ዘወረደ

ዲያቆን ስመኘው ጌትዬ

የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ.ም.

እንኳን ለዓቢይ ጾም በሰላም አደረሰን። የ፳፻፰ (2008) . ዓቢይ ጾም የካቲት ፳፰(28) ቀን ተጀምሮ ሚያዝያ ፳፫ (23) ቀን ይፈጸማል። ይህ ጾም 8 ታላላቅ ሳምንታት የተከፋፈለ ሲሆን እነርሱም ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኲራብ፣ መጻጒዕ ደብረዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ፣ እና ሆሳዕና ይባላሉ፡፡ በዚህ ጾም ውስጥ በአጠቃላይ ጾመ እግዚእነ (የጌታችን ጾም) አርባውን ቀን ሲይዝ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል እና የመጨረሻው ሳምንት የጌታን ሕማማት የምናስብበት ሰሙነ ሕማማት የቀረውን ክፍል ይይዛሉ፡፡

ዛሬ የመጀመሪያውን ሳምንት ወይም ዘወረደ የተባለውን ጾም ስያሜውን እና ምስጢሩን በታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ እናያለን፡፡ የብሉያት እና የሐዲሳት መጽሐፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ከጸዋትወ ዜማ መጽሐፍቱ አንዱ በሆነው የድጓ ክፍል ጾመ ድጓ (በጾም ስለሚደረስ ጾመ ድጓ ተብሏል) ስለ ጾም ብዙ ጽፏል።ከዘወረደ ጀምሮ ያሉት ስምንቱም ሳምንታት ስያሜያቸውን ያገኙት ከጾመ ድጓ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በተለይ ዋዜማ ክፍሉ ላይ ያሉትን የመጀመሪያ ቀለማት በመምረጥ የየሳምንታቱን ስያሜዎች አስገኝቷል፡፡ በዘወረደ ድርሰቱ ቅዱስ ያሬድ በጾም ልናስባቸው እና ልናከናውናቸው የሚገቡንን ነገሮች ከሥነምግባር፣ ከጸሎት፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከመስቀሉ አንፃር እየሆነ ይነግረናል፡፡ ዛሬ በዘወረደ ድርሰቱ ከተገለጡት በጥቂቱ እያነበብን እንማማራለን።

ቅዱስ ያሬድ የጾሙን ድርሰት ሲጀምርሃሌ ሉያቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ሁሉን የጀመረ ሁሉን የሚያስጀምር ሁሉን የፈጸመ ሁሉን የሚያስፈጽም ጾማችንንም እንዲሁ ያድርግልን እያለ ነው።ስለዚህም ቀጠለዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሃዩ በቃሉከላይ ከአርያም የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት ወይም ከላይ መውረዱን አላወቁም ይሆን? እርሱስ በቃሉ ሁሉን የሚያድን ጌታ ነው።የሰኞ ዋዜማውን ይጀምራል።ይህንንም መነሻ አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሳምንቱን ዘወረደ ብላ ሰይማዋለች።

ጾሙን አሁን እንዴት እንየው? “ኩኑ እንከ ከመ ብእሲ ጠቢብእንግዲህ ስለ ኀጢአቱ መሰረይ እንደሚጾምና እንደሚጸልይ ጥበበኛ ሰው ሁኑ።መልካም ነገርን ታገኙ ዘንድ በእውነት ሂዱ ሰንበትን አክብሩ መልካም ነገርን ማድረግ ተማሩ… ” ሊቁ እንደሚጾምና እንደሚጸልይ ሰው ሁኑ ብቻ አላለም ።ነገር ግን ጾማችንን በጥበብ ይሁንጥበበኛአለን እንጂ።ዳግመኛም አስተውሉእንግዲህብሎ መጀመሩን ከዚህ በፊት ምንም ሁኑ ምንም በቃ ሁሉም ይብቃ ጥበብን ወደ ልባችሁ ጥሯት በጥበብም ጾምን እና ጸሎትን ስለ ኃጢአታችሁ ከዚህ በኋላ ገንዘብ አድርጉ።አለፍ ብሎእንግዲህያለውን ቃሉን ይገልጠዋልአከለክሙ መዋዕል ዘሃለፈ ዘተቀነይ ለግእዘጋክሙጋችሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ ከእንግዲህስ ወዲህ ጹሙ ጸልዩም ለእግዚአብሔር ተገዙ …” አሁን ሥጋን ከምኞቱ እና ከመሻቱ ጋር እንሰቅለዋለን። ስለዚህም ከአባቱ ቅዱስ ጴጥሮስ የተማረውን መነገር ባለበት ጊዜ ሊቁ ነገረን።የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” 1ጴጥ 43 አሁን ጊዜው የጾም የመገዛት ነው።ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።መዝ 211 ብሎ ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ቅዱስ ያሬድም በፍርሃት እንድንገዛ በአባቱ ቃል ይመክረናል።

