የጾም ጥቅም

ጾም ማለት ለተወሰኑ ሰዓታት ከእህል እና ከውሃ (ጥሉላት መባልዕትን ጾሙ እስኪፈጸም ፈጽሞ መተው) እንዲሁም ለተወሰኑ ጊዜያት ከሥጋ ፈቃዳት መከልከል ነው።። ስለዚህ መጾም ማለት በጾም ወቅት የምግብ ዓይነትን መለወጥ ብቻ ሳይሆን የምንወደውን የሥጋ ፍላጎት ስለ እግዚአብሔር ብለን መተው ነው።። የሥጋ ፍላጎት የዓለምን ምኞት መፈጸም ሲሆን ይህን ነገር የምንገታው ደግሞ ራሳችንን በጾም በመግዛት ነው። ”ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ- ነፍሴን በጾም አስመረርኋት” መዝ. 68፥10 እንዲል። ታሪካቸው በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎ የምናገኘው ሦስቱ ወጣቶች በንጉሥ ቤት እየኖሩ የተሻለ ነገር መመገብ ሲችሉ እግዚአብሔርን ስለ መውደድ ብለው በንጉሡ ቤት ከሚዘጋጀው ማለፊያ ምግብ ይልቅ ጥራጥሬን መመገብ መረጡ። ትን ዳን. 1፥8-16። በተጨማሪም እንደ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በመፍራት ምክንያተኝነትን በመተው ከኃጢአት መጾም ነው:፡ ዮሴፍ ኃጢአቱን ለመሥራት የእመቤቱን ፈቃደኝነትና የእርሱን ወጣትነት እንደ ምክንያት አላቀረበም። ነገር ግን ፈጣሪውን ዘወትር በፊቱ በማድረጉ ከኃጢአት ለመጾም ችሏል። ዘፍ 39፥7-13;: ስለዚህ ጾም ማለት እያለንና ማድረግ እየቻልን ስለ እግዚአብሔር ብለን መተው ነው።

ለምን እንጾማለን?

ጾም ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነትና ፍቅር የምንገልጽበት የአምልኮ ሥርዓት መገለጫ ነው። እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ መጀመሪያ የሰጠው ትዕዛዝ ጾም ነው(ዘፍ 2፥16-17)። ይኸውም ዕጸበለስን እንዳይበላ ነበር። ለአዳም እና ለሔዋን ይህ ህግ መሰጠቱ የፈጣሪ እና የፍጡር፣ የአዛዥና ታዛዥ መገለጫ ነበር።

አዳም ይህን የጾም ትዕዛዝ በማፍረሱ ከፈጣሪው ጋር ተለያየ ስለዚህም በጾም ማፍረስ የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ የመጣው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ሥራውን የጀመረው በጾም ነበር (ማቴ 4፥1-11)። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ፣ ሁሉ በእጁ ሲሆን ምንም እንደሌለው ተራበ፤ ይህም ለእኛ አርዓያ ይሆነን ዘንድ ነው። አንድም አምላከ ነቢያት ነውና ኦሪትንና ነቢያትን ሊፈጽም እንደ ነቢያቱ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በገዳም አደረ፤ በዲያብሎስም ተፈተነ “ጾመ ሙሴ፤ ጾመ ዳንኤል፤ እግዚእነ ጾመ አርዓያ ዚአሁ ከመ የሀበነ”(ትርጉም:- ሙሴ ጾመ፤ ዳንኤል ጾመ፤ ጌታችንም አርዓያ ይሆነን ዘንድ ጾመ) ጾመ ድጓ። ሐዋርያትም አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት በጾም ነበር ፈጣሪያቸውን የጠየቁት፤ ከዚያም በአገልግሎታቸው የጸኑ ሆነዋል። እኛም ዛሬ ጌታችንን፤ ቅዱሳን ነቢያትን፤ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን አብነት በማድረግ ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ለማስገዛት እንጾማለን።

እንዴት እንጾማለን?

መጾም ማለት ከእህል ውኃ መከልከል ከጡልላት ምግቦች ወደ አትክልት ምግቦች መቀየር ብቻ ሳይሆን ሰውነታችን ከሚፈልገው መጠን ያለፈ ደስታ በመታቀብ የሥጋን ምኞት መግታት መቻል ነው። ስንጾምም በምግብ ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነታችን በተለይም የስሜት ሕዋሳታችን ሁሉ ከኃጢአት መጾም ይኖርበታል። ይህንንም ቅዱስ ያሬድ “ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ – ዓይን ክፉ ከማየት ይጹም አንደበት ክፉ ከመናገር ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም“ በማለት ገልጾታል። ይህም ማየት የኃጢአት መጀመሪያ ነውና ዓይናችን ክፉ ከማየት መቆጠብ ይኖርበታል። ማየት የልቡናን ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ ኃጢአትን ወደመሥራት ይወስደናል። የያዕቆብ ልጅ ዲና ከአሕዛብ ወገን የምትሆን ጓደኛዋን ለማየት ብላ ወደማይመስሏት ሰዎች ሄደች በዚያም የአሕዛብ ወንድ አይቶ ተመኛት ከርሱም ጋር በዝሙት በመውደቅዋ ለራሷም ጥፋት እና ለወንድሞቿ የጥል መንስኤ ሆናለች ዘፍ34። ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር ሴትን አይቶ የተመኛት ሁሉ በልቡ አመነዘረ ብሏል። ማቴ.5፥28 ማየት ክፉ ምኞትን የሚያመጣ የኃጢአት መጀመሪያ ነው። ስለዚህ በምንጾምበት ወቅት ክፉ ከማየት መቆጠብ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊፈትን እና ክፉ ምኞትን ሊቀሰቅስ ወደ ሚችል ነገር ማተኮር ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ዛሬ በቴክኖጂ አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊፈትኑ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ እንደ ክርስቲያንነታችን ከነዚህ ሁሉ ልንጾም ይገባናል።

ሌላው መጾም ያለበት አንደበታችን ነው። ይህም በአንደበታችን ክፉ ከመናገር በመቆጠብ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ለጸሎት መትጋት ይኖርብናል። በጾም ወቅት አርምሞን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል። አርምሞ የሌለበት ጾም ዋጋ አይኖረውም “አርምሞ ተአግሶ ተዐቅብ ሃይማኖተ” (ትርጉም ዝምታ፣ መታገስ ሃይማኖትን ትጠብቃለች) እንዳለ ቅዱስያሬድ። እንጾማለን እያልን ወንድማችንን በማማት የምንጎዳ ከሆነ ጾማችን እርባና አይኖረውም። “ሶበ ትዜከር አበሳሁ ለእኁከ ተንሢአከ ጸሊ በጥቡዕ ልብከ አስተስሪ ሎቱ – የወንድምህን በደል ባሰብክ ጊዜ ተነሥተህ ጸልይለት በቆራጥ ልቦና ይቅር በልለት” (ጾመ ድጓ ዘወረደ)፤ ምክንያቱም ጾም አፍቅሮ ቢጽን የምናጎለብትበት ዓይነተኛው መሣሪያ ነውና። ወንድምን በክፉ ከማንሳት ይልቅ ስለ ወንድምና እህታችን ብለን መጸለይ እና ይቅር ማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ በር እንዲከፈትልን ያደርግልናል።

ሌላኛው መጾም ያለበት የስሜት ህዋስ ደግሞ ጆሮ ሲሆን ይኸውም ክፉ ከመስማት መቆጠብ ነው። ሕዝበ እስራኤልን በባርነት ከነበሩበት ከግብፅ ምድር አውጥቶ፣ ባህር አሻግሮ በምድረ በዳ መና ከሰማይ እየመገበ፣ ውኃ ከአለት እያፈለቀ፣  መዓልቱን በደመና ሌሊቱን በፋና እየመራ ያደረሳቸውን አምላክ ከሀሰተኛ ሰዎች በሰሙት ክፉ ወሬ ብቻ ተሰናክለው የእግዚአብሔርን ኃይልና ረድኤት ዘንግተው እንደገና ወደ ግብጽ መመለስ በመመኘታቸው የተስፋዋን ምድር እንዳያዩ ሆነዋል (ዘዳ 13-14)። አበው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል እንዲሉ፣ እንደ እስራኤላውያን ለክፉ ወሬ ጆሯችንን መስጠት አገልግሎታችንን ሊጎዳ ብሎም በሃይማኖታችን ላይ ኑፋቄን ሊያመጣብን ስለሚችል፣ ጆሯችን ከክፉ ወሬ እንዲጾም ማድረግ ይገባል:፡ እንዲያውም በጾም ወቅት ከምንጊዜውም በበለጠ ገድለ ቅዱሳንን ልንሰማ፣ ልናሰማ ይገባናል፤ ምክንያቱም የቅዱሳን ጽናትና ተጋድሎ የእኛን ሕይወት የምንመዝንበት፣ ተጋድሏቸውን በማሰብ የምንጸናበት ሕይወትን እናገኝ ዘንድ ይረዳናል።

ባጠቃላይም በጾም ወቅት ከሌላው ጊዜ በበለጠ አብዝተን መስገድ፣ መጸለይ እና መመጽወት እንዲሁም የስሜት ህዋሳታችንን በመግታትና አርምሞን ገንዘብ በማድረግ በተመስጦ ወደ አምላካችን መቅረብ ይጠበቅብናል።