የደቡብ፣ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ

ጳጉሜን 02 ቀን 2005 ዓ.ም. 

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ፣ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት ከነሐሴ 24 – 25፣ 2005 ዓ.ም በጀርመን ሀገር በሚገኘው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ እንጦንስ ገዳም ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ፡፡ በዕለቱም ብፁዕ አቡነ ሙሴ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖደስ አባል፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት እና የመንፈሳዊያት ማኅበራት ተወካዮች በአባልነት ተገኝተዋል፡፡ ጉባኤው በብፁዕነታቸው ቡራኬ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል ሀገረ ስብከቱን ማዋቀር፣ የመንበረ ጵጵስና ጽ/ቤት መቀመጫ መወሰን እና በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ወቅታዊ ችግሮች ተወያይቶ መወሰን የሚሉ ሦስት አጀንዳዎችን መርጦ በማጽደቅ ውይይቱን ጀምሯል፡፡

His Grace Abune Mussie

ብፁዕ አቡነ ሙሴ

የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት በሥሩ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሥራቸውንና አገልግሎታቸውን በአንድነትና በመተባበር እንዲሠሩ የሚያስተሳስራቸው መዋቅር ባለመዘርጋቱና ሀ/ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ስላልነበረው የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመፈጸምና ለማስፈጸም ሳይችል መቆየቱን በመጥቀስ ሀ/ስብከቱ ሥራውን በተገቢ ሁኔታ መሥራት እንዲችል ሁሉን ያማከለ መዋቅር መዘርጋትና ሥራውንም በየክፍሉ የሚያስፈጽሙ ክፍሎችን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ጉባኤው  በመዋቅሩ መቋቋም ላይ የጋራ ስምምነት በመያዝ መንበረ ጵጵስናው በጀርመን ሀገር እንዲሆን ወስኗል፡፡ የሀገረ ስብከቱን ሥራ እንደሚጠበቀው ማከናወን ይቻል ዘንድ ሁሉም አጥቢያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በመስማማት ዓመታዊ የበጀት ወጪ በማስላት በአጥቢያዎች ላይ የገንዘብ ምደባ ተደርጓል፡፡ የሀገረ ስብከቱን ሥራዎች በአግባቡ ለማከናወን እንዲያግዝም በብፁዕነታቸው የሚመራ ስድስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ በጉባኤው ተመርጧል፡፡ የሥራ አሥፈጻሚው የአገልግሎት ዘመንም ሁለት ዓመት እንዲሆን ተወስኗል፡፡

Participants

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል 

Participants2

 የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል 

በሦስተኛ አጀንዳንት ተይዞ የነበረው በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ዙሪያ የሚታዩ ወቅታዊ ችግሮችን በተመለከተ ሦስት ጉዳዮችን አንስቶ ተወያይቷል፡፡ እነዚህም “ገለልተኛ” ብለው ራሳቸውን ስለሚጠሩ አጥቢያዎች፣ ስለ ቀድሞው የሙኒክ ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ እና በሃይማኖት ህጸጽ ምክንያት በምእመናን ክስ ቀርቦባቸው ውሳኔ እየተጠባበቁ ስላሉት የቪዝባደን ቅ/ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ ቄስ ገዳሙ ደምሳሽ ሲሆን ብፁዕ ሊቀጳጳሱ በካህናት ጉባኤ ጉዳዩን በማጣራት ውሳኔ እንዲሰጡበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡ በተለይም በትምህርታቸው ምክንያት በምእመናን ክስ ስለቀረበባቸው ካህን ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኝ ጉባኤው በአጽንኦት አሳስቧል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ሊቀጳጳሱ ለጉባዔው መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ በማመስገን ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል፡፡  

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር