ደብረ ዘይት
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
ደብረዘይት የዓቢይ ጾም እኩሌታ ነው ። በእለቱም ስለ ዳግም ምጽአት ይነገራል። ስለ ምጽአት ነቢዩ ዘካርያስ «በዚያን ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ… አምላኬ እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይመጣል …አንድ ቀን ይሆናል…. በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይወርዳል።» (ዘካ ፲፬ ፥ ፬–፰) በማለት አስቅድሞ ትንቢት ተናግሯል :: አምላክ በዚህ ትንቢት እና በሌሎች ነቢያት ያናገረውን ፣ እርሱ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ላይ የዳግም ምጽአት ምልክቶችን እና አመጣጡን ከፍርዱ ሂደት ጋር በግልጽ አስተምሯል። ይህንንም ሁሉ የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት ስትዘከረው ኖራ በምጽአት ቀን ተስፋዋን መንግሥተ ሰማያትን ትረከባለች:: በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደተለመደው በዚህ የደብረ ዘይት ሳምንት ጽሑፍ ስለ ደብረ ዘይት ፣ ስለምጽአት ምልክቶች ፣ ስለምጽአት እና ተስፋው እንዘከራለን ።
ደብረ ዘይት በዚያን ዘመን የወይራ ዛፍ በብዛት የነበረበት ተራራ ነበር። በዚህም ስያሜውን ደብረ ዘይት ወይም የወይራ ተራራ መባልን አግኝቷል። የወይራ ተራራው ምሥጢር የሚነገርበት፣ የወይራ ፍሬ ምሥጢራት የሚፈጸሙበት እንደሆኑ ሲያጠይቅ ጌታ በደብረ ዘይት ይገኝ ነበር። በመሆኑም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ተራራ በማዘወተር ዓበይት ጉዳዮችንም ለማድረግ መነሻ ያደርገው ነበር። ለምሳሌ ያህል እነዚህን ጥቅሶች እንመልከት ፣ «ጌታችን በሆሳዕና እለት ከደብረ ዘይት ተነሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ገባ።» (ማር ፲፩ ፥ ፩) «ከደብረ ዘይት ግርጌ በጌቴሴማኒ ጸሎት አደረገ ፤ ጭፍሮችም መጥተው ከደብረ ዘይት ያዙት ።» (ማቴ ፳፮ ፥ ፴፮) «በደብረ ዘይት ተቀምጦ ስለ ዓለም ፍጻሜና ምልክቱ አስተማረ።» (ማር ፲፫ ፥ ፫) «ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ሰማይ አረገ።» (ሉቃ ፳፬ ፥ ፶፩ ፶፪) «በትንቢትም እንደተነገረው በዓለም ፍጻሜ ለፍርድ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይወርዳል።» (ዘካ፲፬ ፥ ፬–፰) ጌታችን የወይራ ተራራን ዓበይት ጉዳዮች መነሻ እንዳደረገ ሁሉ ከወይራ የሚገኘውን ዘይትም ቤተክርስቲያን ዓበይት ምሥጢራትን መፈጸሚያ አድርጋቸዋለች። ለምሳሌ የወይራ ዘይት ቅብዓ ሜሮን እና ቅብዓ ዘይት ማዘጋጃ በመሆን ይጠቅማል። ይህም በሲኖዶስ ተጸልዮበት የመንፈስ ቅዱስ ማሕተም በመሆን ለቤተክርስቲያን መባረኪያ፣ ለክርስትና ጥምቅት፣ ለሥርዓተ ጋብቻ፣ ለቀንዲል ሥርዓት መፈጸሚያነት ወዘተ ይጠቅማል። የሰው ልጅ በፍርድ ቀን ለመዳን መጀመሪያ ክርስቲያን መሆን አለበት፤ ክርስቲያን ለመሆን በሚፈጸመው ምሥጢራት ውስጥ ደግሞ ቅብዓ ቅዱስ እጅግ አስፈላጊ ነው።
ከደብረ ዘይት ተራራ አብነት ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ የተስፋ ቃሉንና ምሥጢራትን መፈጸሚያ ቅብዓ ቅዱስን ቤተ ክርስቲያን በጥምረት ተረክባለች። የተስፋ ቃሉን በደብረ ዘይት በዓል እለት እና እስከ ዓለም ፍጻሜ ስትዘከረው ፣ ቅባዓ ቅዱሱን ለመጨረሻው ቀን ለክርስቶስ ሙሽሮች የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ማሳደሪያ በረከት በማካፈል ለክብሩ ቀን ታዘጋጃቸዋለች።
የምጽአት ምልክቶች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው የዳግም ምጽአት ምልክትን ጠይቀውታል። እርሱም አስቀድሞ «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» ካለ በኋላ የሚከተሉትን ምልክቶች ገልጾላቸዋል ። (አስቀድሞ በነቢያት የተነገሩትም ምልክቶች ተጨምረዋል)
ብዙ ሀሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ ፣
ብዙ ሀሰተኛ ክርስቶሶች ይነሳሉ ፣
ታላቅ ክሕደት ይሆናል ፣
በብዙዎች ዘንድ ፍቅር ይቀዘቅዛል ፣
የጦርነት ፣ የርኃብ ፣ የቸነፈር የምድር መናወጥ ወሬ መሰማት፣
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ መነሳሳት፣
ክርስቲያኖች በአሕዛብ የተጠሉ መሆን፣
የብዙዎች ለሞት ተላልፈው መሰጠት ፣
የብዙዎች ከእውነት መንገድ መሰናከል ፣
የጥፋት ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ መታየት፣
የተመረጡት እስኪስቱ ድረስ ድንቅ ተአምራት መደረግ ፣ (ማቴ ፳፬ የመከራ ዘመን ይሆናል)
«ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሳል።» (ዳን ፲፪ ፥ ፩ )
የአመጽ ሰው የክርስቶስ ተቃዋሚ መነሳት ፣ (፪ ተሰ ፪ ፥ ፫ )
የአውሬው የስድብ አፍ በገልጽ በብዙዎች ላይ መገለጽ (ራእይ ፲፫፥ ፭ ) ፣ ወዘተ
ከላይ የተገለጹት ምልክቶች በአሁኑ ዘመን በአብዛኛው የታዩ እና እየታዩ ያሉ ናቸው። ትንቢቱን የተናገረው ባለቤቱ ወልደ አምላክ ክርስቶስ በመሆኑ የበለጠ ትኩረት እንድናደርግበት ግድ ይለናል። ከዚህም ተነስተን የክፋት ትንቢት መፈጸሚያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል። ከምልክቶቹ ፍጻሜ አንጻር ግን እራሳችንን መታዘዝ በማስተማር ሕይወታችንን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ብቸኛ መፍትሄ ነው።
ምጽአት
ከብዙ የምጽአት ምልክቶች በኋላ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይሆናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እንዳረገ እንዲሁ ተመልሶ ይመጣል። ስለዚህም ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ «እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ ፥ እነሆነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሏቸው።» (ሐዋ ፩፥፱ ) በማለት ጽፎልናል። ከላይ «ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል» የሚለው ኃይለ ቃል የሚያስረዳው ጌታችን ባረገበት ኃይልና የመላእክት እልልታ እንዲሁ በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ በክብር በደመና ለፍርድ እና ለእያንዳንዱ ዋጋውን ለመስጠት መምጣቱን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈለጋል።
ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ(ማቴ ፳፭) ስለ ጌታችን ዳግም አመጣጥ እና በፍርድ ወንበር መቀመጥ ሲገልጽ «የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።» በማለት ጻድቃንን በበጎች፣ ኃጥአንን በፍየሎች መስሎ ጻድቃንን ለክብር በቀኝ፣ ኃጥአንን ለሃሳር በግራ ለይቶ ያቆማቸዋል። ቀጥሎም ጌታችን ክርስቶስ በፍርድ ቃል በቀኙ ያሉትን «እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።» ይላቸዋል። ነገር ግን ጻድቃን ብዙ መልካም ሥራ ሰርተው ሳለ ምንም እንዳልሰሩና እንዳላደረጉ ሆነው ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሳ ክብር እንደተሰጣቸው አውቀው በትህትና ቃል «ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?» ይሉታል። እርሱም መልሶ በሕይወት ዘመናቸው ከእነርሱ ለሚያንሱት ያደረጉትን መልካም የቸርነትና ትህትና ሥራ እንደዋጋ ቆጥሮላቸው «እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት» ብሎ ጻድቃንን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሰዳቸዋል።
ነገር ግን በኃጥአን ላይ ከዚህ በተቃራኒ ፍርዱም ሆነ የእነሱም ምላሽ የተለየ ይሆናል። ጌታም እርሱን ባላመለኩት መጠንና ከሰይጣናት በተስማማ ሁኔታ መንገዳቸውን ባደረጉ ልክ እንዲህ በማለት ይፈርድባቸዋል፤ «እናንተ ርጕማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።» እነርሱ ግን ፍርዱን በመቃወም እንዲህ እያሉ ይከራከራሉ። «ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም?» ጌታችንም በምላሹ የርህራሄን ሥራ ለታናናሾቻችሁ አልሰራችሁም ፤ ያን አለመስራታችሁ ለኔ አለመስራታችሁ ነው ብሎ ወደ ዘለዓለም ቅጣት ይሰዳቸዋል።
ያቺ የፍርድ ቀን የዓለም ፍጻሜ ናት። በዛች ቀን መስማት እንጂ መመለስ መከራከር የለም። የዚያች ቀን የፍርድ ውሳኔ ዛሬ በምድር ላይ የምንፈጽመው የአምልኮና የመልካም ወይም የክፉ ምግባር ውጤት ነው። ዛሬ አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ካደረግን ከእግዚአብሔር ጋር በተስፋዪቱ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንሆናለን፤ዛሬ አካሄዳችንን ከዲያብሎስ ጋር ካደረግን ግን በግራ ከዲያብሎስ ጋር እንቆማለን፤ትሉ በማያንቀላፋ እሳቱ በማይጠፋ በገሃነም እሳት መኖር ግድ ይለናል። የዛሬ የአምልኮ አያያዛችን የፍጻሜውን ቀን ይወስነዋልና ዛሬ ሳናመነታ አኗኗራችንን እንወስን።
ተስፋ መንግሥተ ሰማያት
የደብረ ዘይት እለት ጻድቃን የሚናፍቋት የተስፋ መንግሥተ ሰማያት እለት ናት። ተስፋ ብርሃናዊ መገስገሻ መንገድ ናት።ተስፋ የማይታየውን አጉልታ፣ ሩቁን አቅርባ የምታሳይ መነጽር፣ መከራውን ደስታ የምታደርግ ሀሴት፣ደካማውን የምታበረታ ኃይል ናት። የሰው ልጅ የተስፋ መንግሥት ሰማያትን ፍጹም ደስታ፣ የቀቢጸ ተስፋ ገሀነመ እሳትን ፍጹም ሥቃይ ቢያውቅ፣ ቢረዳው ኖሮ በዚህ ዓለም ይድላኝ ሳይል ኑሮው በመንኖ ጥሪት ይሆን ነበር። «ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኲሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ሃጉለ። ወምንተ እምወሀበ ሰብእ ቤዛሀ ለነፍሱ። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?» (ማቴ ፲፮ ፥ ፳፮ ) እንዲል።
ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር መንግሥት ናት። እርሷም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያዘጋጃት፣ የእግዚአብሔር ምሕረቱና ጥበቡ የሚገለጽባት፣ በትንሣኤ ዘጉባኤ ፍርድ ቀን በእርሱ ያመኑ የሚገቡባት የእግዚአብሔር ቤት ናት። «በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ … እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።» እንዳል ጌታ በወንጌሉ።
በአጠቃላይ ደብረ ዘይት ሁለት ተቃራኒ ነገሮች የሚፈጽሙበትን የነገረ ዳግም ምጽአት ሁኔታን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምንማርበት የዓቢይ ጾም ሳምንት ነው። ይኸውም ትንሣኤ ዘለክብር እና ትንሳኤ ዘለሀሳር ነው። አንዱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆንበት ሌላው ከሰይጣን ጋር ኑሮው የሚወሰንበት፣ አንዱ መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሌላው ገሀነመ እሳት የሚገባበት፣ አንዱ የሚደሰትበት ፣ ሌላው ዋይታ የሚያሰማበት፣ የበረከትና የመርገም ቀን፣ የተስፋና ተስፋ የመቁረጥ ቀን፣ የደስታና የጭንቅ ቀን፣ የእልልታና የዋይታ ቀን፣ አንዱ ሌላውን የማያድንበት፣ እናት ልጄን የማትልበት፣ ልጅ እናቴን የማይልበት፣ ባልና ሚስት የሚለያዩበት፣ ጓደኞች ዳግም የማይገናኙበት፣ ኃጥእ ከጻድቅ መተያየት የሚያበቁበት የመጨረሻ እለት ዳግም ምጽአት ናት።
ሰሚ ከሆንን የደብረ ዘይትን ጩኸት ልንሰማ ይገባናል። የምትነግረንን የምጽአትን ምልክቶች፣ የምጽአትን ትንቢቶች፥ «እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፣ ወአምላክነሂ ኢያረምም፣ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ። እግዚአብሔር በግልጽ ይመጣል፤ አምላካችን ዝምም አይልም ከፊቱም እሳት ይነዳል» ፣ ወዘተ የሚለውን ፣ ጌታ በወንጌሉ በፍርድ ቀን ለእያንዳንዱ እከፍለው ዘንድ በቁጣ እመጣለሁ ያለውን ፣.. ከደብረ ዘይት ልንማር ይገባናል። ያለዚያ ግን በመጨረሻው ቀን ዕጣ ፈንታችን ከዲያብሎስ ጋር እሳቱ በማይጠፋ እና ትሉ በማያንቀላፋ በገሃነመ እሳት ሥቃይ ይሆናል ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !