የጾም ጥቅም

የጾም ጥቅሙ ምንድን ነው?

ጾም በነፍሥም በሥጋም ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ የትሩፋት ሥራ ነው። በጾም ድኅነተ ሥጋን ካገኙት መካከል የአስቴር እና የወገኖቿን ታሪክ እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። አስቴር በወገኖቿ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ይሻር ዘንድ ያደረገችው ሁሉም ወገኖችዋ እንዲጾሙ እና እንዲጸልዩ ነበር። በዚህም ጾም ጸሎት ምክንያት የተላለፈው የሞት ውሳኔ ወደ ሕይወት እንዲቀየር ሆኗል (መጽ አስቴር 4-10)። እንዲሁም የነነዌ ሰዎች በፍጹም እምነት በመጾማቸውና በመጸለያቸው በኃጢአታቸው ምክንያት ሊመጣ የነበረው መዓት ተመልሷል (ትን. ዮናስ 3 )።

ከዚህም ባለፈ በጾም ራሳችንን መግዛት እስከቻልን ድረስ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ትልቅ ስጋት የሆኑትን በምግብ ብዛት የሚመጡትን የዘመናችን የተለያዩ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችለን ይሆናል። በተለይም በምዕራባውያን ዘንድ አስጊ እየሆነ የመጣው ከልክ በላይ የሆነ ውፍረት ትልቅ የኅብረተሰብ ጤና ችግር ምክንያት እየሆነ መጥቷል። ለዚህም ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የመንፈሳዊ ሕይወት ትሩፋት ውጤት የሆነው ጾም ከስግደትና ከጸሎትጋር እንዲሁም በንስሐ ሕይወት ሆነው ሲፈጽሙት ነው፡፡

ጾም ለድኅነተ ነፍስ ያለው ጥቅም ደግሞ ሥርየተ ኃጢአት እንድናገኝ ማድረግ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የጾምን ጥቅም  “ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጸምም ኵሎ ፍትወታ ዘሥጋ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና- ጾም የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች የሥጋንም ምኞትን ሁሉን ትገታለች ለጎልማሶችም ድካምን ታስተምራቸዋለች“ በማለት ይገልጸዋል። ጾም የነፍስን ቁስል ትፈውሳለች ሲል የነፍስ ቁስል ኃጢአት ነውና በጾመንስሐ አማካኝነት ከኃጢአት የምንነጻበት መንገድ ስለሆነ ነው። ጾም ራስን መግዛት መቻልን ታጎናጽፋለች፤ የሥጋን ፍላጎት መቆጣጠር በራሱ ትልቅ ፈተና ነውና። አንድን ከተማ በጦርነት ድል ከማድረግ ይልቅ ራስን መግዛት ይበልጣልና (ምሳ 16፥:32) እንዲል። እንደ መላዕክት በደብር ቅዱስ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት ራሳቸውን መግዛት ባለመቻላቸው በደቂቀ ቃየል ተሰናክለው ወድቀዋል። ይህም የከፋ ኃጢአታቸው የዓለም በንፍር ውሃ መጥፋትን አስከትሏል (ዘፍ 6)። በመሆኑም ጾም ከኃጢአታችን ይቅር የምንባልበት እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናጎለብትበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።

ሌላው በጾም የምናገኘው መንፈሳዊ ድል ነው። ኃጢአት የሌለበት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አርዓያ ሊሆነን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ አርዕስተ ኃጣውዕ የተባሉትን ስስትን ትዕቢትን እና ፍቅረ ንዋይን ድል ነስቶልናል። (ማቴ 4፥1-10)። እኛም ስንጾም ፍቅረ እግዚአብሔር ይኖረናል፣ የተደረገልንን ቸርነት እናስባለን፣ ድል የተነሱትን አርዕስተ ኃጣውእን በመተው ከትዕቢት ይልቅ ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ስንችል ”ትሕትና ከመ ይደሉ አልቦ ዘይደሉ- ትሕትና እንደሚገባ የተገባ ነገር የለም”(ጾመ ድጓ ዘቅድስት) እንዲሁም ከፍቅረ ንዋይ ይልቅ ምጽዋትን የምናስቀድም እንሆናለን ”ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት- ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ”(ጾመ ድጓ ዘወረደ) እንዲል። ከዚህም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጠነክር የጎላ ሚና ይኖረዋል። የጾምን ጥቅም የተረዱ ሐዋርያትም በእምነታቸው እስከ ሞት ድረስ የጸኑትና ታላላቅ ገቢረ ተዓምራትን ሊያደርጉ የቻሉት በጾምና ጸሎት ነው። ሠለስቱ ምዕት ቅዱሳን አባቶቻችን ስለሃይማኖት ሲወስኑ በጾምና በጸሎት በመትጋት መንፈስ ቅዱስን አጋዥ በማድረግ ነው። ሌሎች ቅዱሳን እነ አብርሐም ሶርያዊ በጾም ተራራው ተነቅሎ እንዲሄድ አድርገዋል፤ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በጾም ግዕዛን የሌላቸውን እንስሳትን ሁሉ በመገዘት እንዲታዘዙ ማድረግ ችለዋል።

እንግዲህ የጾምን ጥቅም በአጭሩ እንደተረዳነው፣ እኛም ዛሬ ጾም ሊያስገኝ የሚችለውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ዕሤት ተስፋ በማድረግ ስለ ራሳችን፣ ስለ ቤተክርስቲያናችን፣ ስለ ሀገራችንና ስለ ዓለሙ ሁሉ መጸለይና መጾም ይገባናል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያናችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በውስጥም በውጭም ከተለያየ አቅጣጫ እየተፈተነች ያለችበት ጊዜ በመሆኑ ይህን ፈተና ለመወጣት አብዝተን መጾምና መጸለይ ይገባናል። ይህንንም ለማድረግ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎትና ምልጃ አይለየን። አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!!