አቡነ መብዓ ጽዮን (በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን)
ጥቅምት ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም
መብዓ ጽዮን በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታቸው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። የንቡረ እድ ሳሙኤል ረባን የሆነው መብዓ ጽዮን አባቱ እስከ ዳዊት ያለውን ትምህርት አስተማረውና ዲቁናን ተቀበለ። ልጁ የትምህርት ዝንባሌ እንዳለው አባቱ ተረድቶ ቤተ ማርያም ከሚባለው ደብር ወስዶ ተክለ አማኅጸኖ ከሚባል የቅኔ መምህር ዘንድ አስገባው። በዚያም ቅኔና እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን እውቀቶችን ገበየ። ከዚህም በተጨማሪ ሥዕል መሳልና ጽሕፈት መጻፍ ተማረ። መብዓ ጽዮን የልጅነቱን ዘመን ሲፈጽም ‹‹ለነፍሳቸው ድኅነት ዋጋ ያገኙ ቅዱሳን ብዙ ናቸው።በመጾም ያገኙ አሉ፤ በትምህርት ያገኙ አሉ፤ በድካም ያገኙ አሉ፤ በጸሎት በትጋት ያገኙ አሉ፤ እኔ ግን የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን የሞቱን መታሰቢያ ማድረግ ይገባኛል። በዚህም ፊቱን አያለሁ፤ እርሱ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ ‹‹የትንሣኤዬን መታሰቢያ ብታደርጉ የሞቴን መታሰቢያ አድርጉ›› ብሏልና›› በማለት ፍላጎቱ በምንኩስና በመኖር ፈጣሪን ማገልገል መሆኑን ለወላጆቹ ገለጸላቸው።
አባትና እናቱም ‹‹ፈጣሪህን ለማገልገል ኅሊናህ ከአሰበ እሺ ፤በጀ ደስተኛ ነን›› ብለው ፈቀዱለት። ከዚያም መብዓ ጽዮን ዳሞት አባ ገብረክርስቶስ ወደሚባል መነኩሴ በመሄድ መነኮሰ። አባ መብዓ ጽዮን አባ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀመጥ ሥርዓተ ምንኩስናን ካጠኑ በኋላ ከአባ ገብርኤል ዘንድ ሄደው የቅስናን ማእረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ በአበው ሕግ በምንኩስና ተወስነው ፤በበአታቸው ሆነው ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፤ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ብለው በጸልዩ ጊዜ ‹‹መከራ መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም ‹‹አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ›› ሲሉ ለጌታቸው መለሱለት። ያን ጊዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተተከለ። በመስቀሉ ላይም እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ ፤በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር።
እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ጌታችን ለአባ መብዓ ጽዮንም ታያቸው። ከዚህም በኋላ አባ መብዓ ጽዮን የጌታችን የመድኃኔዓለምን ሕማሙን፣ መከራውን፣ ግርፋቱን፣ እስራቱን በጠቅላላ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ ፤ራሳቸውንም በዘንግ ይመቱ ነበር። የጌታን መከራ መስቀል እያሰቡ ዐይኖቻቸው አስከሚጠፉ ድረስ ያለቅሱ ነበር ። ጌታችን ግንደ መስቀሉን (የመስቀሉን ግንድ) አንደተሸከመ በማሰብ ትልቅ ድንግያ ተሸክመው ይሰግዱ ነበር። መራራ ሐሞት መጠጣቱን በማሰብ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። የጌታ ደቀመዝሙር ዮሐንስ ወንጌላዊ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ አብሮ ስለነበርና ዐይን በዐይን ስለተመለከተ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል እያሰበ ፸ ዘመን ፊቱን በሐዘን ቋጥሮ እንደኖረ ሁሉ ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የጌታችንን መከራ መስቀል እያሰቡ ከዓለም ተድላና ደስታ ተለይተው በትምህርት ፣ በትሩፋት ፣ በገድል ጸንተው ኖረዋል። ጻድቁ መብዓ ጽዮን በሕይወተ ሥጋ ዘመናቸው የላመ የጣመ እንዳልተመገቡ፤በፈረስ በበቅሎ እንዳልሄዱ፤አልጋ ላይ እንዳልተኙ፤ገድላቸው ያስረዳል። የክርስትናን ትምህርት ለጋፋት ሰዎች እንዲስፋፋ ያደረጉት አባ መብዓ ጽዮን የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያነቡ ዐይኖቻችው ጠፍተው ነበር። ነገር ግን እመ ብዙኃን የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ወደኚህ ጻድቅ አባት በአት የብርሃን ጽዋ ይዛ መጥታ ዐይኖቻቸውን ቀብታ አድናቸዋለች። ከዚህ የተነሳ በትረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ አንደነበር ገድላቸው ያስረዳል።
የጻድቁ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ከመድኃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል። ጥቅምት ፳፯ ቀን ለወዳጆቹ እውነተኛውን ዋጋ የሚከፍል መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን ብዙ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው።
የአቡነ መብዓ ጽዮን ረድኤታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤አሜን!!!