ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፤ (መዝ 64፥ 11)

/  ውብዓለም  ደስታ 

ጳጉሜን 04 ቀን 2005 ዓ.ም. 

ዘመን የሚለወጥበት የመስከረም ወር ዘር ዘርተው ተክል ተክለው የሚኖሩ ሐረስተ ምድር በክረምት የዘሩትን ዘር አሽቶ አፍርቶ ምድርም በልምላሜ ተጊጣ እንስሳትም ለምለሙን ሣር ግጠው ጽሩውን ውኃ ተጎንጭተው ጠግበው አምረው የሚታዩበት የልምላሜ የፍሬ ወር ነው። “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ። መዝ (64 (65)፥ 9-13)

ይህ ከላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል የአምላካችንን ድንቅ መጋቢነት የሚገልጽ ሲሆን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ዓመታትን በቸርነቱ እየለወጠ፤ የበረከት እጁን ሳያጥፍ እየመገበ፤ የሰዎችን ማንነት ሳይለይ ለክፉም ለደጉም፤ ለኃጥኡም ለጻድቁም፣ ለድሀውም ለሀብታሙም፣ ለአሕዛብም ለሕዝብም የምሕረት ዝናቡን እያወረደ ፍጥረትን በሙሉ የሚያረካ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያስረግጥልናል። እንዲሁም ሥነ-ፍጥረትን ብንመረምር የበጋና የክረምት መፈራረቅ፤ ተራሮች በዝናብ መርካታቸው፤  ከድርቀት (ከፀሐይ) ወራት በኋላ የሚመጡት የበረከት (የዝናብ) ጊዜያት እንዴት ባለ በሚያስደንቅ ሁኔታ የምድሪቱን ገጽታ እንደሚቀይር እንገነዘባለን።

በመሆኑም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ዓመታትን በቸርነቱ ለሚያቀዳጅ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የአዲሱን ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዐውደ ዓመት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› በሚል ስያሜ ስታከብረው ኖራለች ትኖራለችም። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱና የቤተክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ በመደንገጋቸው ነው። /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/:: መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል። 

ከዚህም በተጨማሪ ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ይህ ቀን የዘመን መለወጫ ተብሎ ይጠራል። ሌላው ስያሜ ደግሞ ዕንቁጣጣሽ የሚለው ሲሆን ይህም ከሁለት አበይት ምክንያት መጠሪያ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ የመጀመሪያው ምክንያት የኖኅ ልጅ ካም ከወንድሞቹ ጋር ምድርን ሲከፋፈሉ በዕጣ አፍሪካ ስትደርሰው መጀመሪያ ያረፈው ኢትዮጵያ ላይ በመስከረም ወር ሲሆን በዚህ ጊዜ የምድሩንና የአበቦቹን ማማር አይቶ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ሲል ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል። ሁለተኛው ንጉሡ ሰሎሞን ለንግሥት ሳባ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ ያበረከተላት በዚህ ወር በመስከረም ስለነበር፤ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ መጥቷል ብለው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስተምራሉ።  

ከላይ እንዳየነው የዘመን መለወጫ ፍሬ ሃሳብ እንደዚህ ከሆነ እኛስ በአዲስ ዘመን ምን ልናደርግ ይገባናል? ‹‹አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል፤›› (ማቴ 6፥ 33-34) ብሎ ጌታችን እንዳስተማረው እኛም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አዲሱ ዓመት ደርሰናል፤ ይህም  በእኛ መልካምነት ሳይሆን ሁሉንም ሳይለይ (በአንድነት) በቸርነቱ ከመልካምነቱ እንዲሁ ያለዋጋ በሚያድል በእግዚአብሔር የተከናወነ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ባለፈው ዘመን የነበሩ ዘንድሮ ግን በህይወተ ሥጋ የሌሉ  ብዙዎች ናቸው፤ እኛም የምንጠራበት ሰዓት መቼ እንደ ሆነ አናውቅምና አበው ዘመን ለፍሥሐ እድሜን ለንስሐ እንዲሉ ይህን የሰጠንን ዓመት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መንገዳችንን በቃሉ በመምራት ልንጠቀምበት ይገባል። ምክንያቱም አበው ትውልድ ይኃልፍ ትውልድ ይተርፍ፤ ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ትርጓሜ) ከእኛ በፊት የነበረው ትውልድ እንዳለፈ ሁሉ ይኸኛውም ትውልድ በበኩሉ ኃላፊ ነው። እኛ ክርስቲያኖች አሮጊው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ በምን ዓይነት መንፈስ ነው የምንቀበለው? ለዚህ ጥያዌ መልስ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ «የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራት እና በሥጋ ምኞት፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና» በማለት ያስተምረናል። (1ጴጥ.4፥3) 

በአጠቃላይ እግዚአብሔር በቸርነቱ ዘመንን ያቀዳጀን በመንፈሳዊ ሕይወት ታድሰን ተለውጠን አዲስ የተሻለ መንፈሳዊ ሰው እንድንሆን ነው። አዲስ ሰው መሆን ማለት ያለፈ ዘመንን ክፉ ግብር/ሥራ/ መተው፣ ደግሞም ኃጢአት ላለመስራት መታቀብና ራስን  መግዛት ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ለመጨረሸዋ የፍርድ ቀን መልካምን ቃል የሚያሰማንን ተግባር  ለማከናወን ለመልካም ሥራ መነሳሳት፣ የመንፈስ ፍሬያትን ማፍራት ያስፈልጋል። «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።» ገላ5፥ 22 እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው እንዲል። (2ኛ ቆሮ 6፥2) አዲሱ ዓመት ከኃጢአታችን በንስሐ ውኃ የምንታጠብበት፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ በቀራንዮ የቆረሰልንን ቅዱስ ሥጋውን የምንበላበት፣ ያፈሰሰልንን ክቡር ደሙን የምንጠጣበት ዘመን እንዲሆንልን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፣ አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር