የመስቀሉ ነገር ለምናምን ለእኛ የእግዚአብሔር ኃይል ነው ። (1ኛ ቆሮ 1፥18)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በዲያቆን ዮሐንስ አያሌው
ቤተ ክርስቲያናችን በዓለ እግዚአብሔርን በማክበር ነገረ እግዚአብሔርን፤ በዓለ ቅዱሳንን በማክበር ነገረ ቅዱሳንን፤ በዓለ መስቀልን በማከበር ነገረ መስቀሉን ታስተምራለች። በበዓለ መስቀሉ እና በሌሎችም በመንፈሳዊ በዓላት አከባበሯ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰማይ ላይ ደምቃ እንደምታበራ ፀሐይ ናት። ፀሐይ በጨለማው ሰማይ ላይ ብርሃኗን በመፈንጠቅ የቀን ብርሃንና ውበት እንደምትሰጥ ቤተ ክርስቲያናችንም መንፈሳዊ ብርሃኑ በጠፋበት ዓለም የክርስትና ጸጋዋን እያጎናጸፈች ለጨለማው ዓለም ታበራለች። መንፈሳዊ በዓላትን ማክበር ወንጌልን መስበክ ነው። የቀደሙት ክርስቲያኖች ወንጌልን እንደልብ መስማት በማይችሉበት ዘመን በሰሙት ጥቂት ቃለ እግዚአብሔር ከአምላካቸው ጋር ይገናኙ የነበሩት በዓለ መስቀልንና በዓለ ቅዱሳንን በማክበርና መታሰቢያቸውን በማድረግ ነበር።
ቅዱስ ጳውሎስ የመስቀሉ ነገር በሚጠፉ ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፣ ለምንድነው ለእኛ የእግዚአብሔር ኃይል ነው (1ኛ ቆሮ 1፥18) ብሏል። መስቀል በዘመነ ኦሪት ክፉ ይባሉ ከነበሩትና በሐዲስ ኪዳን አምላካችን የሕይወት መገኛ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ከጨለማው ዓለም አውጥቶናል። በመሆኑም ዛሬ መስቀል የብርሃን እና የድል ምልክት ነው። በኃጢአቱ ምክንያት ከአምላኩ እርቆ የነበረውን አዳምን በዲያብሎስ ግዞት ከሚደርስበት መከራ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አድኖታል (ሉቃ. 22፥52)። በዚህም “ፈደየ እዳነ በመስቀሉ” በመስቀሉ እዳችንን ከፈለ እያልን እናመሰግነዋለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በመስቀሉ ጥልን አጠፋ”(ኤፌ. 2፤16) ብሎ እንዳስረዳን መስቀል ዛሬም ጥልንና ጥፋትን የሚያመጡ ወንበዴዎች ሰይጣናት የሚጠፉበት ነው። “ከባላጋራችን የተነሳ በትእዛዝ የተጻፈውን የእዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፣ ከመካከላችንም አራቀው፣ በመስቀሉም ቸነከረው” (ቆላ. 2፤14) እንደተባለ ዛሬም ወንበዴዎች አጋንንትን በኃይሉ ቸንክረን አስረን በሰላም እንድንኖር የሚያስችለን ታላቁ የሰላማችን አምባ መስቀል ነው። መስቀል ኃይል፣ ጸወን (አምባ፣ መጠጊያ፣ መሸሸጊያ፣ ማምለጫ) ነው።
መስቀል ዓለሙ የተቀደሰበት ዛሬም የሚቀደስበት የቅድስናና መንፈሳዊ ሀብታት መገኛ መኾኑን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ውዳሴ መስቀል በተሰኘ መጽሐፋቸው ሲመሰክሩ “አማንኬ ይደሉ ከመ ይስቅሉ ለወልደ እግዚአብሔር እስመ በመስቀሉ ይቄድሶ ለዓለም” – በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ይቀድሰው ዘንድ በመስቀል ላይ መሰቀሉ የተገባ ነበር። ይኽም የተገባ የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አዳም በድሎ፤ እንደ ቃየል ገድሎ፤ እንደ ይሁዳ አታሎ ሳይሆን በመስቀሉ ዓለሙን ኹሉ ይቀድሰው ዘንድ ነው።” በማለት ርኩሳን ይሰቀሉበት የነበረውን የጥፋት መሳሪያ ዓለምን የሚቀድስ መንፈሳዊ የውጊያ መሳሪያ እንዳደረገው ገልጸውልናል። ሌሎች ሊቃውንትም “ወለእመ ኢተሰቅለ እመ ኢድኅነ ” ባይሰቀልስ ኖሮ ባልዳንን ነበር፣ በማለት የሚያስተምሩን ይህንን እውነት ገልጦ ለማስረዳት ነው።
ለቅዱስ መስቀሉ በዓሉን እንድናከብር ብቻ ሳይኾን የጸጋ ስግደት እንድንሰግድለትም ታዝዘናል። ይህንንም ያዘዙን ቅዱስ ወንጌልን ያስተማሩ ሐዋርያት መኾናቸውን ቤተ ክርስቲያናችን ትመሰክራለች። መስተብቍዕ ዘመስቀል በተባለው የቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት ክፍል የተገለጠውን ስንመለከት “አዘዙነ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ለማርያምሰ ዘንሰግድ ላቲ እስመ ነሥአ ሥጋ እም ሥጋሃ እግዚአብሔር ፈጣሪሃ ወረከብነ መድኃኒተ እምኔሃ ለዕፀ መስቀልኒ እስመ አንጠብጠበ ደመ ቃል” – የቅዱስ ወንጌል አስተማሪዎች ቅዱሳን ሐዋርያት/መምህራን ለድንግል ማርያምና ለመስቀል እንድንሰግድ አዘዙን። ለድንግል ማርያም የምሰግድላት እግዚአብሔር ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋም ነፍስን ነስቶ ሰው ስለኾነና ሰው በመኾኑም ከእርሷ መድኃኒትን ስላገኘን ነው። ለመስቀል የምንሰግደውም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ አዳኝ ፈራጅ የኾነ ቅዱስ ደሙን ስላንጠበጠበበት ነው ተብሎ ተብራርቶ ተጽፎልን እናገኘዋለን። (መስተብቍዕ ዘመስቀል)
መስቀል ከላይ እንዳየነው በብሉይ ኪዳን ወንበዴዎች የሚቀጡበት መቀጣጫ የነበረ ቢኾንም የሐዲስ ኪዳን ሕይወትነቱን ለመግለጥ በዘመነ ኦሪትም ብዙ መንፈሳዊ ተአምራት ይፈጸሙበት ነበር። ለምሳሌ፦ በራፌድ በረሃ ሙሴ ከአማሌቃውያን ጋር በተዋጋ ጊዜ እጁን በትምእርተ መስቀል አምሳል በመዘርጋት አማሌቃውያንን ድል ነስቷቸዋል።(ዘጸ 17፥8–13) ስለዚህም “መሰቀል ዘተገብረ በአምሳሊሁ ለእደ ሙሴ በገዳመ ራፌድ በእንተ ጸብአ አማሌቅ” – በአማሌቃውያን ጥል ምክንያት በገዳመ ራፌድ በሙሴ እጆች አምሳል የተዘረጋ ቅዱስ መስቀል ነው ተብሎለታል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ የማራን ውኃም እንጨት በመስቀል አምሳል አመሳቅሎ በመጣል ከመራራነቱ ፈውሶታል።(ዘጸ 15፥23–25) ይኸም “መስቀል ዘአጥዐሞ ለማይ መሪር በገዳመ ሱር ሶበ ተወደየ ውስቴቱ በእደ ሙሴ” በነብዩ በሙሴ እጅ ተመሳቅሎ ወደ ውስጡ በተጣለ ጊዜ መራራውን የሱር ውኃ ያጣፈጠው መስቀል ነው ተብሎለታል።(ውዳሴ መስቀል) የሱርን (የማራን) ውኃ እንዳጣፈጠ ዛሬም መስቀሉ የብዙዎችን መራራ ሕይወት ወደ መንፈሳዊ ጥፍጥና ይለውጣል። ነብዩ ሙሴ የሠራው የነሃስ እባብና መስቀሉም ዕፀ መስቀል እባብ የተባለ የሰይጣንን ተንኮል የምናልፍበት ከንክሻውም የምንድንበት መሆኑን ማሳያ ነው። በአጠቃላይ መስቀል ለክርስቲያኖች ሕይወታችን ነው። በተጨማሪም መስቀል፦
- ክርስቶስ የሚያበራበት ተቅዋመ ወርቅ (የወርቅ መቅረዝ) ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”። በብርሃኔ ተመላለሱ ብሎናል። ፀሐይ የሚሽከረከረው በነፋሳት እንደኾነ መብራት የሚበራውም በመቅረዝ (ማብሪያ) ላይ ኾኖ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ሲኾን ብርሃኑ የተገለጠበት ማብሪያው ደግሞ መስቀሉ ነው። ይህን ይዞ ሊቁ ሲያደንቅ “ኢየሱስ ክርስቶስን ሊሰቅሉት ሥጋውን ከልብስ አራቆቱት ምክንያቱም ለመብራት የሚፈልገው ኹሉ እንዲያየው ከፍ ብሎ በተቀመጠ በመቅረዙ ላይ ኾኖ ማብራት እንጅ በልብስ ተሸፍኖ መቀመጥ አይገባውምና፤ ዳግመኛም ሊሰቅሉ በእንጨት ላይ አወጡት ለምን ካላችኹ መብራትን አብርተው በተራራ ላይ እንጅ ከእንቅብ በታች በምድር ላይ ሊያስቀምጡት አይገባም።” “ተቅዋምሰ መስቀል ውእቱ ወማኅቶትኒ አማኑኤል ውእቱ ናንሦሱ እንከ በብርሃኑ ለወልደ እግዚአብሔር ወኩሎ ዘየአምን ኪያሁ ውስተ ብርሃን ይሐውር ወጽልመትኒ ኢይረክቦ – ማብሪያ መቅረዙ መስቀል ነው፤ በቀራንዮ ተራራ ላይ በተተከለ የመስቀሉ መቅረዝ ላይ የሚያበራው ብርሃን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንን ተረድተን ኹላችንንም በብርሃኑ እንመላለስ በእርሱም እንመን። በእርሱ የሚያምን በብርሃን ይመላለሳል ጨለማም አይቀርበውም” በማለት አስተምሮናል። (ውዳሴ መስቀል)
- አስቀድሞ የሰውን ልጅ ለማዳን የተዘጋጀ ነው።
አባ ጊዮርጊስ ሔዋን “ሔዋን” ተብላ ስም የወጣላት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል አማካኝነት እንደኾነ ኹሉ በመስቀሉ ያመነ ሕይወት እንዲሆነው ስላወቀ መስቀሉንም አስቀድሞ “ዕፀ ሕይወት” አለው በማለት መስቀሉ አስቀድሞ በአምላክ ዘንድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ይመሰክራሉ። የተሰቀለው እርሱ አስቀድሞ ባዘጋጀው መስቀል እንደኾነ ሲገልጡም “አምጽኡ ዘዚአሁ ለዚአሁ፣ የራሱን ለራሱ አመጡለት” በማለት እያደነቁ ጽፈዋል።
- ድኅነታችን የተጻፈበት ሕያው መጽሐፍ ነው።
የዕዳ ደብዳቤያችን አስቀድሞ በእብነ እርካብ ተጽፎ ነበር። መጽሐፍ ድኅነታችን ደግሞ በአምላካችን በደሙ ቀለምነት በመስቀል ላይ ተጽፏል። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ “የዕዳ ደብዳቤያችንን በመስቀሉ ጠርቆ አስሮ ከመንገዳችን አስወገደው”ብሎ የመሰከረው። ሌላኛው ሊቅም “በንጠብጣበ ደምከ ተጽሕፈ ምሕረትከ በሰሌዳ መስቀልከ፣ በመስቀልህ ሰሌዳ ላይ በደምህ ነጠብጣብነት ምሕረትህ ተጻፈች” በማለት ይህንን እውነት አጽንተው አስተምረዋል።
- የአምላካችን የፍቅሩ መግለጫ ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለሰው ልጆች እንደ ክርስቶስ መስቀል ያለ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያስረዳ (የሚገልጥ) ነገር የለም በማለት እንዳስረዳን፤ መስቀል የፍቅሩ መገለጫ ነው።( Commentary on 2nd Timothy) ቅዱስ ዮሐንስም “በወንጌሉ በእርሱ የሚያምን ኹሉ እንዲድን እንጅ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስከ መስጠት ድረስ እንዲሁ ዓለሙን ወዶታል” በማለት የመሰከረለትን የእግዚአብሔር ፍቅር (ዮሐ. 3፥16) ያለ መስቀሉ መረዳት አይቻልም። እስከ መስቀል ድረስ የታመነ ሆነ የተባለውን መረዳት የሚቻለው ነገረ መስቀሉ ሲገባን ብቻ ነው። ነገረ መስቀሉን ሳንረዳ ወደ እምነት ልንመጣ አንችልም። የመስቀልህ ጥላ ፈያታዊ ዘየማንን አንተን ወደ ማመን መለሰው እንዳለ ሊቁ ዛሬም ወደ ንስሐና ወደ ተግባራዊ ክርስትና የሚያደርሰን ትልቁ ሀብታችን በመስቀሉ ላይ የሚያበራው የክርስቶስ ብርሃን በልቡናችን ውስጥ ሲያበራ ነው።
- የሥጦታዎች ኹሉ መገኛ ነው።
ሕይወት፤ ድኅነት፤ ትንሣኤ፤ ምልጃ፤ እርቅ፤ ተስፋ፤ ተድላ ገነት በመስቀሉ የተገኙ ናቸው። እመቤታችንና ሐዋርያት ሁሉም የተሰጡን ከመስቀል ስር ነው። ከመስቀሉ ስር ካለቅስን አብሮን የሚያለቅስ አናጣም። ሌላው መስቀሉ ኃጢአታችንን በመግለጥ ወደ ንስሐ ያደርሰናል። ከመስቀሉ ስንርቅ ግን የአምላካችን ውለታውን እንረሳዋለን።
- የዳግም ምጽአት ምልክታችን ነው።
ክርስቶስ በፍጻሜ ዘመን በኅልቀተ ዓለም የሚመጣው ምልክት እያሳየ ነው። ይህንንም ቅዱሳት መጽሐፍት ሲመሰክሩልን “ክርስቶስ ይመጽእ በደመና ሰማይ ምስለ ኃይል ወመላእክቲሁ ምስሌሁ ወመስቀሉ ቅድሜሁ አሜሃ እለ ወግዑከ ይበክዩ፤ ወእለሰ ይነስዑ ማኅተመ ስምከ ይከውን ሎሙ ሰላመ ወሣህለ እግዚአብሔር – ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃይሉ ጋር መስቀሉ በፊቱ እያበራ በክበበ ትስብእት በይባቤ መላእክት ይመጣል፤ ያንጊዜም የወጉት ያለቅሳሉ፤ የስሙን ማኅተም የያዙ ግን ሰላምና የእግዚአብሔር ምሕረት ይደረግላቸዋል” በማለት ያስተምራሉ። (ራዕ 1፥7፣ ዘካ 12፥1) አምላካችን እኛንም ለቀኝ ቁመት፣ ከእግዚአብሔር የሚሰጠውን ሰላምና ምሕረትም ለመቀበል የበቃን የሚያደርገን ምልክት መስቀል ነው።
በመሆኑም መስቀል በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በአባቶቻችን በካህናት እጅ ተይዞ ስናየው ክብሩና ኃይሉ እንደምናየው በሰውና በቦታ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ምስጢሩና ሀብቱ ጥልቅና ብዙ ነው። ስለኾነም ድርሳን ተደርሶለታል፤ መልክእ፤ መስተበቍዕ፤ ውዳሴ፤ ሰላምና አርኬ ተጋጅቶለታል።(መጽሐፈ ጤፉት) በእነዚህ ድርሳናትም ሊቃውንቱ ደሙ የፈሰሰበት ክቡር መስቀልን ልብን ደስ የሚያሰኝ የሕይወት የወይን ወንዝ (ፈለገ ወይን)፤ መንፈሳዊ ጣዕምን የሚያሰጥ የማር ወንዝ (ፈለገ ማዕር)፤ ሕይወት የሚገኝበት፣ ነፍስን የሚያጠራና የሚያሰማምራት የመንፈሳዊ ዘይት ወንዝ (ፈለገ ቅብዕ)፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ሕጻናት የኾን ሁሉ አባታችንን ወደ መምስል የሚያሳድገን በጸጋና በቅድስና የምንልቅበት የወተት ወንዝ (ፈለገ ሐሊብ)፣ እያሉ በሚያሰጠው ሀብትና ጸጋ ዓይነት እያመሰገኑ እንድናመሰግን አዝዘውናል።
በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልኹበት ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” እንዳለው፤ ትምክህታችን መስቀሉና በመስቀሉ ላይ የተገለጠው ፍቅር ኹኖ ዛሬም የቅዱስ መስቀልን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ቃለ እግዚአብሔር በመስማት፤ ቅዳሴ በማስቀደስ፤ ዝክር በመዘከር መንፈሳዊ በረከት የምንቀበል ብዙዎቻችን ነን፤ ከዚህም በላይ የበረከት፤ የቃል ኪዳን፤ የማንነት ከዚህ አልፎም የሕልውናችን ምንጮች የሆኑ መንፈሳዊ በዓላታችንን በደማቅ ኹኔታ ማክበራችንን የበለጠ አጠንክረን ልንቀጥልበት የሚገባ ነው። የውጭው ጥቁር የባህል ደመና እንዳይወድቅባቸው፤ ከትውፊታዊ ይዘታቸውም ሳይቀነሱ እንዲከበሩ መጣርም ከምንፈጽማቸው ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው። ለዚህም ይረዳን ዘንድ እርስ በእርሳችን እንድንፋቀር፤ አምላካችንን፤ አገልግሎታችንን፤ ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችንን እንድንወድ የልዑል አምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን። አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ለዓለም ዓለም አሜን።