መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)

በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ

መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም

የነፍሳችንን ማሠሪያ እንዲፈታና ዓለሙን ከተያዘ የኃጢአት በሽታ እንዲያድን ለቤዛነት፤ እንዲሁም የመልካምና የበጎ ምግባራት ሁሉ አብነት ሆኖ በሥራና በቃል እንዲያስተምር ወዳለንባት ምድር በሥጋ ቅድስት ድንግል ማርያም ወረደ ተወለደ:: ቤተክርስቲያናችን በአራተኛው ቢይ ጾም ሳምንት እግዚአ ለሰንበት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሳይዳየፈጸመውን ተአምራት መጻጒዕ ብላ ሰይማ ስበዋለች። በዕለቱም በዮሐንስ ወንጌል አምስተኛው ምዕራፍ የተቀመጠው ታሪክ በልዩ ልዩ ኅብረ ምሥጢር ተገናዝቦ በሊቃውንቱ ይነገራል።

መጻጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅባት የኖረባት ስፍራንቤተ ሳይዳትባላለች በቅዱስ መጽሐፍ የሥፍራዎችን ስያሜ ስንመረምር በይሁዳና በገሊላ ለሚገኙ ሁለት የተለያዩ ግዛቶች በተመሳሳይ አገባብቤተ ሳይዳየሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው እናገኛለን። በሁለቱ አውራጃዎች (ይሁዳና ገሊላ) ሥርቤተ ሳይዳበሚል የተጠቀሱት ሥፍራዎች በትርጉም ፊደላቱ ያለአገባብ መሰደር ከወለዱት የሞክሼነት ስህተት (Metathetical Corruption) የተገኘ ክፍተት እንጂ ቦታዎቹስ በጥንታዊቷ የእስራኤል ግዛት ከመገኘታቸው ውጪ ምንም የሚያገናኛቸው መልክአ ምድራዊ ኩነት የለምጲላጦስ ጰንጤናዊ መልአከ ይሁዳ ወሄሮድስ ንጉሠ ገሊላ” (ሉቃ· ፫፥፩) እንዲል የግዛቶቹ አገረ ገዢዎችም እንዲሁ ለየቅል ነበሩ። አገባቡን አካቶ ለመረዳት እንዲያመች የሁለቱንም መካናት ከተማና መንደር ለይቶ ማወቁ ተገቢ ነው።

በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ገቢረ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች ፦ ቤተሳይዳ(Bethesda) ፣ ቢታኒያ ፣ ቤተልሔም ፣ ቤተፋጌ ፣ ኢያሪኮ ፣ ጌቴሰማኒ ፣ ሊቶስጥሮስ(ገታ) ፣ ኤማሁስ፣ ቀራንዮ(ጎልጎታ) ፣ ኢየሩሳሌም እና የደብረዘይት ተራራ የሚጠቀሱ ሲሆን፤

በገሊላ አውራጃ ደግሞ ፦ ቤተሳይዳ(Bethsaida) ፣ ሄኖን ፣ ቃና፣ ቅፍርናሆም፣ ኮራዚ፣ ጌንሳሬጥ፣ ደብረታቦር፣ ናይን እና የገሊላ ባህር ተገልጸው እናገኛልን::

እነዚህኑ “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳና “ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ አካባቢያዊ መገኛ ለይተው የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል) ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት” (ዮሐ ·፭፥፪) ብሎ የገለጠበትንና በገሊላ ስለምትገኘዋ ደግሞ “ወሖሩ እሙንቱሂ ኀበ ፊልጶስ ዘቤተ ሳይዳ ዘገሊላ” (ዮሐ ፲፪፥፳፩) የሚለው ማየት ይቻላል::

በሌላ መልኩ አንዳንዶች ደግሞ በሁለቱም ሥፍራዎች ክርስቶስ አምላካችን ለፈውስ ሥራ ያገኛቸውን ሰዎች አይተው ተመሳሳይ ቦታ ሲመስላቸው ይታያል ይህም “መጻጉዕ” እና “ዕውር” የነበሩትን ማዳኑ ነው:: ይኸውም “ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ) ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ ·፭፥፪) የተባለውና “ወበጽሑ ቤተ ሳይዳ ወአምጽኡ ኀቤሁ ዕውረ ወአስተብቁዕዎ ይግስሶ … ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።” (ማር· ፰፥፳፪) የሚለው ነው::

“ቤተ ሳይዳ” ዘገሊላ (Bethsaida) በትርጉም “የማጥመጃ ቤት” የሚል ፍቺ ያለው በተለይ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾችና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ናት ” ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።” (ዮሐ·፩፡፵፭) እንዲል።

“ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳ (Bethesda or Bethchasday) የመጠመቂያ ሥፍራ ስትሆን በግሪኩ ቤተ ዛታ ( Βηθζαθά) ወይም ቅልንብትራ (κολυμβήθρα) እንዲሁም በእብራይስጡና በአረማይኩ “ቤተ`ስዳ” (Beth hesda ( בית חסד /חסדא )) በማለት “ከማጥመጃ ቤት” ለይቶ “ቤተ ሣሕል / የምሕረት ቤት” የሚል ትርጉም ያለው መጠመቂያና መላለሻ መንገድ መሆንዋን ያመለክተናል። የግእዙ መጽሐፍ ቅዱሳችንም የቦታውን ስያሜ ከእብራይስጡ “የአንድዮሽ ትርጉም” ስያሜ (ቤተ ሳይዳ) ጋር በግሪኩ ያለውንም መጠሪያ ጭምር አካቶ ቅልንብትራ ( κολυμβήθρα / kolumbethra) ሲል እናገኘዋለን::

ቤተ ሳይዳ ዘይሁዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከማየ ጥምቀቱ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት በአምስተኛው የዮሐንስ ወንጌል ተጽ ያለ የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት። “እስመ ኦሪት መንፈቀ ፍጻሜ ወኅዳጠ መክፈልት” እንዲላት መልአከ እግዚአብሔር ለቀድሶተ ማይ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት ።

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የድኅነት ተስፈኛ ሆኖ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ “መፈውስ ወማሕየዊ” ጌታችን ቀርቦ አዎን እንዲለው እያወቀ ያንን በሽተኛ “ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?” አለው። ብወዳችሁ አላዋቂ የሆነ የእናንተን ሥጋ ተዋሕጄ መጣሁላችሁ ሲለን (“አኮ ኢያእሚሮ ኅቡአተ አላ ከመ የሀብ መካነ ለጥንተ ትስብዕቱ ዘኢየአምር ኅቡአተ”) እንዲል:: የሚገርመው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፪ ላይ “የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው ዓይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። ” ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? “(መክ ፮፥፲፪) እንዲል የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ? መጻጒዕ ግን ኋላ የሚክድ ነውና “በሰንበት ላይ ያመጸ ፣ ራሱን ከአብ የሚያስተካክል ፣ ቤተመቅደሱን አፍርሱት ያለ መች አድነኝ ብየው ሳልፈቅድለት ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ ነውኮ” ብሎ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። “አልብየ ሰብእ” ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ሁከተ ማይ ሳያቆየው “ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር … ተንስና አልጋህን አንስተህ ሂድ” አለው ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ።

ይህች “ቤተ ሳይዳ” ዘይሁዳ ምሣሌቷ ብዙ ኅብር ያለው ነው። ለአብነትም ያህል ምሳሌ፦

፩·ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት የአምስቱ መፃሕፍተ ሙሴ በነዚያ ታጥረው ለመኖራቸው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን እነሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው።

፪·በሌላ አገባብ

በዚያ ውኀውን ለማወክ የወረደው መልአክ = ቀሳውስት(ካህናት) “ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት” የመውረዳቸው ምሳሌ ነው።

የመጠመቂያ ውኀው = የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን

በቤተ ሳይዳ ያለው አምስቱ እርከን(መመላለሻ) =የአምስቱ አእማደ ምስጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና።

አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምዕመናን ከነ ፈተናቸው የተመሳጠረበት ምሳሌ ነው (አእሩግ=በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት=በዝሙት፣ አንስት=በትውዝፍት በምንዝር ጌጥ፣ ካህናት=በትእቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት=በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም አጽንኦ በአት እየፈቱ በአንሰሐስሖ ዘበከንቱ ይፈትናቸዋል) ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

፫·ለአዲስ ኪዳን ድኅነተ ነፍስ ምስጢራዊ ምሳሌ አገባብም አለው፤

ቤተሳይዳ የበጎች በር በመባልዋ እና በኦሪቱ በጎች ወደ ቤተ መቅደስ ወጥተው ለመስዋዕት ከመቅረባቸው አስቀድሞ የሚታጠቡበት ውኀ ያለበት በመሆኑ ለአዲስ ኪዳንም የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት የሚገኝባትን ወደ አማናዊ መስዋዕት ቅዱስ ቁርባን የምታደርስ የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ

አምስቱን መመላለሻ የምታደርስ ደግሞ ወደ ፍፃሜ ሕግ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር አልፎም ፍጽምት ወደሆነች ወደ ሕግጋተ ወንጌልም የምታደርስ የአምስቱ ብኄረ ኦሪት መፃሕፍተ ሙሴ ምሳሌ ያደርጋቸዋል።

ለሁከተ ማይ የወረደው መልአክ የመድኃኒታችን የክርስቶስ ምሳሌ ነው

ከአንድ ብቻ በቀር ሕሙም በአንድ ዕለት አለመዳኑ በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር አምነው ያሉ ምዕመናንና ምዕመናት ብቻ ድኅነተ ነፍስ እዳላቸው ያሳያል።

የውኀው መናወጽ የሰቃልያነ ክርስቶስ “ሁከተ አይሁድ” ምሳሌ ጥንቱን “ስቅሎ ስቅሎ ” የሚለው ያ ቁጣ የዕለተ ዓርብ መድኃኒት መገኛ ነውና።

እስኪ ደግሞ በማጠቃለያው ወደ መጻጒዕ ታሪክ እንመለስና ጥቂት ፍሬ ነገር ለሕይወታችን እንስማ።

ቀድሞ በ`ቤተ ሳይዳ` እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ የፍርድ ገታ ቆሞ በረሳ ጊዜ ” ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?” እንኳ እንዳይል ያለ ተረፈ ደዌ አንስቶት ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ግን ታዲያ ይህ ምስኪን መጻጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ ማን እንደሆነ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም “ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …የዳነው ያዳነውን አላወቀውም” ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይለዋል። ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ለምሥጋና ያይደለ ለክስ ነበር ስሙን የፈለገው። “ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ።” ተብሎ ለናቡከደነፆር በነቢዩ እንደተነገረ ያለ ነው (ኤር.፶፩፥፴፬ ) በአገራችንም ካለው ብሂለ አበው “ታሞ የተነሳ ፈጣሪውን ረሳ” የሚለው እንደነዚህ ያሉትን በሚገባ ለመግለጽ የተነገረ ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴን በዘዳግም ፲ ቁጥር ፳፩ ላይ እንዲህ ይላል “ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው።” ነገር ግን ይህን ሁሉ ያደረገውን አምላክ ብዙዎች የነበሩ “ህዝበ እስራኤል” ረስተው አሳዝነውት በምድረበዳ በከንቱ ወድቀው ቀሩ ….. ዛሬም ከደዌው :ከማጣቱ :ከችግሩ: ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ ዳግመኛ ለመታረቅ እንደ መጻጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው ” ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?” (ኤር. ፳፫፥፲፰) ማንም። ጌታችን ባስተማረው ማሕየዊ ቃሉ ላይ እንኳ ሳይቀር ያመጹትን አይሁድ እስኪ ተመልከቱ ” ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።” ሉቃ ፲፮፥፲፬ እኛንም ቢሆን ከአዳም እስራት ነፃ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን በቃሉ የምናፌዝ ሁላችንን ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል “እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ ” እንዲል ( ኢሳ· ፳፰፥፳፪ )።

በፍፃሜ ሕይወቱ በአውደ ምኩናን የሀሰት ክስ የቀረበበትን ይህን የእውነትና የሕይወት ጌታ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ። “ዘተሰብሐ ውስተ ገጸ ሙሴ በትስብእቱ ተጸፍአ ገጾ ወተቀስፈ ዘባኖ በእንቲአነ ከመ ይፈጽም ስምዓ ነቢይ ዘይብል መጠውኩ ዘባንየ ለመቅሰፍት ወመላትሕየ ለጽፍአት… በገጹ ነፀብራቅ የሙሴን ፊት ያበራ እርሱ በነቢዩ ጀርባዬን ለግርፋት ጉንጮቼንም ለጽፍአት ሰጠሁ ተብሎ የተነገረውን ለመፈጸም ለእኛ ሲል ፊቱን በጥፊ ተመታ ጀርባውንም ተገረፈ “እንዲል (ሰይፈ ሥላሴ) አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ “ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ … ከዚህ የጠናው “ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ” እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል” (ቁ ፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች አንዱ ሊቅ ይህን አልሰማ ባይ መጻጒዕ እና ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው ይህን ተናገረ

” ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ

ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ”

(መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)

አብረው አያሌ ዓመታት የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ተነፋፍቀው መለያየቱ እምቢኝ እንደሚላቸውና እንደሚታረቁ ሁሉ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተብሎ ሳለ ጌታውን ጸፍቶ መጻጒዕም ዳግመኛ ወደ ፴፰ ዓመት “የአልጋ ወዳጁ” ደዌ መመለሱን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። እንግዲህ እኛም በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መጻጒዕን “ተነሳ” እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት መዘንጋት፣ ኃጢአት በንስ እንዲያነሳንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። አሜን!