አብርሃ ወአጽብሐ

ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም

ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሐ አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ/አህየዋ/ በቅድስና የሚኖሩ እግዚአብሔርን በቅድስና በንጽህና የሚያገለግሉ ነገር ግን ልጅ ያላገኙ መካኖች ነበሩ። ስለሆነም ጌታ ሆይ ደስ የሚያሰኝህ በትእዛዝህም የሚኖር ልጅ ስጠን እያሉ እግዚአብሔርን ይለምኑ ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ስለ እግዚአብሔር ቸርነት ሲነጋገሩ ንግሥት ሶፍያ የሐና እመ ሳሙኤልን ጸሎት በመጥቀስ እሷም እንደ ሐና ሱባዔ ገብታ ፈጣሪዋን እንድትለምን ንጉሡን ጠየቀችው፤ ንጉሡም ኦ ብእሲቶ ሰናየ ሀለይኪ- አንቺ ሆይ መልካም አስበሻል በማለት በምክሯ ተስማምቶ ሱባዔ ገብታ ፈጣሪዋን በጸሎት እንድትጠይቅ ፈቀደላት፡፡ ንግሥት ሶፍያም የካቲት 18 ቀን ሱባዔ ገብታ ፈጣሪዋን መለመን ጀመረች፡፡ ከጸሎቷም ጥቂቱ «በኪሩቤል ላይ የምትኖር፣ ቀለያትንም (ጥልቅ ባሕርንም) የምትመለከት ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ አቤቱ ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ፤ ልቅሶየንም አድምጥ ቸል አትበለኝ» የሚል ነበር፡፡

ደጓ ንግሥት ሶፍያ በብዙ ጸሎትና እንባ ሱባዔዋን ለመጨረስ ስትቃረብ፣ አንድ ራእይ ተገለጠላት፤ እርሱም ከተራራ ላይ የተተከለች ረዥም ዛፍ አየች፡፡ ፍሬዋም ጫፍ እስከ ጫፍ የሞላ ነበር፡፡ ጫፎቿም ምድርን የሚሸፍኑ ነበሩ፡፡ አንድ ሰው፣ ብርሃን ለብሶ ብርሃን ተጎናጽፎ፣ በእጁም ትእምርተ መስቀል ያላት የወርቅ ዘንግ ይዞ መጣ፡፡ ሁለት መሰላልም ይዞ ከዛች ዛፍ ግራና ቀኝ አቆማቸው፡፡ ንግሥት ሶፍያ ግን የዚህ ራእይ ምስጢር አልረዳ ቢላት ተጨነቀች፤ምስጢሩን ይገልጽላት ዘንድም ፈጣሪዋን ለመነች፡፡ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔርም የራሱ ባለሟል የሆነውን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላከላት፤ መልአኩም ብርሃን ተጎናጽፎ ነበርና ከግርማው የተነሳ የነበርችበት ቦታ ሁሉ ብርሃን ሆነ ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በቀኝዋ ቁሞ ራእይዋን ተረጎመላት ፤ እንዲህም አላት፥ «ያየሻት ዛፍ ወንጌል ናት ፤ ዛፍዋ የተተከለችባት ተራራም ኢትዮጵያ ናት፤ የዛፏ ፍሬም ሃይማኖት ነው፤ምድርን ያለበሱ ቅርንጫፎችም መምህራን ናቸው፤ ብርሃን ለብሶ መሰላሎቹን በዛፍዋ ግራና ቀኝ ሲያስቀምጥ ያየሽው ሰውም ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተብሎ የሚጠራው ፍሬምናጦስ ነው፡፡ በእጁ የያዛት የወርቅ ዘንግም ጥምቀት ናት፤ እነዚህ ሁለቱ መሰላሎችም ልጆችሽ ናቸው፤ በመሰላሉ የሚወጡ የሚወርዱ ሰዎችም ምእመናን ናቸው፡፡ የሚበሉትም ፍሬ የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው» ከዚህም በኋላ ከእርሷ ተሰወረ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሡ በራእይ ተገልጾ ፥ «ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር የሰጠህን እነዚህን ዕንቍዎች እንካ ተቀበል» ብሎት ተሰወረ፡፡ እግዚአብሔር ይሁን ብሎ የወደደውና የፈቀደው አይቀርምና እግዚአብሔር ንግሥት ሶፍያንና ንጉሥ ታዜርን በበረከት ስለጎበኘ ሶፍያ ጸነሰች፡፡ የጽንሷም ወራት በተፈጸመ ጊዜ ታኅሣሥ 29 ቀን በ 312 ዓ.ም መንታ ልጆችን ወለደች፡፡ ሕጻናቱ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እንደ አዋቂ ሰው በፍቅር ተጠምደው አንዱ ለሌላው በማሰብ ጡት እየያዙ አንደኛው ለሁለተኛው ይሰጣጡ ነበር፡፡ እንደ ሕጻናት ጸባይ አላለቀሱም፡፡ ነገር ግን ይትባረክ እግዚብሔር አምላከ አበዊነ -የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡

እንደ ሙሴ ሥርዓትም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዷቸው፤ እግዚአብሔር ተግዳሮትን /ሽሙጥን/ ከእኛ አራቀ ሲሉም ስማቸውን አዝጓጉ ብለው ጠሯቸው፡፡ አዝጓጉ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ በብፅዓት የተወለዱ ስለነበር በተወለዱ በአምስት ዓመታቸው በታላቅ ክብርና ስነ ሥርዓት ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፡፡ ኑሯቸውና ዕድገታቸውም በቤተ መቅደስ ሆነ፡፡ መጻሕፍተ ኦሪትንም እየተማሩ አደጉ፡፡

አዝጓጉ በተወለዱ በ 12 ዓመታቸው ፣ ቤተ መቅደስ በገቡ በ 7 ዓመታቸው አባታቸው ንጉሥ ታዜር/ ሠይፈ አርእድ/ አረፈ፡፡ ምንም እንኳ እናታቸው ሶፍያ / አህይዋ/ ለጥቂት ጊዜ መንግሥቱን ስትመራ እንደቆየች ቢታወቅም ፣ መንግሥቱን ለዘለቄታው ለሚመራ ማስተላለፍ ግድ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሁለት ዐበይት ችግሮች ተከሰቱ፡፡ እነሱም አንደኛ ልጆቹ የብፅዓት ልጆች በመሆናቸው ቤተ መቅደስ መግባታቸው፣ ሁለተኛ የንጉሥ ልጅ ይሾም ቢባልም ልጆቹ በአንድ ጊዜ የተወለዱ መንትያዎች በመሆናቸው ለማንኛቸው መስጠት እንደሚቻል አሳሳቢና አስቸጋሪ ጉዳይ መስሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰው የሚቸገረው እንደራሱ ፈቃድ እየተመራ በራሱ ውሳኔ ሲጓዝ እንጂ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን መፍትሔው ከእግዚአብሔር በመሆኑ ችግሩ ከባድ አልሆነም። በዚህ መሠረት ሕዝቡ ሊቀ ካህናቱን ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት፡፡

ሊቀካህናቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ «የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ የአባቶቻችን አምላክ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ሆይ ሙሴን በደብረ ሲና፣ ሳሙኤልን በቤተ መቅደስ እንደተነጋገርካቸው ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ፤ ፊትህንም ከእኔ አትመልስ ፈቃድህን የሚነግረኝን ደገኛውን መልአክህን ላክልኝ» ብሎ ጸለየ፡፡

እግዚአብሔርም ልመናውን ሰማና መልአኩ ሚካኤልን ላከለት እንዲህም አለው፥ «እግዚአብሔር እነዚህ ሁለቱን ልጆች አንግሥ፤ ሁለቱንም በአንድ መንበር አስቀምጣቸው ብሎሃል፡፡» ልጆቹ ግን እኛስ ለእግዚአብሔር የብፅዓት ልጆች ሁነን ተሰጥተናልና መንገሥ አይገባንም፤ ሌላ ንጉሥ ፈልጉ አሉ፡፡ ሕዝቡም እጅግ አዘነ፡፡

ነገር ግን ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ስለነበር መልአኩ መጥቶ ፥ «በዘመናችሁ ብዙ ሥራ ይሠራ ዘንድ አለውና፣ በእጃችሁም አብያተ ክርስትያናት ይታነጻሉና እሺ በእጄ በሉ፤ የሊቀካህናቱንም ቃል ስሙ» አላቸው፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አሉ፡፡ ሥርዓተ ንግሥናቸውም በታላቅ ክብርና ሥርዓት ተፈጽሞላቸው ሥመ መንግሥታቸውም ኢዛና እና ሳይዛና ተብሎ ነገሡ ፡፡ በአንድ መንበር ሁለቱም እንደ አንድ ሰው ሁነው ነገሡ ፡፡ በሚያስደስትና በሚያስደንቅ ፍቅር ኢትዮጵያን መምራት ጀመሩ፡፡በክፋት የተነሳባቸውን ጠላት አልተበቀሉም፡፡ በዘመናቸው ፍትሕ አልተጓደለም ፤ ድሀ አልተበደለም ፤ እንደ ነገሥታት ሥርዓት በቤታቸው በር ዘብ አላቆሙም ፤ በገፊና በተገፊ ይፈርዱ ዘንድ በአደባባይ ይቀመጡ ነበር እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ በዘመናቸው የታወቀች ሆነች /የኢዛና አገር ተብላ/ ዜናቸውም በየአህጉሩ ሁሉ ተሰማ፡፡ በዘመናቸውም አመፀኛ ቀማኛ አልነበረም፡፡ ነገርግን ወጣቶቹ ነገሥታት አንድ ነገር ያስጨንቃቸው ነበር ፤ ይህን ጭንቀታቸውንም ለሊቀካህኑ እንዲህ ብለው ነገሩት ፥ «እኛን የሚያስጨንቀን ስለመንግሥታችን አይደለም፤ ስለጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው እንጂ፡፡» እርሱም «ጌቶች ይህስ ምስጢር ለእኔም ድንቅ ነው» አላቸው፡፡ ነገር ግን በአልዓሜዳ የመጣ ፍሬምናጦስ የሚባል አንድ ሰው እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች ግዝረትና እምነት አላችሁ ጥምቀትና ቍርባን ግን የላችሁም እያለ ይናገራል አላቸው፡፡

እነርሱም ፍሬምናጦስን አስጠርተው ስለነገረ ትስብእቱ ምስጢር እንዲያስረዳቸው ጠየቁት። እርሱም ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው/ተመርተው/ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ይወለዳል ካሉበት ጀምሮ የልደቱን፣ የጥምቀቱን፣ የትምህርቱን፣ የስቅለቱን፣ የሞቱን፣ የትንሣኤውንና የዕርገቱን ምስጢር በሚገባ አስተማራቸው፡፡ ሐዋርያትም በጌታ ተሾመው ዓለምን ዙረው ማስተማራቸውን ተረከላቸው፡፡ እነርሱም ፍሬምናጦስን ይህን ሥርዓት በሀገራችን እንድታስፋፋ አሉት፡፡ እርሱም በወቅቱ ሥልጣነ ክህነት አልነበረውምና ይህን ሥራ ለመሥራት ሥልጣነ ክህነት ያስፈልጋል አላቸው፡፡

ነገሥታቱም ወደ እስክንድርያው ፓትርያርክ እርሱን እንዲሾምላቸው እና ሀገራቸውንም ተዘዋውሮ እንዲያስተምርላቸው ደብዳቤ ጽፈው ፣ገጸበረከትም በማስያዝ ፍሬምናጦስን ከብዙ ሊቃውንት ጋር ላኩት፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ እጅግ ተደስቶ ፍሬምናጦስን አቡነ ሰላማ በማለት ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ ሰደደው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ለአቡነ ሰላማና አብረውት ለነበሩት ሊቃውንት መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና የሥርዓተ ቤተ ክርስትያን መጻሕፍትን እንዲሁም ሌሎች ንዋያተ ቅዱሳትን አስይዞ ለነገሥታቱ ደብዳቤ ጽፎ ከብዙ ገጸ በረከት ጋር በታላቅ ክብር ሸኛቸው፡፡

አቡነ ሰላማ ከቅዱስ አትናቴዎስ የተላከውን ደብዳቤ ለነገሥታቱ ካቀረበና የጉዞውን ነገር ሁሉ ካስረዳ በኋላ የማጥመቅ ሥራውን ቀጠለ፡፡ ከሁሉ በፊትም ነገሥታቱ ተጠመቁ ፤ ኢዛና አብርሃ፣ ሳይዛናም አጽብሐ ተባሉ፡፡ ቀጥሎም ሠራዊቱና ሕዝቡ ሁሉ ተጠመቁ፡፡ ሥርዓተ ቍርባንም ድንኳን አስተክለው ተፈጸመላቸው፡፡

አብርሃ ወአጽብሐ በአክሱምና በአካባቢው ሕዝቡን አስተምረው ካጠመቁ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት ጋር ተገልጾ በተራራው ላይ / አሁን መከየደ እግዚእ ተብሎ በሚጠራው ቦታ/ ቆሞ ታያቸውና በዚህ ቦታ ቤተክርስትያን ስሩልኝ አላቸው፡፡ ነገር ግን ቦታው የውኃ መከማቻ ባሕር ስለነበር ከየት እንስራ አሉት፡፡ ጌታችንም ከገነት ትንሽ አፈር አምጥቶ በውኃው ላይ በተነ፡፡ ያችም ባሕር እንደ በረሃ ደረቅ ሆነች፤ ጌታችንም ቤተክርስትያኔን ከዚህ ቦታ ሥሩ ብሎ አዝዟቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ነገሥታቱም የቤተ መቅደስ ሥራ ወደ ሚችሉት ወደ ጢሮስ ንጉሥ የኪራምን ልጆች እንዲልክላቸውና እንዲያንጹላቸው ከብዙ ወርቅና ገንዘብ ጭምር ደብዳቤ ላኩ፡፡ በዛም ወራት የግሪክ ጥበበኞችና የጢሮስ ብልሃተኞች መጡ፡፡ የጠቢባኑም ቁጥር ሃያ አራት ነበር፡፡ እነርሱም 12 የግሪክ/ፅርዕ/ጥበበኞች፣ 12 የኪራም የልጅ ልጆች የሆኑ የጢሮስ ብልሃተኞች ነበሩ፡፡ ጠቢባኑም በየምድባቸው በአንዲት ቦታ የ12 ቤተ መቅደስ መሠረት ጀመሩ፡፡ መሠረቱን ሲያከናውኑ ጌታችን ለነገሥታቱ ታያቸው ፤እነርሱም ባዩት ጊዜ ሰገዱለት፡፡ ይቺ የምታሰሯት ቤተ መቅደስ እንደ ኢየሩሳሌም ያለች ሰማያዊ ናት ብሎም ባርኳቸው ተሰወረ፡፡

ይህ ቤተ መቅደስ ስራው ሁሉ በግሩም ሁኔታ ተከናውኖ ለ600 ዓመታት አገልግሎ ት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአንበሳ ውድም ዘመነ መንግሥት እርሱን ድል ነስታ 40 ዓመታት በነገሠችው በዮዲት ጉዲት ተቃጥሏል፡፡

አብርሃና አጽብሐ በመላው ሀገሪቱ እየተዘዋወሩ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከመፈጸማቸው በተጨማሪ 154 አብያተ ክርስትያናትን ያሳነጹ ሲሆን ከእነዚህም 44ቱ አስደናቂ ናቸው፡፡ ባለ44 ምሰሶ ከፍልፍል ድንጋይ የተሰሩ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ በገልአርታ የሚገኘው ሰው የማይከፍተው ሰው የማይዘጋው የቀመር አርባዕቱ እንስሳ ቤተክርስትያን ይገኝበታል፡፡ እነዚህ ጻድቃን ነገሥታት ሀገሪቱን ተከፋፍለው በወሎ፣ በሸዋ የየካ ሚካኤል / አዲስ አበባ/ ፣ በከፋ የብሐ ጊዮርጊስን፣ በሰላሌ የዋሻ ሚካኤልን፣ በጎጃም የዲማ ጊዮርጊስን፣ በጎንደር ስማዳ የጃን ሚካኤል ቤተ ክርስትያንን አሳንጸው እየተዘዋወሩ እያገለገሉ እንደነበር ታላቁ አብርሃ በ374 ዓም ጥቅምት 4 ቀን በዕለተ እሑድ ዐረፈና ተቀበረ፡፡ ወንድሙ አጽብሐ ደግሞ ጥቅምት 4 ቀን 379 ዓም ዐረፈ፡፡ሁለቱም ነገሥታት ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነበር፡፡ ዓመተ ምሕረቱ ግን ይለያያል፡፡ በሞቱም ጊዜ በመቃብራቸው ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ ታይቷል፡፡ እነዚህ ነገሥታት ለሀገራችን ብርሃንን የገለጹ ባለውለታዎቻችን ሲሆኑ የኦሪቱን ሥርዓት በሐዲስ ሥርዓት የለወጡ ቅዱሳን ናቸው፡፡

ጌታችንም ለእነዚህ ቅዱሳን ነገሥታት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ዝክራችሁን የዘከረ፣ ሥማችሁን የጠራ እምርላችኋለሁ፡፡ በስማችሁ ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ እኔ የሕይወት ውኃ አጠጣዋለሁ፡፡ በስማችሁ ለተራበ እንጀራ ያበላ እኔ የሕይወትን እንጀራ አበላዋለሁ፡፡ በስማችሁ ቤተ ክርስትያን ያሳነጸ በመንግሥተ ሰማያት ቤት እሰጠዋለሁ፡፡ በስማችሁ ማኅሌት የቆመ የመላእክትን ማኅሌት አሰማዋለሁ በማለት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡

የአብርሃ ወአጽብሐ ረድኤታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤አሜን!!!