ምኵራብ
በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን
መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ።“ይደልዎነ ንእምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመ ኵሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደኃራዊ መዋዕል” ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭ ብለን በማመን እንደ አባቶቻችን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ምኵራብ እንማራለን የምናነበውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።
የእስራኤል ልጆች መቅደስ(Temple) እና ምኵራብ የሚባሉ ሁለት መንፈሳዊ መገናኛዎች ነበሩአቸው፤ ምኵራብ [በጽርዕ (Synagogue/ συναγωγή)፡ በዕብራይስጥ (Beyth Kenesset/ בית כנסתይባላል። መቅደስ የሚባለው በኢየሩሳሌም ብቻ የሚገኝ ስለ ኃጢአት ስለ ምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት የብሉይ ኪዳን ማዕከል ነው። ምኵራብ የቦታ ወሰን የሌለው በየአቅራቢያው የሚገኝ አጥቢያ ቤተ ጸሎት ነው።የምኵራብ መታነፅ ከባቢልን ምርኮ (exile in Babylon 538 A.D.) ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው። በባቢሎን ምርኮ በባእድ ሀገር በዚያው ባሉበት ስርዓተ አምልኮ ለመፈፀም ዳግመኛም ይህ ሁሉ መከራ በአባቶቻችን የተደረገባቸው ቤተመቅደስን ባይሰሩ ነው እኛ ሚጠት የተደረገልን እንደሆነ ቤቱን እንሰራለን በሚል ዋናውን ቤተ መቅደስም ሆነ ብዙ ምኵራባት ሰርተዋል። 10 አባወራዎች ባሉበትም ምኵራብ እንዲሰራ ህጋቸው ያዝ ነበር። በምኵራብም የሚደረገው መንፈሳዊ አገልግልት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ማንበብ መስማትና መተርጎም ንዑሳን በዓላትንም ማክበር ነበር።ማንኛውም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ ለዐበይት በዓላት በኢየሩሳሌም መቅደስ ተገኝቶ አምልኮን መፈጸም ግዴታው ነበር። በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በንባብ በትርጓሜ ይሰማሉ።
በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ እንዳስተማረ ለመግለጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅደስ ያሬድ ማሕሌታዊ የዓቢይ ጾም ሦስተኛውን ሰንበት ምኵራብ ብሎ ሰይሞታል። ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡- “ ቦኦ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋት አበድር እመስዋዕት አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ . . .” ትርጓሜው፡- “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ። የሃይማኖትን ቃል አስተማረ። ከመሥዋዕትም ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው። የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷ እኔ ነኝ አላቸው የአባቴ ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል። ምኵራብ ገብቶ ተቆጣቸው ዝም ይሉ ዘንድ ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ፣ የነገሩን መወደድ፣ የአፉን ለዛ አደነቁ” በማለት ቅደስ ያሬድ ዘምሯል።
ቅዱስ ያሬድ በሰዓታት በወራት እና በዘመናት የተከፋፈሉ ድንቅ ምሥጢር የያዙ መዝሙራትን(ምስጋና) ከብሉያትና ከሐዲሳት ለቤተክርስቲያን እንደ ንብ ቀስሞ እንደ ሰምና ወርቅ አስማምቶ የአገልግሎት ሥርዓትን የሠራ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ነው።ለምኵራብ የሚሆነውንም ዝማሬ ከዮሐ 2፡12-25 ላይ ወስዶ አመስጥሮ እስማምቶ ጾመ ድጓ በተባለ መጽሐፉ አዘጋጅቶልናል። ይህንን የመጽሐፍ ክፍል እንደሚከተለው እናየዋለን።
ቁ.12 “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” ከቃና ዘገሊላው የዶኪማስ ቤት ሰርግ ውሃውን ወይን አድርጎ ታምራቱን ካሳየ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ከእናቱና ከወንድሞቹ ደቀመዛሙርት ጋር ሄደ በዚያም ጥቂት ቀን (11 ቀን ይላል በወንጌል አንድምታ) ተቀመጡ። ቁ.13 “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።” ይህም የመጀመሪያ ፋሲካ ነው ጌታ የተሰቀለው በአራተኛው ነው። በምስጢርም ኢየሩሳሌም ወጣ መባሉ ጌታ ከሕይወት ወደመስቀል ምእመናንም ወደ ሕይወት የሚሄዱበት ዘምን በደረሰ ጊዜ ጌታ ሐገረ ሰላም ኢየሩሳሌም ወደተባለ መስቀል ሄደ ማለት ነው። ቁ.14 “በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤” ለስም አጠራሩ የክብር ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ በተገኘ ጊዜ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ከሚነበበው እና ከሚተረጎመው ከሚፀለየውም ይልቅ የሚሸጠውና የሚለውጠው በዝቶ ተመለከተ። ውንብድና ቢሉ ፈሪሳዊያን የሚያንፀባርቅ እና የሚያንሽዋሻ ልብስ ለብሰው በውጭ ከብቱን ያስደነብሩና ወደምኵራብ ያስገቡታል ከዚያም ከል የገባ አይነጣም ቤተመቅደስ የገባ አይወጣም እያሉ የህዝቡን ገንዘብ ይቀሙታል።መለወጥ ቢሉ ህዝቡ መባ ሊያስገቡ ቀይ ወርቅ ይዘው ሲመጡ እግዚአብሔርማ የሚሻው ነጭ ወርቅ እንጅ ቀይ ወርቅ ነውን ይሉታል እነርሱም በትህትና እውነት ነው ብናጣ ነው እንጅ ለእግዚአብሔርማ ንፁህ ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት ቀይ ወርቅ ብታመጡ ባንድ ነጭ ወርቅ እንለውጣችኋለን እያሉ ይበዘብዟቸዋል።ከብቱን ከስቷል ጥፍሩ ዘርዝሯል ፀጉሩ አሯል ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይሏቸዋል እነርሱም በትህትና እውነት ነው በመንገድ ደክሞብን ከስቶብን እንጅ ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት የከሳ ከብት ብታመጡ ባንድ የሰባ እንለውጣችኋለን ይሏቸዋል መሸጥም ቢሉ የከሳውን ከብት አወፍረው አድልበው ይሸጡ ነበር
ቁ.15–16 “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡” በቤተ ፀሎት ይህን ያልተገባ ነገር ሲፈፅሙም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው ይላል ይህንም ጅራፍ ሐዋርያት አዘጋጅተው ሰጥተውታል የጭፍራውን ለአለቃው መስጠት ልማድ ንውና። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገበያውን ፈታ። ለሰውነታቸው ቤዛ የሚሆናቸው ስለሆነም የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ በትር አይችሉምና ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ አላቸው። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። በተአምራትም ገንዘብ ገንዘባቸውን ለይቶ ከዛፍ ላይ እንደሰፈረ ንብ ከቃ ከቃቸው ላይ አስቀምጦላቸዋል። ቁ.17 “ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ።” ነቢየ እግዚአብሄር ቅዱስ ዳዊት በመዝ 68፡9 በቤተ መቅደስ ስዕለ ፀሀይ አቁመውበት መስዋእተ እሪያ ሰውተውበት ገበያ አድርገውት ሲሸጡበት ሲለውጡበት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ለቤተ እግዚአብሄር የቀናውን ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ ይላል።
“እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። ትርጉም የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት። ”
ይህ ትንቢት ለጊዜው ለመቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው። በመቃቢስ ጊዜ አንጥያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል። በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል። ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማይበረታቱበት አምላከ አማልክት ወንጉሠ ነገሥት ነው። ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑት በቤተመቅደስ ውስጥ ባሉት ታቦታት፣ንዋያተ ቅደሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። ነቢየ እግዚአብሄር በቤተመቅደስ ገበያ አቁመው የሚገዳደሩትን ባየሁ ጊዜ ተግዳሮታቸው በእኔ ላይ ወደቀ ነፍሴንም በጾም አስመረርኋት ይላል። በደብተራ ኦሪት ሁለት እጓላተ ለህም አቁመው እንደተገዳደሩት፣መና ከደመና አውርዶ ቢመግባቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና ብለው እንደተፈታተኑት ፣ በኋላም ወልደ እጓለ እምሕያው ስጋየን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው ቢላቸው እፎ ይክል ዝንቱ የሀበነ ሥጋሁ ንብላዕ ብለው እንደተገዳደሩት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ሰውነቴን በርሃብ በቀጠና አደከምኩዋት እያለ ነቢየ እግዚአብሔር የተናገረውን ደቀመዛሙርቱ አስበው እነሱም ለቤቱ ቀኑ። በዚህ ዘመን እኛም ለቤተክርስቲያን ቅናት ሊኖረን ይገባል ለክብሩ መቅናት ለገዳማቱ ለአብነት ትምህርት ቤቱ መፈታት ለሊቃውንቱ መታረዝ ልቡናችን ሊቃጠል ይገባል። “ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።” ቁ.19 እና 20 በ46ቱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተነገረውን ልደቱን ሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ሁሉ ስለ ሰውነቱ አስረዳቸው። እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ። በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ።
አንጽሆተ ቤተመቅደስ
ይህም ቀን የማንጻት ቀን አንጽሆተ ቤተመቅደስ ይባላል።ኦሪት ወንጌልን፣ ምኵራብ ቤተክርስቲያንን አስገኝተዋል ጌታም የበግ የፍየል መስዋእት መቅረቱን ለቤዛ ዓለም መምጣቱን አስተማሯቸዋል አስጠንቅቋቸዋል። ምኵራብ ሁሉ የማይገባባት ነበረች በመጽሐፈ ነህምያ ምዕ 13፡1 “አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ።” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የማይመረጥባት አንተ አይሁዳዊ አንተ ሮማዊ የማትል አንዲት ኵላዊት ቤተመቅደስን ሰጠን።
ምኵራብ /ቤተ መቅደስ/ የሰውልጅ ምሳሌ ነው ምኵራብ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው ሸቀጡም የኃጢአት ምሳሌ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነትን ስለማንፃት እና እራስን ከሸቀጥ ስለማራገፍ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስተማረውን ማሰብ ያስፈልጋል እኛም የህያው አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደስ ነንና ሰውነታችን ሽያጭ የሚፀናበት እንዳይሆን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል።
●1ኛቆሮ ምዕራፍ 3-17 “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
●1ኛቆሮ ምዕራፍ 6-20 ላይ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
●2ኛቆሮ ምዕራፍ 2-17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
በቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ “ተንስኡ በፍርሃተ እግዚአብሔር ከመ ታፅምኡ አርኅው መሳክወ አእዛኒክሙ ወአንቅሁ ልበክሙ” እግዚአብሔርን በመፍራት ተነሱ የጆሮቻችሁን መስኮቶች ክፈቱ ልቦናችሁን አንቁት እንደተባልን ሳንፈዝ ማን አዚም አደረገባችሁ ተብለንም እንዳንወቀስ የእግዚአብሔርን ተግሳፅ የአበውን ምክር ሰምተን አሁን ሰውነታችን በንስሐ ለማንጻት እንነሳ። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ 94፡8 “ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታፅንኡ ልበክሙ” ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ስትስሙ ልባችሁን አታፅኑት እንዳለ ይህን በምኵራብ አምላካችን ያደረገውን ስንሰማ የዘረኝነት የፍቅረ ንዋይ የተንኮል የትዕቢት ሸቀጣችን ትተን ቤተመቅደስ ሰውነታችን በንስሐ አጥበን ልባችን በትህትና ሞልተን በቤቱ ለበለጠው ጸጋ ቀንተን ቅንነትንም አክለን በቤቱ ለመኖር አምላካችን ይርዳን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!