መስቀል (ለሕፃናት)

መስከረም 15 ፣ 2013

ብንያም ፍቅረ ማርያም

ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል።

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በአዲስ ደብተር፣ በአዲስ እስክርቢቶ፣ በአዲስ ልብስ … ስትማሩ ምን ተሰማችሁ? በጣም ያስደስታል አይደል? ይህ ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር አዲስ ዘመን አዲስ ዓመት ስለሰጠን ነው፡፡ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓልም የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፡፡

 የዘወትር ጸሎት በሚጸለይበት ጊዜ ስለመስቀል እንዲህ የሚል አልሰማችሁም “…መስቀል ኃይላችን ነው፤ ኃይላችን መስቀል ነው፤ የሚያጸናን መስቀል ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመንነው እኛ በመስቀሉ እንድናለን፡፡ ድነናልም፡፡ …” እያልን የምንጸልየው እኛ በጉልበታችን፣ በእውቀታችን ባለን ነገር ሁሉ እንዳንመካ፤ ነገር ግን በመስቀሉ እንድንመካ ነው፡፡

 በመስቀል እንመካለን ምክንያቱም መድኀኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ማለትም ከአባታችን አዳም ከእናታችን ሔዋን ጀምሮ እስከ አሁን ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስን እንደ ደካማ በመስቀል ተሰቅሎ /ተቸንክሮ/ ድል ስላደረገው፤ አዳምና ሔዋንን ከሲዖል እስራት ነፃ ስላደረጋቸው ነው፡፡ ለእኛም መስቀሉ መመኪያችን ሆኖ ዲያብሎስ መስቀሉን ሲያይ ይሸሸናልና ነው፡፡

 ልጆች መስከረም 17 የምናከብረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት አይሁድ መስቀሉ የታመሙትን እንደሚፈውስ፣ የሞቱትን እንደሚያስነሣ ባወቁ ጊዜ በክፉ ቅናት ተነሣሥተው በመስቀሉ ክብር እንዳይገኝ ቆፍረው ቀብረውት፣ ቆሻሻ መጣያም አድርገውት ስለነበር እግዚአብሔርም መስቀሉ ተቀብሮ እንዲቀር ስላልፈለገ ንግሥት እሌኒን አስነሥቶ አባ መቃርስ እና አባ ኪራኮስ በሚባሉ አባቶች መሪነት በቦታው በደረሱ ጊዜ ቦታው ከቆሻሻው ክምር የተነሣ ተራራ ሆኖ ስለነበር ትክክለኛው ቦታ የት እንደሆነ ማወቅ አልቻሉም፡፡

 ንግሥት እሌኒም ወደ እግዚአብሔር በመጸለይዋ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላት ደመራ እንድትደምር በዚያም ላይ እጣን እንድትጨምር ስለነገራት አገልጋዮቿን ወታደሮቿን ጠርታ በአካባቢው ደመራ እንዲተክሉ፣ እንዲያቀጣጥሉ፣ እጣንም እንዲጨምሩበት ነገረቻቸው፡፡ በተባሉትም መሠረት አድርገው ጢሱ  ወደሰማይ ከወጣ በኋላ በእግዚአብሔር ኃይል ተመልሶ መስቀሉ ወደ ተቀበረበት ተራራ አመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ንግሥት እሌኒ እና አገልጋዮቿ ደስ አላቸው፡፡

 ከስድስት ወራት ቁፋሮ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ የጌታችን የመድኃኔታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም የታመሙትን ሲፈውስ ሙት ሲያስነሣ በማየታቸው ከሁለቱ መስቀሎች ለመለየት ችለዋል፡፡ ዲያብሎስ በአይሁድ ላይ አድሮ መስቀሉን ቢደብቅም በእግዚአብሔር ኃይል ሊገኝ ችሏል፡፡ ልጆች መስቀላችሁን አትደብቁ እሺ!

ቸር ሰንብቱ፡፡