“ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ” (መኃ 2፡10)
ዲ/ን ውብዓለም ደስታ
ከኔዘርላንድስ ቀጠና ማዕከል
ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ከመዝሙር ሁሉ በሚበልጥ መዝሙሩ ሰሎሞን እመቤታችንን እንዲህ ብሏታል፡፡ «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ÷ ዝናቡም አልፎ ሄደ ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ ÷ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡» (መኃ.2-10-14)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምስጢራዊ ነገሮችን ያቀፈ ነው፡፡ «በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዎች ናቸው፡፡ የመከራሽ ጊዜ አልፏል ሲላት «አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ማለቱ ከልጅሽ እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረው ወንጌልን የተቀበሉ ሐዋርያት አንቺን በእናትነት የተረከቡ የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ሁሉ መሰማቱን ያጠይቃል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን «የዜማ ጊዜ ደረሰ» ያለው የመከሩን ወቅት ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ እንደመኖኑ ሐዋርያት የዘሩት ዘር /የሐዋርያት ስብከት/ ፍሬ አፈራ ክርስቲያኖች በዙ፤ «በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሐዋርያት ስብከት ተምረው ምግባር መሥራት ጀመሩ፤ «ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል» በመላው ዓለም ያሉ ምዕመናን በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ መስጠት ጀመሩ፤ በሚል ምስጢራዊ ትንታኔ ይተረጉሙታል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ወደጄ ሆይ ተነሽ እያለ የሚናገረው ተወዳጁ ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያምን በመለኮታዊ ስልጣኑ ከሙታን ለይቶ ማስነሣቱን ሲያስረዳን ነው።
ስለዚህ ድንቅ ምስጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ተንሥዕ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ፤ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› መዝ 131፡8፤ ብሎ የተናገረው ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍትና ትንሳኤ እንዲሁም ፍልሰት (ዕርገት) ከማሳየቱም በተጨማሪ የአምላክ እናት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብር መኖሯንም በግልጽ ያስረዳል ያስገነዝባልም፡፡
‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች››(መዝ 44፥9) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ትንቢታዊ ቃል የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መተርጉማን ‹‹ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና›› ተሸልማና አጊጣ በሰማያዊው ዓለም በልጇ መንግሥት በክብር መኖሯን የሚያመለክት መሆኑን አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሰማያዊው አባታቸውን እግዚአብሔርን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት፤ በሰማያት የምትኖር አባታችን›› እያሉ ዘወትር ሲያመሰግኑ፤ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊት እናታቸውን ድንግል ማርያምን ‹‹በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ›› እያሉ ዘወትር ያከብሯታል ያመሰግኗታልም፡፡ (ሉቃ 1፡28) ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዘወትር በምንጸልየው የእሑድ የእመቤታችን ውዳሴ ላይ ‹‹ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ የሆንሽ ድንግል ሆይ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልኝ ዘንድ ለአንቺ ይገባል፡፡ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከቅዱሳን ነቢያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት ከሰብዓ አርድእትም ትበልጫለሽ፡፡ ዳግመኛም ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችንም ሕይወትን፣ ድኅነትን የምትለምኚና የምታማልጅን አንቺ ነሽ›› በማለት የእመቤታቸን ልዕልናዋን የጸጋዋን ፍጹምነትና የክብሯን ታላቅነት በአጽንኦት ገልጾ መስክሯል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ድንግል ማርያም በዚህ ምድር በሕይወተ ሥጋ ሦስት ዓመት ከእናት አባቷ ቤት፣ አስራ ሁለት ዓመት በቤተመቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን ፀንሳ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ አስራ አምስት ዓመት ከዮሐንስ ቤት በአጠቃላይ ስድሳ አራት (64) ዓመታት ያህል ቆይታ በክብር አርፋለች፡፡ እመቤታችን ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ(21) ቀን በ50 ዓ.ም ገደማ ነው፡
ቅዱሳን ሐዋርያት በፈቃደ እግዚአብሔር ከያሉበት መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የፈጣሪያችን እናት ድንግል ማርያምን በጸሎትና በማዕጠንት አክብረው ገንዘው ጥልቅ በሆነ ኃዘን ሊቀብሯት ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል»በሚል የክፋት ምክር ተነሳሱ፡፡ በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኮል ከተነሳሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ አማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችው የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ፡፡ በዚህን ጊዜ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን (2ኛ ሳሙኤል 6፡6 ፤ 1ኛ ዜና መዋልዕ 13፡7-10) ላይ የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ እጁን በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ታውፋንያንም ሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጆቹን ቀጣው ቆረጠው፤ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም፤ (1ሳሙ 26፡ 9) እንደተባለ፤ እጆቹም አልጋ/አጎበር/ ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያም ስለተቆረጡት እጆቹ ወደ እመቤታችን አምኖ ወደ እሷ ቢጮህ ቢማጸናት፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካይኝነት እጆቹን እንደ ቀድሞ ሆነው ድነውለታል፡፡ በጌታችን ትእዛዝ መልአኩ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥጋ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮ ሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር አኑሮታል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ዮሐንስ ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን እንደምን አለች? አሉት፡፡ ዮሐንስም «ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ/መግቢያ/ ጾም ጀመሩ፡፡ ጥር አርፋ በነሐሴ ወር ሁለት ሱባኤ ይዘው ሲጨርሱ በነሐሴ 14 መልአኩ ቅዱስ ሥጋዋን ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸው በጸሎትና በምሕላ ቀብረዋታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም ፡፡ በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት አዝኖ፣ ‹‹በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ‹‹ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ›› ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡ ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ሌላ እንዳላየ ነገራው ለምስክር እንዲሆነው ሰበኗን/መግነዝ ሰጥታው ዐረገች፡፡ ቶማስ ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ምስጢሩን ደብቆ ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› አላቸው፤ሐዋርያትም “አንተ ተጠራጣሪ ነህ” ብለው መቃብሩን ሊያሳዩት ሲከፍቱ አጧት፡፡በዚህ ጊዜ እመቤታችን ተነስታ አርጋለች ብሎ ሁኔታውን ተረከላቸው፤ ለምስክር ይሁንህ ብላ የሰጠቸውንም ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን አይተው ትንሣኤዋን አመኑ። ሰበኗን ቆራርጠው ለበረከት ተከፋፍለው ወደየሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል፡፡ ዛሬም በመጾር መስቀልና በካህናት እጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሯት ‹‹መሀረብ›› የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱ ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አሳርጎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቅዳሴ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገቷን በዓይናቸው አይተውና በሚገባ ተረድተው ዓለምን ዙረው አስተምረዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያናችን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ ሕጻናቱ የእመቤታችን ፍቅር ስቧቸው ጹመው ይቆርባሉ ፡፡ ብዙ ምዕመናንም ቤታቸውን እየዘጉ በገዳማትና በየአጥቢያ ባሉ የቤተክርስቲያን መቃብር ቤቶች ሱባዔ ገብተው በጾምና በጸሎት እየተጉ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል ሱባኤውን ያሳልፋሉ።የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም በረከትና ምልጃ ከሁላችን ጋር ይሁን፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