፍም እኛ ብቻችንን ሆነን ማንም ሰው ባያይም የማመልከው አምላክ እግዚአብሔር ያያልና “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአት እሰራለሁ?” ዘፍ 39፡9 በማለት በስደት ዓለም ሞገስና ኃይል ለሆነው ለእግዚአብሔርና በቤቱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ለሾመው ለጲጥፋራ ታማኝነቱን አሳይቶ የዲያቢሎስን ክፉ ሥራ አከሸፈበት።
እኛም ዛሬ ለእግዚአብሔርና ለምናገኘው ማንኛውም ኃላፊነት ታማኝ ሆነን ከኃጢአት ርቀን በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር ከተጋን በስደት ዓለም እንደ ዮሴፍ ፈተናውን ሁሉ በድል እንወጣለን። በመንፈሳዊ ሕይወት የሚኖር ሰው እግዚአብሔርን ያስቀድማል፤ ኃጢአትን ለመስራት ምክንያት አይፈጥርም ይልቁንም እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን እሰራለው ብሎ ለሥራው፣ ለተሰጠው ኃላፊነት፣ ለትዳሩና ለሁሉም ነገር ታማኝ ይሆናል። በዚህም ምክንያት በእግዚአብሔርም በሰው ዘንድም ሞገስን ያገኛል። ዮሴፍ በሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን ያስቀድም ስለነበር በእስር ቤት በነበረበት ጊዜም እግዚአብሔር ሞገስ ሆኖት ለእስረኞች ኃላፊ እንዲሆን አደረገው። “አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም” መዝ 24፡3 በማለት ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን ተስፋ ያደረገ ሰው በማንኛውም ቦታ ቢሄድ፤ በማንኛውም ችግር ውስጥ ቢገባ ከቶ አንዳች ነገር እንደማይሆን ይነግረናል። ለዚህም ነው ዮሴፍ በስደት በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ሞገስን፣ አስትዋይነትንና ጥበብን አድሎት በስደት ለሚኖርባት ግብፅም እንዲሁም ለስደት የዳረጉትን ወንድሞቹን እንኳ ሳይቀር ለበረከት ምክንያት የሆናቸው። እኛም እንደ ቅዱስ ዮሴፍ በምንሄድበት ሁሉ እግዚአብሔርንና ትዕዛዙን አክብረን፣ በእምነታችን ጸንተን በመንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከሆነ በስደት ለምንኖርበት አገርም፣ ለአገራችንና ለቤተሰቦቻችን የበረከት ምክንያት ልንሆን ስለምንችል መትጋት ያስፈልጋል።
እኛም ዛሬ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያቆብ፣ የዮሴፍ፣ የዳንኤል የሰለስቱ ደቂቅን የእምነታቸውን ጽናት እየተመለከትን እነርሱ የሠሩትን ሥራ መስራት ይገባናል። በስደት ዓለም የምንኖር ሰዎች ዳንኤልንና ሰለስቱ ደቂቅን ማስታወስ ለእምነታችን ጽናት ከበቂ በላይ ነው። ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ/ አናንያ አዛርያ ሚሳኤል/ በምርኮ ከትውልድ ቦታቸው ወደ ባቢሎን ተጋዙ። ታሪኩን በዳን 1፡1_ ጀምረን እንደምናገኘው እነርሱ ግን በምርኮ በነበሩበት ስዓትም እግዚአብሔርን ከማምለክ ወደ ኋላ አላሉም። ይልቁንም በጾምና በጸሎት ይተጉ ነበር እንጂ። ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ተግተው ይለምኑት ስለነበር ሞገስና ጥበብን፤ በተለያየ አውራጃ ላይ ሹመትንም አደላቸው። ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና በስደት እግዚአብሔርን ስላመለኩ ሰለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት፣ ዳንኤልን ወደ አናብስት ጉርጓድ እንዲጣሉ አደረገ ተጣሉም። “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” ማቴ 17፡20 ብሎ ለሐዋርያት እንደተናገረው ዳንኤልና ሰለስቱ ደቂቅ ፍጹዕም እምነት ስለነበራቸው እሳቱ ውኃ፤ አናብስቱ እንደ መልካም ጓደኛ ሆኑላቸው። እምነታቸው ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን ወደ አናብስት ጉርጓድና ወደ እሳቱ እንዲመጡ አደረገ። ሰለስቱ ደቂቅ ወደ እሳት ሊጣሉ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀራቸው እምነታቸውን የገለጹበት ቃል አስደናቂ ነው፤ “የምናመልከው አምላክ ከሚነደው እሳት እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፣ ባያድነንም እንኳ አንተ ላቆምከው ለወርቅ ምስል ለጣኦት አንሰግድም” ዳን 3፡17 እንዴት አይነት እምነት ቢኖራቸው ነው? ዛሬ ብዙዎቻችን ምድራዊ ኑራችን አልተሟላም ብለን እግዚአብሔርን ስናማርር እንገኛለን። እነርሱ ግን ከእሳት እቶን ባያድነንም፣ በዚህ ምድር በሥጋ እንድንቆይ ፍቃዱ ባይሆንም ለጣኦት አንሰግድም አሉ። ስለዚህ እኛም እንደ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ወደ ስደት የመጣንበት ዓላማ ቢሳካም ባይሳካም፣ የተመኘነውን ማግኘት ብንችልም ባንችልም፣ የስደት ሕይወት ከባድ ቢሆንም ባይሆንም፣ ብዙ ችግሮች ቢገጥሙንም እምነታችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን አንለውጥም አንቀይርም አንተውም ማለት ያስፈልጋል። እንዲህ ብለን በእምነት ከጸናን ደግሞ አምላካችን ይረዳናል፤በቅዱሳን ምልጃና ጸሎት ከፈተና ሁሉ ያወጣናል።
በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖር ከእኛ የሚጠበቁ በርካታ ነገሮች አሉ። ከብዙ ጥቂቶቹን ለማየት እንሞክራለን።
1.ቃለ እግዚአብሔርን መማር፦ መንፈሳዊ ሕይወት ቀስ በቀስ የሚያድግ ስለሆነ በአንዴ ተነስቶ መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም። ያለንን መንፈሳዊ ጸጋም እስከመጨረሻው አጽንተን የምንጓዝ ምግበ ነፍስ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ስንሰማና ስንማር ነው። ሰው መማሩን፣ መጠየቁን፣ የአባቶችን ምክር ካቆመ ለተለያዩ ፈተናዎች እየተጋለጠ መሄዱን ያሳያል። “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ማቴ 4፡4 ተብሎ እንደተጻፈ መማር፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብ፣ አባቶችን መጠየቅ በእግዚአብሔር እንድንታመን፤ በቅዱሳን አማላጅነና ተራዳይነት አምነን እንድንጠቀም፤ የቤተክርስቲያናችንን ታሪክ፣ ሕግ፣ ስርዓት፣ ዶግማና ቅኖና እንድናውቅ ያደርጋል።
ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” 2ጢሞ 3፡16 እንዳለ ቅዱሳት መጽሕፍት ለመንፈሳዊ ሕይወት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። በእርግጥ ቅዱሳት መጽሕፍትን በቀላሉ ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዛሬ የምንኖርባት ዓለም በቴክኖሎጂ ሰውን ከሰው ማገናኘት፣ የምንፈልገውንም ነገር በፍጥነት ለማገናኘት የምታስችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ስለዚህ ይህን የቴክኖሎጂ የመረጃ መረብ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመጠቀም ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን ምግብ መመገብ እንችላለን። እዚህ ላይ ግን በጥንቃቄ ማወቅ የሚገባን ነገር ትክክለኛው የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚተላለፍበት ድረ ገጽ የቱ ነው የሚለው መሰመር አለበት። ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ የሚለው የወንጌል ቃል ይፈጸም ዘንድ በርካቶች በቤተክርስቲያናችን ስም የጡመራ ድረ ገጽ ከፍተው ቅዱሳንን ሲሳደቡ፣ የብሉይና የሐዲስን ሕግ አሟልታና አስማምታ የያዘችውን ቤተክርስትያን ሲተቹ፣ ከዚህም አልፎ እመ አምላክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን መግለጽ በሚከብድ መልኩ ሲጽፉና ሲናገሩ እናያለን እንሰማለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” 2ጢሞ 4፡5 ብሎ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንዳስጠነቀቀው እኛም ከእነዚህ ርቀን የራሳችን የሆኑትን ድረ ገጽ ለይተን በመጠቀም መንፈሳዊ ሕይወታችንን ማሳደግ ይኖርብናል።
2.ትዕዛዛተ እግዚአብሔርን መጠበቅ፦ አባቶቻችን ሃይማኖት ካለስርዓት ዋጋ የለዉም፤ ካለምግባር መንግሥተ ሰማያት ሊያስገባን አይችልም በማለት የእግዚአብሔርን ትዕዛዝና ሕግ መፈፀምና መጠበቅ እንዳለብን በአጽንኦት ይነግሩናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሕግና ትዕዛዝ ሁሉን አሟልቶ የያዘ ነውና። በትዕዛዛቱ ውስጥ ስለእግዚአብሔር ማንነትና ምንነት፣ መልካም ምግባር መፈፀም እንዳለብን እና የሃይማኖታችንን ስርዓትና ሕግ እንረዳበታለን። ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመኖርና መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ትዕዛዙን መፈፀምና መጠበቅ ያስፈልጋል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “የሚወደኝ ቢኖር ትዕዛዜን ይጠብቅ” ዮሐ 14፡15 መቼም እግዚአብሔርን የማይወድ ማንም የለም እርሱን የምንወድ ከሆነ ደግሞ ትዕዛዙን መጠበቅ ነው። እግዚአብሔርም በእኔ የምታምኑ ከሆነ፣ ከወደዳችሁኝ፣ ከአከበራችሁኝ ሕግና ትዕዛዜን ጠብቁ ፈፅሙ በማለት ትዕዛዙን መጠበቅ እርሱን መውደዳችን የምንገልፅበት መንገድ መሆኑን ይነግረናል።“ትዕዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችሁ የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው” ዮሐ 14፡21 በማለት 6ቱ ቃላተ ወንጌልን ማቴ 5፡21 እና 10ቱ ትዕዛዛተ ኦሪት ዘፀ 20፡1 – 17 ከጾምና ከጸሎት ጋር መፈጸም እንዳለብን ያስረዳናል።