«የአክለክሙ መዋእል ዘሃለፈ ፥ ያለፈው ዘመን ይብቃችኋል» ቅዱስ ያሬድ እና ፩ኛ ጴጥሮስ ፬ ፥ ፫- ፬

በመጋቢ ሀዲስ ምስጢረ ስላሴ ማናየ

ጳጉሜን  ፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. 

«የአክለክሙ መዋእል ዘሃለፈ ፥ ያለፈው ዘመን ይብቃችኋል» ቅዱስ ያሬድ እና ፩ኛ ጴጥሮስ ፬ ፥ ፫- ፬

በቅድሚያ ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ ያሸጋገረን፤ በመግቦቱ ያልተለየን፤ በችርነቱ የጠበቀን፤ በምህረት አይኖቹ የተመለከተን፤ በብርቱ ክንዶችሁ የደገፈን፤ የዘመናት ባለቤት የፈጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ለዚህ ኣመት ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ይድረሰው አሜን።

በቸር አድረን የምንውለው፤ ተኝተን የምንነሳው፤ ሰርተን የምናገኘው፤ ደክመን የምንበረታው፤ ታመን የምንደነው፤ ወድቀን የምንነሳው፤ ከቸርነቱ ከጠባቂነቱ የተነሳ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን ከድንጋይ እና ከእንጨት ለይቶ በደማዊት ነፍስ ከእንስሳት እና ከአራዊት ለይቶ በህያው ነፍስ አክብሯታል በአርያው እና በአምሳሉም ፈጥሯታል። «ወገብሮ እግዚአብሔር ለእጓለ እመህያው እመሬተ ምድር በአሪያሁ ወበአምሳሊሁ ፤ እግዚብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአርያውና በአምሳሉም ፈጠረው» ዘፍ ፩፥፪፮

የሚኖርበትን ምድርና የሚመገበውን ምግብ አዳምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ አዘጋጅቶ ለዘመናትም ልክ ይሆኑት ዘንድ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብትን፣ ረምትና በጋን፣ መዐልትና ሌሊትን ሰጠው። «እግዚአብሔርም አለ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ ለምልክቶች፣ ለዘመናት፣ ለእለታትም ለዓመታትም ይሁኑ» ዘፍ ፩።፩፬

እለታትን በብርሐን እና በጨለማ ለይቶ እለታትን በሳምንታት፣ ሳምንታትን በወራት፣ ወራትን በዓመታት ፣ዓመታትን በዘመናት ተክቶ ለሰው ልጅ ሰፍሮ ለክቶ ይጠቀምበት ዘንድ ሰጠው። ቀን ሳምንት ወር ዓመት የተሰጠው የሰው ልጅ ተግባረ ስጋውን ፤ ተግባረ ነፍሱን እንዲሰራበት ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ስጦታ ሁሉ ዘመን ትልቁ ስጦታ ነው። ዘመን ፀሐይ ነው ለሁሉ ያበራል፤ ዘመን የጨለመበትን ፀሐይ ሊያበራለት አይችልም ከዚህ የተነሳ የቀን ጨለማ ዋጠኝ ይላል። ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ካመለጠ፣ ካለፈ የማይመለስ ፤ ቆሞ የማይጠብቅ ፤ በባንክ የማይቀመጥ ፤በተሰጠንበት ጊዜ ብቻ ልንጠቀምበት የምንችል ልዩ ስጦታ ነው።

ዘመን ጎርፍ ነው፤ ጎርፍ ይዞት የማይመጣው የለም ዘመንም እንደዚሁ እድገትን፣ ስልጣኔን፣ እውቀትን፣ ትንሳኤን፣ ማግኘት፣ ማጣትን፣ መሾምን፣ መሻርን፣ መክበርን፣ መዋረድን ብዙ ነገርን ያመጣል። ክፉውን እየተው መልካሙን እየመረጡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚያበቃን ርስቱን ለመውረስ፤ ስሙን ለመቀደስ፤ ዘመን የሚያመጣውን ጊዜ የሚወልደውን ክፉ ነገር ለማለፍ በዘመን ሁሉ የሰው ልጅ መንገዱን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ አለበት። ዘመን ከተጠቀሙበት ይጠቅማል ካላወቁበት ግን ያጠፋል ።

በዘመን በንፍር ውሃ ሰዎች አልቀዋል ያወቁበት እነ ኖህ ተርፈዋል፤ ጊዜውን ተጠቅመው መርከብ ሰርተው፤ ትእዛዘ እግዚአብሔርን አክብረው። ዘፍ ፮፥፩ ፣ ዘፍ ፯፥፩ ፣ ዘፍ ፰፥፩ ሙሉውን ማንበቡ ለዚህ በቂ ነው። ለኖህም ለሰብአ ትካትም የተሰጣችው ዘመን እኩል ነው አጠቃቀማቸው ግን ይለያያል።

አሁን በዘመናችን ዘመን ለሁሉም እኩል ይሰጣል አዲስ ዘመን በመጣ ቁጥር የሰዎች አጠቃቀም ልዩ ልዩ ነው። አዲስ ዓመት ሲመጣ እንደ ሰብአ ትካት ለጭፈራ እና ለዳንኪራ የሚዘጋጁ አሉ፤ ለበደል ለኃጢያት የሚሰለፈውም በዚያው ልክ ነው። ዓለማችን ከትናንት ዛሬ እንደ ብረት ምጣድ እየተቀጣጠለች፤ በጦርነት በጥላቻ እየነደደች፤ ህዝቦቿ ሰላም እየናፈቃቸው ነው። ሰው በቁሙ እንደ በግ ተጎትቶ ሲታረድ በአይናችን አይተናል፤ በጆሮአችን ሰምተናል። ለዚህ ሁሉ ያበቃን በዘመን መጠቀም አለመቻላችን፤ ለንሰሐ ለፍቅር ለመልካም ስራ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ትእዛዙን ለማክበር የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ማሽቆልቆል ነው። ከዚህ ጊዜ ያደረስከኝ ከደዌ የፈወስከኝ ብሎ ፈጣሪውን ማመስገን የሚገባው ሰው ዘመኑን በከንቱ እያባከነው ይገኛል። «ህይወትን የሚወድ ሰው ማነው? በጎውንም ዘመን ለማየት የሚወድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምን አድርግ ሰላምን ተከተላትም» መዝ ፴፫፥፲፪

በዘመን የሰዶምና የገሞራ ሰዎች በእሳት ጋይተው ሞተዋል፤ ሎጥ በዛው ዘመን በከተማቸው እየኖረ ከእሳት ድኗል። ለምን ጻድቅ ነበርና። ዘመን አንድ ቢሆን ለሚጠቀምበት እና ለማይጠቀምበት ሁለት ገጽታ አለው። አዲስ ዘመን ሰለመጣ መደሰት መፈንደቅ ለንሰሐ ካልተጠቀምንበት ዋጋ ያጣል። ዘፍ ፩፱፥፩፪ – ፪፱

እስራአል በዘመን ለግብጽ ተገዝተዋል በዘመን ነጻ ወጥተዋል። ዘመን ለሁሉም ፍጡር ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው የባርነት ጊዜአቸውን አሳልፈው፤ ገዢዎቻቸውን ድል ነስተው፤ ባህር ተከፍሎላቸው፤ ደመና ተጋርዶላቸው እና መና ወርዶላቸው ጠላት ጠፍቶላቸው ንሴብሖ ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል።

ዘመን እግዚአብሔር ሳይቀር የቸርነቱን ስራ የሚቆጥርበት አደባባይ ነው «አቡየሂ አስከ ይእዜ ይገብር ወአነሂ ከማሑ እገብር ፤ አባቴ አስከ ዛሬ ይሰራል እኔም አሰራለው» ዮሐ ፭፥፩፯ የሰው ልጅም ያለ ዘመን ምንም ምን ሊሰራ አይችልም። ዘመንን የሰው ልጅ በወርቅ በብር በልዩ ልዩ አልማዝ ሊገዛው አይችልም። በዘመን ግን ሁሉንም የፈለጋችውን በመዳፉ ማስገባት፤ ገንዘብ ማድረግ ይችላል፤ ቢወድቅ ይነሳል፤ ቢያጣ ያገኝል፤ ጠላት ቢነሳበት በዘመን ያልፋሉ ።

ዘመን ከእግዚአብሔር በታች ከባለስልጣናት ሁሉ በላይ ፈራጅ እና ወሳኝ ነው። ሰዎች በዘመናቸው የወሰኑትን አና ያቀዱትን የሠሩትን፤ ፈላስፎች የተራቀቁበትን ዘመን ይሽረዋል። ሁሉም ፍጡራን እና ሥራዎቻቸው ሁሉ በዘመን ይተካሉ፤ በዘመን ያልፋሉ። ስለዚህ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ አዲስ ዓመት ይባላል። ሰው በንሰሐ ከኃጢአት ፤ ተግቶ በመሥራት ከስርቆት ከስንፍና የሚታደስበት፤ ጊዜው ያመጣለትን ሥራ ለመሥራት የሚፋጠንበት መሆን ይገባዋል። መባከን የለበትም ልዩ ስጦታ ነውና። ዘመን እንደ ነፋስ ፈጣን ነው፤ አንድ ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋበት ጥላ ነው። «ሰው ከንቱ ነገርን ዘመኑም ይመስላል ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል» መዝ ፩፬፫ ፥፬

«ሺ አመት በፊት እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና ዘመኖቹ የተናቁ ይሆናሉ። በማለዳም እንደሳር ያልፋል ማልዶ ያብባል ያልፋል በሰርክም ጠውልጎ እና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቁጣህ አልቀናል በመአትህም ደንግጠናል። በደላችንንም በፊትህ አስቀመጠህ ዘመናችን ሁሉ አልፏልና እኛም በመአትህ አልቀናልና ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። የዘመኖቻችን እድሜ ሰባ ዓመት ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው» መዝ ፰፱፥፫-፲

በዘመን ጥላ ስር የማያልፍ ማንም የለም ሰው ይቅርና ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት በስጋ ዘመን ተቆጥሮለታል፤ ፴ አመት ሆነው ተብሎ። ሰው ሁሉ በዘመን ማህጸን ይጸነሳል ይወለዳል ያድጋል፤ የተወሰኑለትን ዘመን ተጠቅሞ ፈጣሪውን ቢያገለግል ዘመን የማይሽረው ጊዜ የማይለውጠው ክብር ያገኛል። ማለት መንግስተ ሰማያት ይገባል፤ ካገኙ ማጣት ከገቡ መውጣት የሌለበት ህይወት መላእክትን መስሎ ይኖራል። በእርግጥ ጥንተ ዘመን የሌለዉ ኋላም ዘመኖቹ የማያልቁበት የማይለውጡት እግዚያብሔር ብቻ ዘመናት በርሱ ይወጣሉ በርሱ ያልፋል እርሱ ግን ለማይቆጠሩ ዓመታት እና ዘመናት ይኖራል። «የዘመኔን አነስተኝነት ንገረኝ፤ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሰረትክ ሰማያትም የጅህ ስራ ናቸው፤ አነርሱ ያልፋሉ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው አንደ ልብስ ያረጃሉ አንደ መጎናጸፊያ ትለውጣቸዋለህ።  አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ አመቶችህም ከቶ አያልፉም።» ዝ ፻፩፤፪፬-፪፰

ዘመን ከውቂያኖስ ይልቅ እጅግ ሰፊ ነው። በውቂያኖስ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት የበለጡ አና የበዙ ፍጥረታት በዘመን ውስጥ ይኖራል። ዘመን ከእግዚያብሔር በታች ለሁሉም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ነው ጥበበኛው ሰሎሞን አንዲህ ያለው «ለሁሉ ዘመን አለው ከሰማይ በታች ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለዉ» መክ ፫፤፩

ከዚህ የተነሳ የሰው ልጅ የተሰጠዉን ጊዜ በዋዛ በፈዛዛ ከማሳለፍ የተነሳ ተዘጋጅቶ ዕለተ ሞትን አያሰበ እግዚያብሔርን እያከበረ ሊኖር ይገባዋል። በከቱ ያሳለፋቸው ዘመናት ይበቃሉ። ቅዱስ ጴጥሮስ «ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ» ያለው ዘመኖቹ ክፎዎች ናቸውና ሰው እራሱን መጠበቅ አለበት። «መንፈስ ግን በግልጽ በኋላኛው ዘመናት አንዳንድ የሚያስቱ መናፍስትና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያዳመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ።» ፩ጢሞ ፬፥፩-፫

«ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን አንዲመጣ እወቅ ሰዎች እራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ።  ገንዘብ የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትእቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመስግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ እርቅን የማይሰሙ፣ እራሳቸውን የማይገዙ፣ ሃሜተኞች፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ ይሆናል። »፩ጢሞ፫፥፩-፱

እነዚህ በሙሉ አሁን ያለንበትን ዘመን የሚያምለክቱ ናቸው። ሰው ሁሉ በእነዚህ እንደ ብራና ተወጥሯል፤ ሟች መሆኑን ረስቷል፤ ኃጢያት ሠርቶ አይጠግብም ።«ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ»

«ወይእዜኒ በጽሃ ጊዜሁ ለነቂህ እምነዋም ኀለፈት ሌሊት ወመጽአት መዓልት ወንግድፍ እምላእሌነ ምግባረ ጽልመት ወንልበስ ወልታ ብርሃን ከመናንሰሉ በምግባረ ፅድቅ፤ ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቧል፤ ሌሊት አልፏል፤ ቀኑ ቀርቧል፤ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃን ጋሻ ጦር እንልበስ፤ በቀን እንደምንሆን በአግባቡ እንመላለስ። በዘፈንና በስካር በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤ በክርክር እና በቅናት አይሁን»ሮሜ ፩፫፥፩፩

«ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ» በኃጢአት፣ በርኩሰት፣ በጠብ፣ በክርክር፣ በቂም፣ በቀል፣ በስካር ያለፈው ይብቃ። የተቀበልነው ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የብልፅግና የንስሐ ያድርግልን

«ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ»

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር ዘሃሎ በአርያም

ወለወላዲቱ ድንግል ማርያም

ወለመስቀሉ ክቡር ዕፀ ፍቅር ወሰላም

አሜን