ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ

አባቷ  ባሕር አሰግድ እናቷ  ደግሞ  ክርስቶስ አዕበያ  ይባላሉ። ትውልዷ ከዳሮ /ምስራቅ ኢትዮጵያ/ ወገን ነው። ወንድሞቿ ዮሐንስና ዘድንግል በንጉሥ  ሱስንዮስ ጊዜ ታላላቅ ባለስልጣናት ነበሩ። እናት አባቷ  በህግ በስርዓት ካሳደጓት በኋላ ሥዕለ ክርስቶስ የሚባል የስስኑዮስ የጦር አበጋዝ ቢትወደድ  አግብታ 3 ልጆች መውለድዋን ገድሏ ይናገራል። ይህ ቢትወደድ ይኖርበት የነበረው ግንብ ቤት ፍራሽ እስከ አሁን ድረስ በጋይንት ስማዳ ይታያል።

ወለተ ጴጥሮስ ከቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ጋር በሰላም በመኖር ላይ እያለች ንጉሡ አጼ ሱስንዮስ የተዋሕዶ ሃይማኖቱን ቀይሮ በሮማውያን ሀሰተኛ መምህራን በመታለል ካቶሊክነትን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ህዝብም ካቶሊክ እንዲሆን ዐወጀ።   በዚህ ዐዋጅ የተነሣ በንጉሡ ደጋፊዎችና የቀደመ ሃይማኖታችንን አንለቅም ባሉት እውነተኛ የተዋህዶ ምዕመናን መካከል ታላቅ ጠብ ሆነ።

የንጉሡ ሠራዊትም በተዋሕዶ ምእመናን ላይ ዘመቱ። ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ከዘመቻ ሲመለስ የጳጳሱን የአቡነ ስምዖንን ልብስ እንደግዳይ ሰለባ ለንጉሡ ይዞለት መጣ። ይህንን የሃይማኖቷን መናቅ የአባቶቿን መደፈር የተመለከተችው ወለተ ጴጥሮስ እንደዚህ ካለው ከሀዲ ጋር በአንድ ቤት አብሮ መኖር አያስፈልግም ብላ ቆረጠች። ከዚህም በኋላ ከቤቱ የምትወጣበትን ዘዴ ያለ እረፍት ማሰላሰል ጀመረች:: ከዚያም ወደገዳሙ ለመድረስ እንዲረዷት ከጣና መነኮሳት ጋር መላላክ ጀመረች። የጣና ቂርቆስ ገዳም አበምኔት አባ ፈትለ ሥላሴም ወለተ ጴጥሮስን ይዘዋት እንዲመጡ ሁለት መነኮሳትን ላኩ። በዚያ ጊዜ ልጆቿ ሁሉ ሞተውባት ነበር። ወለተ ጴጥሮስ ከመነኮሳቱ ጋር መጥፋቷን ያወቀው ቢትወደድ ሥዕለ ክርስቶስ ይዘው ያመጡለት ዘንድ አያሌ ሠራዊት ከኋላዋ ሰደደ። ነገር ግን ወለተ ጴጥሮስና ሁለቱ መነኮሳት በእግዚአብሄር ረዳትነት   በዱር ውስጥ ተሰዉረዉባቸዉ  ሊያገኟቸው አልቻሉም። ይህ ተሰዉረዉበት የነበረዉ ቦታ እስከዛሬ ድረስ “ሳጋ ወለተ ጴጥሮስ” ይባላል። በኋላ ዘመንም በስሟ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶበታል።

ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ዕንቁ ገዳም  ገብታ ስርዓተ ምንኩስናን ተምራ መነኮሰች። ታላቁ ገድሏ የተጀመረውም ከዚህ በኋላ ነው። ወለተ ጴጥሮስ ከምንኩስናዋ በኋላ በመላ ሀገሪቱ እየተዘዋወረች ሕዝቡ በተዋሕዶ እምነት እንዲፀና፣ በጸሎተ ቅዳሴም ጊዜ ሃይማኖቱን የለወጠው የንጉሡ የሱስንዮስ ስም እንዳይጠራ ትመክር ጀመር። ብዙ ሰዎችም በምክሯ ተስበው በሃይማኖታቸው እየጸኑ ሰማዕትነትን መቀበል ያዙ።

ይህንን የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ  የሰማው ንጉሥ ሱስንዮስ ተይዛ ለፍርድ ትቀርብ ዘንድ ብዙ ወታደሮች በየአካባቢው አሰማራ። በመጨረሻም በሰራዊቱ ተይዛ በሱስንዮስ ፊት ቀረበች።  መሳፍንቱ መኳንንቱና ለእንጀራቸው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የለወጡ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ትመረመር ጀመር።

ከሳሽዋ “ ንጉሡን ካድሽ፣ እግዚአብሔርን ካድሽ፣ ትዕዛዙን እምቢ አልሽ፣ ሃይማኖቱን ዘለፍሽ፣ሌሎች ሰዎችም ሃይማኖቱን እንዳይቀበሉ ልባቸውን አሻከርሽ” ሲል ከሰሳት። ወለተ ጴጥሮስ ግን እንደ አምላኳ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በከሳሾቿ ፊት ዝም አለች። ንጉሡም ርቃ እንዳትሄድ ነገር ግን ከቅርብ ዘመዶቿ ጋር እንድትኖር / የቁም እስር/ ፈረደባት።

ሃይማኖት ተንቃ፣ ቤተ ክርስቲያን ተዋርዳ የመናፍቃን መጨዋቻ ስትሆን ማየት የሃይማኖት ፍቅርዋ ያላስቻላት ወለተ ጴጥሮስ በግዞት መልክ ከተቀመጠችበት ቦታ ጠፍታ ዘጌ ገዳም ገባች። አብርዋትም ወለተ ጳውሎስና እህተ ክርስቶስ የተባሉ እናቶች ነበሩ። በዚያም በገዳሙ የነበሩ መነኮሳት እና  የአካባቢው ምእመናን በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እንዲጸኑ እየመከረች ጥቂት እንደቆየች የሚያሳጧትና የሚከሷት ስለበዙ ቦታውን ለቃ ወደ ዋልድባ ገዳም ገባች። ዋልድባ ገብታ ሱባዔዋን ከፈጸመች በኋላ በገዳሙ የነበሩትን አባቶችና እናቶች በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆዩ  ትመክራቸው ጀመር።

አጼ ሱስንዮስ የወለተ ጴጥሮስን ተጋድሎ፣ መነኮሳትንና ምእመናንን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ የካዱትም ከክህደታቸው እንዲመለሱ ማድረጓን ሲረዳ ብዙ ወታደሮችን ይልክባት ነበር። በዋልድባ እያለችም የንጉሡ ሰራዊት ሊያስኖሯት ስላልቻሉ ወደ ጸለምት አመራች። በጸለምት የወለተ ጴጥሮስ ትምህርት እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፋ። ምእመናን እየውደዷትና እየተቀበሏት እራሳቸውን ለሰማዕትነት አዘጋጁ። ይህንን የሰማው ሱስንዮስ ይቺ ሴት እኔ ብተዋት እርሷ አልተወችኝም፣  አለና የጸለምቱን ገዥ ባላምባራስ ፊላታዎስን ወለተ ጴጥሮስን ይዞእንዲያመጣለት አዘዘው።

ወለተ ጴጥሮስ በጸለምቱ ገዥ ተይዛ ወደ ሱስንዮስ መጣች። አስቀድመው ሃይማኖቷን እንድትለውጥ ሊያግባቧት ሞከሩ። እርሷ ግን ጸናች። ሦስት የካቶሊክ ቀሳውስት መጥተው ስለሃይማኖትዋ ተከራከሯት። ወለተ ጴጥሮስ ግን የሚገባቸውን መልስ ሰጥታ አሳፈረቻቸው። በየቀኑ የካቶሊክ ቀሳውስት ሃይማኖቷን ትታ ካቶሊክ እንድትሆን በምክርም በትምህርትም ለማታለል ሞከሩ። ይሁን እንጂ ወለተ ጴጥሮስ በተዋሕዶ ዓለት ላይ ተመስርታ ነበርና ፍንክች አላለችም፡፡

በመጨረሻ አንዱ የካቶሊክ ቄስ “እርሷን እቀይራለሁ ማለት በድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ ነው” ሲል ለንጉሡ አመለከተ። ሱስንዮስ ይህንን ሲሰማ ሊገላት ቆረጠ። አማካሪዎቹ ግን “አሁን እርስዋን ብትገል ህዝቡ ሁሉ በሞቷ ይተባበራል፣ ስለ ሃይማኖቱ እንደ እርሱዋ መስዋዕት ይሆናል። ደግሞ ሰው ሁሉ ካለቀ በማን ላይ ትነግሣለህ? ይልቅስ ታስራ ትቀመጥ።” ብለው መከሩት። ንጉሡም ገርበል ወደተባለው በርሃ ሊልካት ወሰነ።

መልክዐ ክርስቶስ የተባለው ዋነኛ የካቶሊኮች አቀንቃኝ ወደ ሱስንዮስ ፊት ቀርቦ “ንጉሥ ሆይ በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ ክረምቱ እስኪያልፍ ድረስ ከእኔ ጋር ትክረም። እኔ እመክራታለሁ። የፈረንጆቹ መምህር አልፎኑስም ሁልጊዜ መጽሐፉን ያሰማታል። ይህ ሁሉ ተደርጎ አሻፈረኝ ካለች ያንጊዜ ግዞት ትልካታለህ” ሲል ለመነው ንጉሡም ተስማማ።

መልክዐ ክርስቶስ ወለተ ጴጥሮስን የካቶሊኮች ጳጳስ ወደሚኖርበት ጎንደር አዘዞ ወሰዳት። ሁለቱ ተከታዮቿ ወለተ ክርስቶስ እና እኅተ ክርስቶስ አብረዋት ሰነበቱ። ወለተ ጳውሎስ ዘጌ ቀርታለች። አልፎኑስሜንዴዝም ዘወትር እየሄደ የልዮንን ክህደት ያስተምራት ነበር። ንጉሡም የወለተ ጴጥሮስን ወደ ካቶሊክነት መቀየር በየጊዜው ይጠይቅ ነበር፣ የሚያገኘው መልስ ግን ሁልጊዜ  አንድ ነው “በፍጹም”። ክረምቱ አለፈ። ኅዳርም ታጠነ። ወለተ ጴጥሮስም በትምህርትም በማባበልም ከተዋሕዶ ሃይማኖቷ ንቅንቅ አልል አለች። ስለዚህ ወደ ስደት ቦታዋ ገርበል በርሃ በሱስንዮስ ወታደሮች ተጋዘች። ወለተ ጴጥሮስ ብቻዋን ገርበል ወረደች። በእርጅና ላይ ያለችው እናቷ ይህንን ስትሰማ አንዲት አገልጋይ ላከችላት። ቆራጧ ተከታይዋ እኅተ ክርስቶስም ወዲያው ወደ እርሷ መጣች።