ስለ ጾምም “ይህች የተከበረች እና ታላቅ ጾም ለሚያምኑ ሕዝበ ክርስቲያኖች የተሰጠች ናት ለእግዚአብሔር ልጆች መሪ የሆነቻቸው የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ።በዚህች ጾም የእሥራኤል ልጆች ባሕርን ተሻገሩባት፣ የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ዳንኤል ከአናብስት አፍ ዳነባት፣ የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ሶስና ከአይሁድ ረበናት ዳነችበት፣ የጾምን ክብሯን ታላቅነቷን ተመልከቱ ታላቅነቷን ተመልከቱ ለሰነፎች ሀዘን ለጠቢባን ደስታቸው ናት፣ የጾምን ታላቅነት ተመልከቱ የዚችን ጾምእያለ ልንጀምረው የምንደረደርለትን ጾም እያከበረ እያዜመ አስታወቀን። በጾምስ እንዴት እንሁን እንዳይሉትእርሱ ልብ የሚል የሚያስተውል የሚጾምም ራሱን ዝቅ የሚያደርግም ምስጉን ነው።በሕይወቱ ስለ ሠራው በጎ ሥራ ከአምላኩ ክፍያውን ይወስዳል(የሚወስድ ነው) ” እያለ እያዜመ ይቀጥላል።”…እጄ ምድርን መሰረታት ቀኜም ሰማይን አጸና በሕይወት ትኖሩ ዘንድ በጾምና በጸሎት በቀናች ሃማኖት ወደ እኔ ተመለሱ።ነፍሳችን በምትሰማው ሠማያዊ ዜማ የሚለን ነገር አለ።እንጹም እንጸልይ በየዋሃትና በፍቅር ለእግዚአብሔር እንሁን ቀደምት አባቶች ከኃጢአት እንደዳኑ በአርምሞ ከፈተና እንዳመለጡ (እንደሸሹ)” ጾምን ከጸሎት አይለያትም ዋጋዋ ታላቅ ነውና።ጸሎት ደግሞ በልምድ ሳይሆን በተሰበረ ልብ በየውሃት መሆን አለበት ።አሁንም ቢሆን የውሃት ብቻውን አይበቃም።ሁሉን ማሰሪያው ፍቅር ሊታከልበት ይገባል።ለዚህም ነው በዚህ ድርሰቱ ቅዱስ ያሬድ በየገጹ ቢያንስ አንድ ጊዜአፍቅር ቢጸከ” “ወንድህን ውደድየሚል ትእዛዝ ሳይጽፍ ያላለፈው።ፍቅር ያለው ሰው ደግሞ በየትኛውም ጊዜ በምንም ሁኔታ ራሱን ለአምላኩ ያስገዛል፣አርምሞን ገንዘቡ ያደርጋል።ይህም እርሱን ወደ አላማው ያደርሰዋል።አላማው የእግዚአብሔር መሆን አይደለምን? የእርሱ ከሆነ ደግሞ ወጥመድን ፈተናን ሁሉ ያልፋል።ዓለም የምታዘጋጅለት ሁሉ ከአምላኩ አይለየውም።ስለዚህ አባታችን በዚህ ፍቅር ኖሮ ፍቁራንየእያለ ያዜምልናል ድምጹን እንስማየምወዳችሁ ወንድሞቼ የዚህ አለም ንብረት ምን ይጠቅመናል? ምድራዊ መዝገብ እንደሚጠፋ አልሰማችሁምን?ስለዚህ በእግዚአብሄር መታመንን ያጸና በሕይወት ይኖራልይህን ያለን ደግሞ ንብረት አያስፈልግም ለማለት አይደለም ሁሉ እያለን እንደሌለን እንኑር ከአለም ከንቱ መጎምዠት እንጹም እያለን እንጂ።ይህ ይቻላልን? ትሉኝ ይሆናል።እኔ ምን እላችኋለሁ እርሱ ግን መልስ አለው።ይጹም ዓይንዓይን ይጹም ልሳን ይጹም ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም በፍቅር ይህ ሁሉ ይሁንይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ እኛ በአለም እያለን ከአለም ውጪ እንሆናለን።ያኔ ደግሞ ሰማያዊ ሆንን፣ ጾምን ማለት ነው።እስመ በጾም ወበጸሎት ይሰረይ ኩሉ ኃጢአት በጾም ድኅኑ አበው ቀደምት ኤልያስ ዐርገ ውስተ ሰማያትበጾምና በጸሎት ኃጢአት ሁሉ ይሰረያልና ፣የቀደሙ አባቶች በጾም ዳኑ ኤልያስም ወደ ሰማያት ዐረገ።ኤልያስን በጾም ሕያዋን ከመሬት ከፍ ብለው በጿሚው ሥጋቸው ሥጋዊውን ምድር አሸነፉ አለን።ስለዚህ ወገኖቼ በጾም ህግን መጠበቅ ብቻ ሣይሆን ከምድራዊ ሕግም በላይ በመሆን ከሥጋ ፈቃድ ወጥቶ ወደ ርቱዕ ሕይወት መሸጋገር እንዲቻል ሲያሳውቀን ነው።

እንዲህ ሊገስጸን ደግሞ ጀመረ።አንተስ አስቀድመህ ራስህን መርምርየምን ምርመራ ነው?ሥጋዊ ምርመራ አይደለም የነፍስ ህመምን እንጂ ።ወገኖቼ የጾምን በር ሳናንኳኳ አንከፍትም። ለመግባት ግን እንድንገባ ሆነን መገኘት አለብን ።ከኃጢአታችን ጋር ከበደላችን ጋር ሆነን አንገባም። ያለፈውን ትተን ንስሐ ገብተን ያቀድነውን የኃጢአት ቀጠሮ ሰርዘን ራሳችንን የተገባ ካደረግን በኋላ የበሩን ደውል እንጫን። አሁን ከራሳችን ጋር ከምርመራ በኋላ ታርቀናል። ቀጣዩን እርሱ ያዚምልንጹም ለእግዚአብሔርም ተገዛበእውነት ዜማው ይለያል፣ ጣዕመ ዜማው አዲስ ነው።”በምሥጋና ላይ እንግዳ (ወንድም) መውደድን ጨምርምሥጋና ላይ መውደድ ጨምሩ ማለቱ ለምን ይሆን? በትክክል የሚጾም ጾም ምሥጋና ነው።ስለዚህ በምሥጋና ጾማችን ላይ እንግዳ (ወንድም) መውደድን ጨምሩ አለን።አሁንም እንዲሁ የተፈለጠው እንጨት(ጾምን) በልጥ ፍቅር መታሰር አለበትና ወንድማችሁን ውደዱ እያለ ሊቁ ያሳስበናል።

ከምግብህ ላይ ስጥ የተራበን አጥግብይህንን ዜማ ሰማችሁን? በጾም ያተረፍነውን (ቁርስ ወይም ምሳ) ምግብ በምንበላ ሰአት በአይነት እንዳናካክሰው እንዲህ አለን። ያልተበላ ምግብ በገንዘብ የሥጋዊ ሕይወት ኢኮኖሚ ማድለቢያ ሳይሆን የነዚያ ተርበው ፍርፋሪ ያጡት እንግዶች ነው።እንውደዳቸው ብሎን የለ?ታዲያ ሲርባቸው ቢያንስ በዚህ እናጥግባቸውና ፍቅራችንን የእውነት ጾማችንን የጽድቅ እናድርገው።የራባቸውን አብሉ ሳይሆን አጥግቡ ማለቱን ልብ እንበል።ለድሃ አደጉም ፍረድድሃ አደጉ ዛሬ በጾም ከእኛ የሚፈለገው የለምን?ለምኖ ስላልተሰጠው የእኛን ፍትህ አይሻምን? ለተራበው፣ለተጠማው፣ለታረዘው፣ለታመመው፣ የእኛን በጎነት ለሚጠብቀው ሁሉ እንድረስ። እዝን ያለው በውሳጣዊ እዝን(ጆሮው) ይስማ። ጾማችን በረከትን ያሰጠን ዘንድ ለችግረኞች ሁሉ መድረስ ቸል አንበል።

ራሳችንን መርምረን ብንጾም፣ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ብንገዛ፣እንደ መላእክቱ ለምሥጋና ብንተጋ፣ ወንድሞቻችንን እንደ ራሳችን ብንወድ፣ካለን ለተቸገሩ ብናካፍል፣ለምስኪኑ ብንራራ በኋላ በተፍጻሜቱይህ ለአንተ መልካም ነውይለናል

ጌታም በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ ተብሎ በነቢዩ የተጻፈውን እንደፈጸመ ደቀ መዝሙሩም ቅዱስ ያሬድ የጾምን ነገር በጾሙት እየመሰለ እንዲህ አለንሙሴ ጾመ ዳንኤልም ጾመ ጌታም ስለ እኛ ጾመ ስለዚህ ጾምን ቀድሱሙሴ ቢጾም ሕግን ሊቀበል ዳንኤል ቢጾም ከአናብስት አፍ ሊወጣ የወገኖቹን ነፃነት ናፍቆ፣እንኪያስ ጌታ ለምን ጾመ? አርአያ ሊሆነን ፣ጾምን ሊቀድስልን እንጂ ምን ጎድሎበት ምን ሊያገኝ ነው? ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ ነግሮን የለምን?2ኛ ጴጥ 3:10 ስለዚህ እኔም ከአባቴ ጋር አልሁ ጾምን ቀድሱ ፣ተቀድሶ ተሰጥቶናልና።ጾምን ቀድሱ ያለፈው የኃጢአት አገልግሎት ይብቃ።ጾምን ቀድሱ ሙሴ በሲና ጾሟልና ኢያሱም በጾም ዳነ በገባኦን ፀሐይን አቆመ” ።ዜማው እንዳያልቅብን ብንጓጓም ዛሬ በነገ መቀየሩ ግድ ነውና ሳይሰናበተንበበጎ ሥራ ሁሉ ስትጓዙ የሰላም መንገድን ተከተሏት በእርሷም ሂዱ ጾምን ፍፁም እንጹም የሰላም እህት ቅድስት ጾምን ጌታ ራሱ ጾሟታልናእኛም ስንሰናበትየማይጠልቅ ፀሐይ ፣የማይጠፋ ብርሐን፣የማያበድሩት ባዕለ ጸጋ ፣የሐዋርያት ጌጣቸው፣የችግረኞች ሃብታቸው፣ለተገፉት መጠጊያቸው ሁልጊዜ እናመሰግንሃለን መሀሪ ንጉሥ ራው ቸል የማይል።የአብርሀም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ምሕረትህን አሳየን በአርአያህ የሠራኸውን የፈጠርከውን ሕዝብህን አታጥፋ አትተው።እንዳለ ቅዱስ ያሬድ።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየንይቆየን!