ደብረ ታቦር

በዲን. ኃይሌ ታከለ

ነሐሴ 12፣ 2004 ዓ.ም.

Debre_Tabor

ደብረ ታቦር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ታቦር በተሰኘው ረጅም ተራራ የገለጠበት ታላቅ በዓል ነው።  በማቴ 16፥13-19 እንደምንመለከተው ኢየሱስ በፊልጶስ ግዛት ከምትሆን ከቂሣርያ አውራጃ በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- ”ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም ደግሞ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንኩ ትላላችሁ አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱም መካከል ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ በማለት መለሰለት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- ”የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” በማለት ተናገረው።

በዚህ ጥያቄና መልስ እንደምንረዳው በዚያን ዘመን ክርስቶስ በሥጋ በተገለጠበት ወራት አይሁድ ምንም እንኳ መጥምቁ ዮሐንስ አስቀድሞ ስለ መሲህ ክርስቶስ ቢሰብክላቸውም፤ ክርስቶስም በቃል ቢያስተምራቸውም፤ ተአምራት ደጋግሞ ቢያሳያቸውም ማን እንደሆነ ግን አላወቁትም ነበር። አንዳንዶቹም ንጽሕናውን አይተው ዮሐንስ መጥምቅ፤ ድንግልናውን አይተው ኤልያስ፤ ቅድስናውን አይተው ኤርምያስ፤ ይህም ባይሆን ተአምራቱን አይተው ከቀደሙት ነቢያት ውስጥ አንዱ ነው  በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የባሕርይ ልጅ፥ በኋለኛው ዘመን የሰውን ልጅ ለማዳን ንጽሕት ቅድስት ድንግል ከምትሆን ከማርያም እንደተወለደ አልተረዱም ነበር።

ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ከጠየቃቸው ከስድስት ቀን በኋሏ ከነቢያትም አንዱ ነህ ብለውታልና የነቢያት አምላካቸው እንደሆነ ለማጠየቅ፤ ሶስቱን ባለሟሎቹን (ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ቅዱስ ዮሐንስን) ለብቻቸው ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ገጹም እንደ ፀሐይ ብሩህ፤ ልብሱም እንደ በረድ ነጭ ሆነ። እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ሙሴ የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል የሙሴ አምላክ ይበሉህ እንጂ፤ ኤልያስም የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ይልሃል የኤልያስ አምላክ ይበሉህ እንጂ ሲሉ ተሰምተዋል። ቅዱስ ጴጥሮስም በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለው። እርሱም ገና ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም- ”በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” የሚል ድምጽ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሰምተው ደነገጡ ፈጽመው ፈሩ በፊታቸውም ወደቁ። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው፤ አይዟችሁ ተነሡ አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዩ እንጂ ማንንም ማን አላዩም (ማቴ. 17፥1-8)። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን በታቦር ተራራ ገለጸላቸው። ይኸውም “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል” (መዝ 88፥12-13) ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት ተፈፀመ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብሩን ስለምን በተራራ ገለጸዉ ቢሉ ተራራ የወንጌል፣ የመንግስተ ሰማያት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። ተራራ ሲወጡት ይከብዳል ከወጡት በኋላ ግን ሜዳውንና ጭንጫውን ኮረብታውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል: ወንጌልም ሲማሯት ታጽራለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኃጢያትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና። አንድም ተራራ በብዙ ፃእር እንዲወጡት መንግስተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና ነው። በዚህም ተራራ ከነቢያት ሁለቱን ከሐዋርያት ሶስቱን ማምጣቱ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ እንዲነገር ለማጠየቅ ነው። መንግስተ ሰማያትንም ነቢያትና ሐዋርያት፤ ደናግላን እንደ ኤልያስና መዓስባን እንደ ሙሴ ያሉ፤ ሕያዋን እንደ ኤልያስና ምውታን እንደ ሙሴ ያሉ በአንድነት እንዲወርሷት ለማስረገጥ ነው።

በፊሊጶስ ቂሣርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ”የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ሲል እንደመሰከረው ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) የሰውን ሥጋ ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ እኛን ለማዳን መምጣቱን ዳግመኛ በደብረ ታቦር ገለጸልን።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ለነቢያት እና ለሐዋርያት እንደገጸ ለኛም የብርሃነ መለኮቱን ምስጢር ይግለጥልን:: ንጽሕት በምትሆን በተዋህዶ ሃይማኖት እስከ መጨረሻው ያጽናን አሜን።