«ትንቢት ይቀድሞ ለነገር ፤ ተግባርን (ድርጊት) ትንቢት ይቀድመዋል»

በዘመናት ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስክር ሆነው ሕይወታቸውን ከሰጡ ሰዎች መካከል ሠለስቱ ደቂቅ በዚህ ዘመን በተለይ ለወጣት ክርስቲያን ልጆች አርአያ ሆነው ይጠቀሳሉ። እግዚአብሔርም እራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው ስለእርሱ በመስጠት የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል ፤ ከእጅህም ያድነናል። ”(ዳን 316) በማለት እንደተናገሩት ትንቢት ፣ በቅጽበት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ተአምራቱን ገልጾላቸዋል። በእውነትም ይህ ታሪክ በተለይ በሃገራችን በታላቅ በዓል ታጅቦ መከበሩ እግዚአብሔርን በእውነት ላመኑ ፣ በሥሙም ለታመኑ ፣ ወደፊትም አምነው ለሚታመኑ ሁሉ ትልቅ ምስክር ነው ።

የቅዱስ ገብርኤል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

..ክ በ587 ዓመተ ኩነኔ ንጉሥ ናቡከደነጾር በባቢሎን አውራጃ በሐቅለ አደራን (በዱራ ዓዳ) ቁመቱ 60፣ወርዱ ደግሞ 6 ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል (ጣኦት) አሠርቶ አቆመ። ምስሉንም የሠራበት ምክንያት፡

1. ራሱ የወርቅ ተብሎ የተተረጎመልህ አንተ ነህ ብለው ክፉ አማካሪዎች በስህተት ስለመከሩት (ዳን 232)

2. ነቢዩ ዳንኤል የተረጎመውን ሕልም ንጉሡ አምኖ በመቀበሉ ምክንያት የባቢሎን ሕዝብ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ስላከበረውና ጣኦታቱን እየረሳቸው ስለመጣ ሕዝቡ በእስራኤል አምላክ እንዳይማረክ ስጋት ስለአደረበትና ጠቢባኑም ስለመከሩት ነው። ምስሉም የቆመው ከዛሬዋ ባግዳድ ከተማ ደቡባዊ ምዕራብ 27 .ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው “ቴልዴር” ከተማ እንደሆነ ጥናታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ንጉሡ የወርቁን ምስል ካሠራ በኋላ የባቢሎን ባለሥልጣናትና ሕዝቡ በሙሉ እንዲሰበሰቡና ለወርቁ ምስል እንዲሰግዱ እዛዝ ሰጠ ። ሠለስቱ ደቂቅም በትእዛዙ መሠረት ተገኝተዋል፤ እነርሱም ባለሥልጣናት ናቸውና ። የተገኙበት ዋናው ምክንያት ግን ፦

1. የአምልኮ ጣኦትን ከንቱነትና የእግዚአብሔርን ክብር ለመመስከር ።

2. በምርኮ ላሉት እስራኤላዊያን ፈርተውና ተታለው እንዳይሰግዱና በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ አርአያ ለመሆን ነው።

የሠለስቱ ደቂቅ እምነት እና ጽናት በዚህ ዘመን በሥልጣን ላይና በሥራ ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ስለሚገባው የእምነት አቋም የሚያሳይ ተግባር ነው። ለሥልጣን አድልተው እወደድ ብለው ክፉ በሚሠሩ የበላዮቻቸው ዘንድ እውነትን መመስከር እንደሚገባ ያስረዳል ። ጊዜና ሁኔታ አይቶ ከእምነትና ትክክለኛ ዓላማ መውጣት እንደማይገባ አርዓያ መሆን ከባለሥልጣናት ይጠበቃል ።

ናቡከደነጾር የተጠቀመው ስልት

የተሰበሰበው ሕዝብ በሙሉ ለወርቁ እንዲሰግድ ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሟል።

1. ከባለሥልጣናቱ እስከ ተራው ሕዝብ ያለው በአዋጁ መሠረት እንዲሰግድ አዋጅ ማወጁ ነው ፤ ይህም የሚያስገድድ ተግባር ነው።

2. የሕዝብን ልብ በሙዚቃ እያስደሰቱ ሳያስቡት በደስታ ስሜት ተውጠው እንዲሰግዱ ማድረግ ነው።

3. ወደ እሳት ጉድጓድ ትጣላላችሁ ብሎ በማስፈራራት እንዲሰግድ ማድረግ ነው። ዲያብሎስ ሰውን ከእግዚአብሔር ለመለየት እና የእርሱ ተገዢ ለማድረግ ሁሉንም ዓይነት መንገዶች ይጠቀማል ። የኃጢአትን መንገድ ያውጃል ፤ ማስታወቂያ ያስነግራል ፤ ወሬ ያስወራል ፤ በሰው ልቡና ይቀርጻል ፤ በመጠጥ፣ በአደንዛዠ እፆች፣ በዋዛና ፈዛዛ (በቀልድ) ያባብላል፤ ስሜትን ይቀሰቅሳል ፤ ያልታሰበ ኃጢአት ያሰራል። ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ ሀብትህን ፣ ሥልጣንህን ፣ ክብርህን ታጣለህ ፤ ኋላ ቀር ትሆናለህ ፤ ደሀ ትሆናለህ ፤ በማለት ያስፈራራል ።

ናቡከደነጾር በአስቀመጣቸው ስልቶች መሠረት አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፣ የመሰንቆውን ፣ የክራሩን ፣የበገናውን የዘፈኑንም ድምጽ በሰሙ ጊዜ ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።(ዳን 37)

የሠለስቱ ደቂቅ መከሰስ

ከለዳዊያን ናቡከደነጾር ያየውን ሕልም መተርጎም ስለአቃታቸው እንዲገደሉ ተወስኖባቸው ነበር። በንጉሡ ትእዛዝ ከመጣው ሞት ያዳኗቸው ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ ናቸው ።(ዳን 212) አሁን ግን ከለዳዊያን ሠለስቱ ደቂቅን ለሞት በታዘዘው አዋጅ ለማስገደል ነገር እየሠሩ ነው። “በባቢሎን አውራጃ ላይ የሾምሃቸው (ሲድራቅ ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ) የተባሉት አይሁድ ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል ፤አማልክትህን አያመልኩም ፤ ላቆምከው የወርቅ ምስልም አይሰግዱም”። በማለት ከሰሱአቸው። (ዳን 38-12)

የወጣቶቹ አለመስገድ ንጉሡን አስገርሞት ወጣቶቹን አስጠርቶ በፊቱ አቆመና ላቆምኩት ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም ብትሰግዱ መልካም ነው ባትሰግዱ ግን በሚነድደው እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? በማለት ተናገራቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ በሁሉም መንግስታዊ ሥራ ታዝዘው ሠርተዋል ፤ኃላፊነታቸውንም ተወጥተዋል። ከአምላካቸው የሚለያቸው ሁኔታ ሲመጣ ግን መደራደር አላስፈለጋቸውም። “የምናመልከው አምላካችን ያድነናል፤… ባያድነንም አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከው የወርቅ ምስል እንዳንሰግድ እወቅ፤ ናቡከደነጾር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም” (ዳን. 3)በማለት ሃይማኖታዊ አቋማቸውን፣ ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር በግልጽ አሳወቁት። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” እንዲል። (ሐዋ 529) አስቀድመውም ዝማሬ ሲፈልጉባቸው በባቢሎን ወንዝ አጠገብ የገቡትን ቃል ኪዳን አስታወሰው በአቋማቸው ጸኑ። (መዝ 1361-6)

ሠለስቱ ደቂቅ በጉድጓድ ውስጥ

የወጣቶቹን ንግግር ንጉሡ ሲሰማ ቁጣ ሞላበት፤ የፊቱም መልክ ተለወጠ ። አስቀድሞ ይነድ ከነበረውን ሰባት እጥፍ አድርገው እሳቱን እንዲያነድዱት አዘዘ ። ወደ እሳቱም እንዲጥሏቸው ከሠራዊቱ መካከል ኃያላኑን መርጦ እስከ ልብሳቸው እንዲጥሏቸው አደረገ።

ወጣቶቹ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህንም ሁሉ ይጨምርላችኋል። (ማቴ 633) የሚለው አምላካዊ ቃል በልቡናቸው በታማኝነት የተመሰከረላቸው ስለነበር አሁንም በጉድጓድ ውስጥ ሁነው ይጸልያሉ፤ ያመሰግናሉ።በምስጋናቸውም ውስጥ አምላክ ሰው በመሆኑ በዚህች ምድር 33 ዓመት እንደሚቆይ ተገልጾላቸው ምስጋናቸውን በዚያው መጠን አደረጉት። ነበልባሉም ሌሎች ማቀጣጠያ ተጨምረው ከጉድጓዱ 49 ክንድ ወደ ላይ ከፍ አለ። በዚህም ከ490 ዓመታት በኋላ አምላክ ሰው በመሆን ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ ክብር ይግባውና ምሳሌውን አሳያቸው። በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲህ ይገኛል።

ቅዱስ ገብርኤል ከወጣቶቹ ጋር

ሃይማኖት ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል። ማመንና መታመን፣ መወሰን፣ መቁረጥና ማድረግ ። ሦስቱ ነገሮች ከተስማሙና ከተፈጸሙ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየንም። ወጣቶቹ ይህን በማድረጋቸው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እሳቱ ምድጃ ወርዶ በጉድጓድ ውስጥ ያለውን የእሳቱን ነበልባል እንደቀዘቀዘ ነፋስ አደረገው ።

ሠለስቱ ደቂቅንም እሳቱ ምንም አልነካቸውም ፤ የራሳቸውንም ጸጉር አልለበለባቸውም ። የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል ። (መዝ 33 7) አንድ መልአክ ነው ፤ ግን ብዙዎችን ይጠብቃል፤ ብዙዎችን ያድናል። ናቡከደነጾር ታስረው ወደ ጉድጓድ የተጣሉትን እሳት ሳይነካቸው፣ የከሰሱአቸውንና አብረው የጣሏቸውን የእሳቱ ወላፈን ሲገድላቸው ተደነቀ፤ ፈጥኖ ተነሣና አማካሪዎቹን፦ ሦስት ሰዎች አስረን ጥለን አልነበረምን? እነሆ! የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ። የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል አለ ። እግዚአብሔርንም እንዲህ ብሎ አመሰገነ ። መልአኩን የላከ ፣ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም እንዳያመልኩ ፣ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን፣ በእርሱም የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ። እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና ….” (ዳን. 3)በማለት ሠለስቱ ደቂቅን ከፍ ከፍ አደረጋቸው።

የተከበራችሁ ምእመናን ታኀሣሥ 19 ቀን የቅዱስ ገብርኤልን በዓል የምናከብርበት ምክንያታችን ይህ ነው።

ከዚህ በኋላ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን በቅዱስ ገብርኤል ሥም ከታነጹት አብያተክርስቲያናት መካከል በአቢይነት የሚጠቀሰውን የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ታሪክ እንገልጻለን ። ስለዚህም ቤተክርስቲያን ገናና መሆን አስቀድሞ በመንፈሣዊ አባቶች ትንቢት ተነግሮ ነበር።

መዝሙረኛው ዳዊት ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው (መዝ118126) በማለት እንደተናገረው አንድ ሥራ ከመሰራቱ በፊት መቼ እንደሚሠራና እንዴት እንደሚሠራ በሰው ልብ ይታሰባል ፤ ይታቀዳል ። በሰው ዘንድ የታሰበውና የታቀደው እግዚአብሔር ካልፈቀደ ሳይፈጸም ይቀራል። ለዚህም ነው “የልብ ዝግጅት ከሰው ነው የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ነው ተብሎ የተነገረው ፤ ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈጽማል” እንዲሉ ።የሰውን አሳብ ለሰው ትተን ስለ እግዚአብሔር አሳብ ስንናገር እግዚአብሔር በልብ የመከረውን ፣ በቃል ያስነገረውን እርሱ በወደደና በፈቀደ ጊዜ ያከናውናል። ይህንንም የሚከለክልና የሚቃወም ማንም ፍጥረት የለም።በዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያነት ከዮዲት ጉዲት መውደቅ በኋላ የተነገረው ትንቢት ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን መፈፀሙን ስናስተውል እግዚአብሔር ሥራው ግሩም ድንቅ ነው ከማለት በስተቀር ሌላ ምን ማለት እንችላለን?

ደብረ ኃይል ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 461 .ሜ ርቀት ላይ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ውስጥ ነው።

ትንቢት ፦ በ9ኛው መቶ ክ/ዘመን (842-892 ..) ዮዲት ጉዲት በጠላትነት ተነሳስታ አብያተ ክርስቲያናትን ስትደመስስ ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ስታቃጥል ፣ ንዋየተ ቅድሳትን ስትዘርፍ በዘመኑ የነበረው ሕፃኑ የአክሱም ንጉሥ አንበሳ ውድም በአክሱም አካባቢ የነበሩትን ታቦታትና ንዋየተ ቅድሳት በመያዝ ወደ ደቡብ ኢትዮጲያ (አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ትገኛለች) ዝዋይ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

40 ዓመት የስደት ቆይታ በኋላ አንበሳ ውድም ወደ አክሱም ተመልሶ የንዋያተ ቅድሳት ቆጠራ ሲደረግ በቅዱስ ገብርኤል የተሰየመው የቃል ኪዳኑ ታቦት በዝዋይ መቅረቱ ታወቀ።የቀረበትም ምክንያት ንጉሡ ከአክሱም ያመጣቸውን ታቦታት እንዲመልሱ ትእዛዝ ሲሰጥ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት በፈቃደ እግዚአብሔር ከተቀመጠበት መነሳት ባለመቻሉ ነው።

ንጉሡም አባ ሌዊ በተባሉ አባት የሚመራ ልዑክ በመመደብ ታቦቱን እንዲያመጡ ወደ ዝዋይ ደሴት መልሶ ላካቸው። አባ ሌዊ ዝዋይ ደርሰው የሰባት ቀናት ሱባኤ ካደረጉ በኋላ የቅዱስ ገብርኤልን ታቦት ይዘው ወደ አክሱም ለመመለስ ጉዞ ሲጀምሩ መልአኩ ገብርኤል ተገልጦ እኔ ወደማሳይህ ቦታ ይዘህ ትሄዳለህ በማለት ትእዛዝ ሰጣቸው።

አባ ሌዊም በቅዱስ ገብርኤል እየተመሩ የዛሬው ምሥራቅ ሐረርጌ ቁልቢ የተባለው ቦታ ደረሱ ። አባ ሌዊ ታቦቱን ከዚህ ሥፍራ ማኖር እንዳለባቸው፣እርሳቸውም በዚህ ቦታ እንደሚያርፉ ፣በኋለኛው ዘመን በዚህ ቦታ ድንቅ ሥራ (ገቢረ ተአምር)እንደሚደረግ ፣ቤተ ክርስቲያንም በስሙ እንደሚሠራ መልአኩ ነግሯቸው ተሰወረ። ሰብአ ሰገልን ይመራ የነበረው ኮከብ (መልአክ) ቤተልሔም ዋሻ ሲደርሱ እንደተሰወረባቸው።

ዕረፍት ፦ አባ ሌዊ ከ130 ዓመታት ዕድሜ በኋላ በንጉሥ ግርማ ሥዩም ዘመነ መንግሥት (1070-1084..) ታኀሣሥ 14 ቀን በክብር ዐርፈዋል። የቅዱሳን ሞታቸው ሕይወታቸው፣ዕረፍታቸውም በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነውና (መዝ 1156)እንዲል ። በረከታቸው ይደርብን።

አመሠራረት፦ ከ16ተኛው እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በምሥራቁ የአገራችን ክፍል የነበረው አስተዳደር ሰላም የጠፋበት፣ኢአማንያን የበዙበት፣ ክርስቲያኖች በቁጥር እጅግ ያነሱበት፣ ስብከተ ወንጌል የተዳከመበት እንደነበር የሚታወቅ እውነት ነው። በመሆኑም በዚህ አካባቢ ስብከተ ወንጌል ማስፋፋት ፣ አብያተ ክርስቲያናትን መትከል የማይቻልበት ሁኔታ ነበር።

18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ግን ታሪክ ተለውጦ የአካባቢው ሰላም አስተማማኝ እየሆነ በመምጣቱ በርከት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት እየተተከሉ መንፈሳዊ አገልግሎቱና የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴም ውጤታማ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳምም የተተከለው በዚህ ዘመን ነው ። ስለ አተካከሉም ሁለት ዓይነት ታሪኮች ይነገራሉ። 1. ግራኝ አህመድ ኢትዮጵያን በወረረና ወደ ሰሜን በገሠገሠ ጊዜ በአንጻሩ ደግሞ በሰሜን አካባቢ ምናልባትም ከደቡብ ጎንደር ታቦታትን ፣ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን ይዘው የተሰደዱ ካህናት በእግዚአብሔር ፈቃድ ቁልቢ የተባለው ቦታ ይደርሳሉ የካህናቱም ስም፦

1. መልዓከ ገነት መብረቁ

2. መምህር የማነ አበበ

3. አባ ተከስተ ሥችስ ይባላሉ ።

እነዚህ አባቶች ቁልቢ ገብርኤል ደርሰው ቦታውን ሲጎበኙ ከተነጠፈ ድንጋይ ላይ ጽሑፍ ያገኛሉ።ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል በስውር ቦታ መቀመጡን፣ልዩ ልዩ ተአምራት እንደሚፈጸምበት፣ ወደፊትም ታላቅ ቤተ መቅደስ እንደሚሠራ አባ ሌዊ ታቦቱን ወደ እዚህ እንዴት እንዳመጡ ጽሑፉ ይገልጻል። እነርሱም ይህንን ታሪክ ይዘውት በነበረው መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ኅደጉ ላይ (footnote) ጽፈው አስቀመጡ። ሲመለሱም ታቦቱን ይዘው ተመለሱ ፣ ከመጽሐፉ ጋርም በዝዋይ ደሴት አስቀመጡት።

የሐረር ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ መኮንን ከዝዋይ ደሴት መጽሐፈ ቀሌምንጦስ አስመጥተው ሲያነብቡ የቅዱስ ገብርኤልን ታሪክ በማግኘታቸው ቤተ ክርስቲያን በስሙ ለመመሥረት ተነሳሱ ። ልዑሉ በአካባቢው አየር ንብረት ተማርከው በቦታው ቤት ሠርተው መኖር ጀምረው ነበር። ቦታው ቤተክርስቲያን ከመሠራቱ በፊት የአካባቢው ሕዝብ ባለመግባባት የሚዋጋበት ቦታ ነበር ፤ በተጨማሪም የቦታው ስያሜ ሽንኩርትና ድንች ሌላም የእህል ዓይነት የሚመረትበት ስለ ነበር “ቁሉቢ” ተብሏል። ቁሉቢ ማለት በኦሮምኛ ሽንኩርት ማለት ነው።

ልዑሉ በአካባቢው ሰላም ካወረድህ በዚህ ቦታ በስምህ ቤተ ክርስቲያን አሠራለሁ ብለው ለቅዱስ ገብርኤል ተሳሉ። ስእለታቸው በመፈጸሙ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት የት እንደሚገኝ ሲያፈላልጉ ሰሜን ቡልጋ ውስጥ አገኙት። ካህናተ ሰማይ ከተባለ ቦታ አባ ዱባለ የተባሉ ካህን ያስቀመጡት ቅዱስ ገብርኤል መኖሩ ተነገራቸው ። ራስ መኮንን መልእክተኛ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ወደ ዓጼ ምኒልከ በመላክ ካስፈቀዱ በኋላ ካህናቱ ከነሠራዊታቸው ታቦቱን ተሸክመው የካቲት 20 ቀን 1879 .. ወደ ቁልቢ ጉዞ ጀምረው በመድረስ ፣ መቃኞ (ጊዜያዊ ማረፊያ) ቤት በማሰራት ሐምሌ 19 1884 .. ቅዳሴ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር አድርገዋል።በዚሁ ዕለት የዋናው ሕንፃ ቤተክርስቲያን መሠረት ተጥሎ ታኅሣሥ 19 1888 .. ሥራው ተጠናቅቆ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ተባርኮ ታቦቱ ገብቷል። ቦታውም የተገዛው በአካባቢው ከነበሩ ባላባቶች በ40 የቀንድ ከብት ነው።

2ኛው ልዑል ራስ መኮንን በአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ሲያስቡ ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ይተከል የሚለውን ለማወቅ በጾምና በጸሎት በሱባዔ በነበሩበት ወቅት ከአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳም ከተሰወሩ ቅዱሳን መካከል አንዱ በመገለጥ መተከል ያለበት ቅዱስ ገብርኤል መሆኑን ተናግረው ታቦቱም የሚገኘው ከላይ ስሙ በተጠቀሰው ቦታና በአባ ዱባለ እንደሆነ ተናግሮ ተሰወራቸው። የሚለው ነው ። (ፈለገ ጥበብ መጽሔት)

በአጠቃላይም ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን ስለ ቅዱስ ገብርኤል ታቦት አመጣጥ የሚያወሱ ታሪኮችን ለማያያዝ መጀመሪያ ከአክሱም ወደ ዝዋይ ፣ከዝዋይ ወደ ቁልቢ ዳግመኛም ከቁልቢ እንዴት ወደ ቡልጋ ተመልሶ እንደሄደ የሚተርክ ጽሑፍ ባናገኝም ታቦቱ በስውር (በእግዚአብሔር ጥበብ) ወደ ቡልጋ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ኋላ ተመልሶ ከቡልጋ ወደ ቁልቢ በልዑል ራስ መኮንን አማካኝነት እንደመጣ ግን መረጃው ይገልጻል ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታቦቱ በቁልቢ ይገኛል። (ለበለጠ መረጃ የቤተክርስቲያን መረጃዎች” (ዳንኤል ክብረት፣1999 ..) ይመልከቱ።

ትንቢትና ተግባር ፦ ከ1888-1954 .. ድረስ በጽድና በዝግባ ከተሰራ ቤተመቅደስ ሲገለገል ቆይቶ ስእለት ሰሚነቱ እየታወቀ ፣ ስሙ እየገነነ፣ተአምራቱ እየበዛ በመምጣቱ፣ የሕዝቡ ቁጥርም በመጨመሩና በጽድና በዝግባ የተሰራው ቤተ መቅደስ አነስተኛ በመሆኑ ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ታስቦ ከስእለት በተገኘው ገንዘብ ከ1954-1957 .. ባለው ጊዜ ውስጥ ለዓይናችን ድንቅ ሆኖ የሚታየው ሕንፃ በዘመናዊ ፕላን ተሠርቶ በተገቢው ሁኔታ በመጠናቀቁ ታቦተ ሕጉ ወደ አዲሱ ቤተ መቅደስ በሚገባበት ጊዜ ብፁዕወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ንጉሥ ዓጼ ኃይለ ሥላሴና ክቡራን ሚኒስትሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን ተገኝተዋል።

ቁልቢ ገብርኤል አሁን

በክብረ በዓሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ክርስትናን ያልተቀበሉ የውጪ አገር ዜጎችም ሁሉ ይታደማሉ። ስእለት ያለባቸውም ሆነ ሌሎች ምእመናን ከድሬዳዋ፣ ከሐረር፣ ከአሰበ ተፈሪ ጀምሮ የእግር ጉዞ ያደርጋሉ ። በተለይ የሐሮማያ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚያደርጉት የጋራ የእግር ጉዞ በእግርም በመኪናም የሚሄደውን ዓይን ይማርካል። ከ2000 .ም በፊት በገዳሙ ዙሪያ ሥጋዊ እንቅስቃሴ መብል ፣ መጠጥ ፣ጭፈራ እና ስርቆት እንደነበረ በቦታው የተገኘ ሰው የሚያስታውሰው እውነት ነው ። አሁን ግን እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ነገር ይቅርና ማንኛውም እንቅስቃሴ ሥርዓት እንዲይዝ ተደርጓል። መንፈሳዊ አገልግሎቱን በተመለከተ ፦

በየቀኑ የቅዳሴ ሥርዓት ይከናወናል።

የሠርክ ጉባኤ ይካሄዳል።

ገዳሙ ለጎብኚዎች ሁልጊዜ ክፍት ነው።

የካህናት ስልጠና ይካሄድበታል።

የአብነት መምህራን ይገኛሉ።

በአካባቢው ለሚኖረው ሕዝብ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ተሠርቶና መንግስት ተረክቦት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የእግዚአብሔርን ሕዝብ በቀንም በሌሊትም የሚያገለግል ፣ በእግዚአብሔር ፊት ለአማላጅነት ለተልዕኮ የሚቆም ቅዱስ ገብርኤል ሁላችንንም ይጠብቀን።

የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት አይለየን

አዘጋጅ መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ለይኩን ብርሃኑ

በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል መምህር

ምንጮች ፦

1) የቤተ ክርስቲያን መረጃዎ ፦ /ን ዳንኤል ክብረት ፡ ማኀበረ ቅዱሳን 1999 .ም ገጽ 203

2) ፈለገ ጥበብ መጽሔት ፦ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ፡ በየ3ወር የሚታተም ሐምሌና ነሐሴ 3ኛ ዓመት፣ቁጥር 91993 .ም ገጽ 33