ዕውቀት እንዳይሞት
ቤተ ክርስቲያን ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ነበረች። ዓለማት ከተፈጠሩ በኋላ በዓለመ መላእክት፣ በዓለመ መሬት በሕገ ልቡና እና በሕገ ኦሪት እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያትና ካህናቱ አማካኝነት ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ስታገናኝ ኖራለች። በዘመነ ሐዲስ ደግሞ በደመ ክርስቶስ ተዋጅታ ሕገ ወንጌልን ስትናኝ እና አምልኮተ እግዚአብሔርን ስታስፋፋ ኖራለች። በነዚህ አዝማናት ሁሉ ስለ እርሷ ሳይፈሩና ሳያፍሩ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ እግራቸውን ለሰንሰለት የሰጡላት፣ በብዙ መከራዎች የተጋደሉላትን አበው፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታትን እና በእነርሱ መንገድ የተጓዙ ብዙ ሊቃውንትን አፍርታለች (ዕብ ፲፩)።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕገ አበውን፣ ሕገ ኦሪትንና ሕገ ወንጌልን አስተባብራ በመያዝ የጥበብ ምንጭ፣ የሥርዓት መፍለቂያ፣ የዕውቀት ባሕር ሆና ሁሉ የተሟላላት ስንዱ እመቤት ናት። በማኅበራዊ አገልግሎቷ ደግሞ የድኩማን መጠጊያ፣ ያዘኑና የተከፉ መጽናኛ፣ የማንነትም አሻራ ነች። ለዚህም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶች ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት የተንኮልና የክህደት ቋጠሮ ይዘው የመጡ መስሐቲያን (አሳሳቾች) አፍረው የተመለሱት ከአብነት ት/ቤቶቹ በወጡ መምህራን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለሀገር መሪ ለሕዝብ አስተማሪ በመሆን ሕዝብን ያገለገሉ ደጋጎች ከእነዚህ የአብነት ት/ቤቶች በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ናቸው።
ሌላው ልንገነዘበው የሚገባ ቁም ነገር ቢኖር ገና ያልደረስንባቸው ብዙ እምቅ መንፈሳዊ ሃብቶች ያሉን መሆናቸዉ ነው። ለምሳሌም፦ በዜማዉ የአጫብር፣ የቆሜ፤ በቅኔው የዋድላ፣ የጎንጅ፤ በመጻሕፍት ትርጓሜ የላይ ቤት፣ የታች ቤት እየተባሉ የሚሰጡ ትምህርቶች/ይትበሃሎች አሉን። እነዚህ መሠረታቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት ሆነው አካባቢያዊ መልክ ያላቸውን እምቅ እሴቶች ልንፈለፍላቸውና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ናቸው።
የቤተ ክርስቲያኒቱ አብነት ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት አሁን በዓለም እውቅ ከሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ከሆነው ከሐርቨርድ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚያመሳስለው ነገር ያለው ሲሆን ይህም አግራሞትን የሚፈጥርና የሥረዓተ ትምህርቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። ሆኖም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥረዓተ ትምህርት በዘመን ቀዳማዊ ሆኖ መገኘቱ እጅግ የሚያኮራ ነው።
የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሳይከለስና ሳይበረዝ ተጠብቆ እስከአሁን እንዲዘልቅ ያደረጉት ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የአብነት ት/ቤቶች ናቸው። ስለሆነም እነዚህ የትምህርት ማዕከላት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዳይዘጉ፤ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው እንዳይሰደዱ፣ ወንበር እንዳይታጠፍ በጋር እና በተናጠል ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ሆኖም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ የእሳት ማጥፋቱ ሥራ በልማት ቢታገዝና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ቢቻል መልካም መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው።
ማኅበረ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሲመሠረት ከሚመለከተዉ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምሪያ ጋር በመሆን ምእመናንን በማስተባበር ከፍ ብሎ የጠቀስነውን ዓቢይ ጉዳይ እንደ አንድ የአገልግሎት ዘርፍ አድርጎ እንዲሠራ ነው። ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት በንዋያተ ቅድሳት እጦትና በአገልጋይ ካህናት እጥረት እንዳይፈቱ፣ የአብነት ትምህርት መምህራንና ተማሪዎቻቸው የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ እጦትን ጨምሮ በተጋፈጡባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት ወንበሩ አጥፈው እንዳይበተኑ ምእመናንን በማስተባበር ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በርካታ ተማሪዎች ያለ ችግር የጀመሩትን ትምህርት በየወንበሮቻቸው እንዲቀጽሉና የዕውቀት ጥማታቸውን ከማርካት አልፈው የነገይቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢነታቸዉን እንዲያረጋግጡ ለማድረግ ተችሏል።
ይህ የተቀደሰና ለነገ የማይባል የድጋፍ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቤተ ክርስቲያን ያሉ የአገልግሎት አካላት እንዳለፉት ጊዚያት ሁሉ በበለጠ መትጋት፣ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ሁሉ ማድረግና ምእመናንንም በስፋት ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል። በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማት አገልግሎት በሚያቀርባቸዉ የአገልግሎት ዘርፎችና የድጋፍ ጥሪዎች ሁሉ አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ሲሳተፉ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እስካሁን ያደረጉት ድጋፍ ያፈራውን ፍሬ እየተመለከቱ የበለጠ መትጋት ይጠበቅባቸዋል። ቅዱስ እግዚአብሔር በቸርነቱ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ጸጋ እንዲጠብቅልን እኛንም በቤቱ አገልግሎት እንዲያበረታን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን ሁሉ ረድኤታቸው በረከታቸዉ አይለየን፤ አሜን።