ገርበል በርሃ ለ፫ አመት ስትኖር ብዙ ጊዜ ትታመም ነበር። ስለዚህ መከራውን ሁሉ ስለሃይማኖቷ ቻለችው። ከግዞቱ ከተፈታች በኋላ ደንቢያ ውስጥ ጫንቃ በተባለ ቦታ ተቀመጠች። በስደቱ ምክንያት ቆባቸውን አውልቀው የነበሩ አያሌ መነኮሳትም ስደቱ መለስ ሲል በዙሪያዋ ተሰበሰቡ: በገዳማቸዉም ፀንተዉ እንዲኖሩ ትመክራቸዉ ነበር።በኋላም ወደ ጣና ቂርቆስ ተጉዛለች።ከዚያም ምጽሊ ወደተባለው ደሴት ሄዳ በዙርያዋ አያሌ መነኮሳትን ሰብስባ ለሃይማኖታቸዉ እንዲጋደሉ መከረቻቸዉ።። ነገር ግን መከራ ያልተለያት ወለተ ጴጥሮስ መዝራዕተ ክርስቶስ የተባለው ሰው ካቶሊክ ያልሆኑ ምእመናንን አስገድዶ  የሚያስጠምቅበትን ደብዳቤ ይዞ ወደ አካባቢው መምጣቱን ስለሰማች መነኮሳቱን መክራና አስተምራ ወደ እየበረሃው ከሰደደች በኋላ እርሷም እንደገና ስደት ጀመረች። ተመልሳ ወደ ምጽሊ የመጣችው አገር ሲረጋጋ  በ፵፱ አመቷ ነው።

ከስደት ስትመለስ መኖርያዋ ያደረገችው መንዞ የተባለውን ቦታ ነው። በዚያ ቦታ ላይ በጸሎትና በስግደት ተጠምዳ ኖረች። በምጽሊ ገዳም አብሯት የነበረው የደብረ ማርያም አበምኔት አባ ጸጋ ክርስቶስም መጽሐፈ ሐዊን ይተረጉምላት ነበር።

አጼ ሱስንዮስ ምላሱ ተጎልጉሎ  ከእግዚአብሔር ቅጣቱን ሲቀበልና የተዋሕዶ ሃይማኖት ስትመለስ አቡነ ማርቆስ ግብጻዊ ጵጵስና ተሹመው  ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመንገድ ላይ ጠብቃ ቡራኬ ተቀበለች። ስለሃይማኖቷ ብላ ከባሏ መለየትዋ እና መከራ መቀበሏ እስከ ግብጽ ድረስ መሰማቱን ጳጳሱ ነግረዋታል።

ከዚያም በመንዞ ገዳም አቋቁማ በተጋድሎተ ቀመጠች። ያቋቋመችው ገዳም የወንዶችም የሴቶችም ነበር።

የተዋሕዶ ሃይማኖት  በዐዋጅ ከተመለሰችና አጼ ፋሲል ከነገሠ በኋላ ንጉሡን ለማግኘትና ወንድሞቿንና ዘመዶቿን ለማየት ወደ ጎንደር መጣች። ንጉሡም በታላቅ ክብር ተቀበላት። በየቀኑም ሳያያት አይውልም ነበር። ወደ እርስዋ  ሲገባም አደግድጎ  ነበር። ይህም ስለሃይማኖትዋ  ጽናትና ስለቅድስናዋ ክብር ነው።

ወለተ ጴጥሮስ በተጋድሎና በምንኩስና ኖራ በ፶ አመቷ  በቆረቆረችው ገዳም ዐረፈች። መታሰቢያዋም ኅዳር ፲፯ ቀን ይከበራል። የተከታይዋ ወለተ ክርስቶስ በዓል ደግሞ  ኅዳር ፯ ቀን ይውላል። በሃይማኖት ጸንቶ  መጋደል ወንድ ሴት አይልም። ቤተ  ክርስቲያናችን እንደነ ወለተ ጴጥሮስ ያሉ አያሌ ልጆች አሏት። የዛሬዎቹ እህቶችና እናቶችም በምግባር ታንፆ በሃይማኖት ጸንቶ በእምነት መጋደልን ከእነዚህ እናቶች ሊቀስሙ ይገባል።  የእናታችን የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ እና የተከታዮቿ ረድ ኤትና አማላጅነት አይለየን። አሜን+++