ጾመ ፍልሰታ

በኤርምያስ ልዑለቃል

ሐምሌ 30፣ 2004 ዓ.ም.

filseta

“አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” ሉቃ 1 ፡28

ጾመ ፍልሰታ በከበረች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የምንኖር የእግዚአብሔር ልጆች በረከትን ከምንቀበልባቸው የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን በየዓመቱ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 16 ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ፍቅር ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ ለእግዚአብሔር በመገዛት በተሰበረ ልቦና እና በተሰበሰበ ህሊና ከጥሉላት መባልዕት (ለሰውነት ብርታት ከሚሰጡ የእንስሳት ተዋፅኦ እና ቅባትነት ካላቸው ምግቦች) እና ከክፉ ስራ ሁሉ ተለይተን በበረከት የምንትረፈረፍበት የጾም ወቅት ነው። ፍልሰታ የሚለው ቃል ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር፣ የነበሩበትን ስፍራ ለቆ ወደ ሌላ ስፍራ መወሰድ ወይም መፍለስ ማለት ነው።

ጾም አምላካችን እግዚአብሔርን የምናስብበት፣ ነፍስና ሥጋችንንም የምናስገዛበት ክርስቲያናዊ ስነ ምግባር ነው። በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳን አበው ጾም የጸሎት እናት፣ የእንባ ምንጭ፣ የነፍስንም ቁስል የምትፈውስ መድኃኒት መሆኗን አስተምረውናል። በመሆኑም በከበረ ጾም የለበሱት መንፈሳዊ ጸጋ ዛሬም ድረስ ስማቸው በሚጠራበት ክብራቸው በሚዘከርበት ቦታ ሁሉ አጋንንትን የሚቀጠቅጥ ኃይልና የትሩፋት ፍሬ ሆኖ ይገኛል።

ጾመ ፍልሰታን በመጀመሪያ ጊዜ የጾሙ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው። የጾሙበት ምክንያትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር 21 ቀን ነፍስዋ ከሥጋዋ ተለይታ አርፋለች። ከጌታችን ዕርገት በኋላ በእርስዋ ሲጽናኑ የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በእመቤታችን እረፍት አዝነው፤ አልቅሰው የከበረ ሥጋዋን ተሸክመው በክብር ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ ሲጓዙ አይሁድ በክፋት ተነሱባቸው። ቀድሞ ‘ልጅዋ ተነሳ ዐረገ’ እያሉ ያስቸገሩን አንሶ ደግሞ እርስዋንም ‘ተነሳች ዐረገች’ እንዳይሉን ሥጋዋን እናቃጥል ብለው በኃይል መጡባቸው። ከእነዚሁ አይሁድ መካከል ጉልበታም የነበረ ታውፋንያ የተባለ ሰው በጉልበቱ ታምኖ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ጎትቼ እጥላለሁ ብሎ የአልጋውን ሸንኮር ቢይዝ የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጁን ቀጥቶታል። ወዲያውም መላኩ የከበረች የድንግልን ሥጋ ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር በደመና አሳርጎታል። የቀሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ እመቤታችን ሲያዝኑ ሲተክዙ ቅዱስ ዮሐንስን አግኝተው የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ? ቢሉት በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አለች ብሎ አጽናንቷቸዋል።

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈሳዊ ፍቅር እና ቅናት ተነሣሥተው ለቅዱስ ዮሐንስ የተገለጠ ምስጢር ለእኛም ይገለጥልን ብለው ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ፤ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ሰነበቱ። ሁለተኛውን ሱባኤም ሲጨርሱ በ14ኛው ቀን እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶ የከበረ መዓዛ ያለውን የእመቤታችንን ሥጋ በመላእክት እጅ አምጥቶ ሰጥቷቸዋል። ቅዱሳን ሐዋርያትም በፍጹም ምስጋናና በታላቅ ክብር እመቤታችንን በጌቴሰማኒ ቀብረዋታል። ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጇ ሥልጣን ፍጹም ኃይል ሆኗት በክብር ተነሥታለች። ትንሣኤዋን ‘ከመ ትንሣኤ ወልዳ’ ወይም ‘እንደ ልጇ ትንሣኤ’ ነው ያሰኘውም ይሄ ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሙታን ተነሥታ፣ በውዳሴ መላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ ከቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በደመና ተጭኖ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ አግኝቷታል። ሐዋርያው ቶማስም ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ከወንድሞቼ ተለይቼ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ለማየት አልታደልኩም ብሎ በጣም አዘነ። እመቤታችንም ቶማስን ‘ከአንተ ቀድሞ ትንሣኤዬን ያየ የለም እንግዲህ ሄደህ ለወንድሞችህ ሐዋርያት ተነሣች ዐረገች ብለህ የምሥራች ንገራቸው፣ ምልክትም ይሆን ዘንድ እነሆ መግነዜን (ሰበኔን) ውሰድ ፣ አንተ ዕርገቴን እንዳየህ እነርሱም ይህን አይተው እንዲያምኑ’ ብላው ወደ ሰማይ ዐረገች። የሐዋርያው ቶማስ ሀዘንም ወደ ደስታ ተለወጠ።

ይህ ሐዋርያ ኢየሩሳሌም ደርሶ ሌሎቹ ሐዋርያትን አገኛቸው ‘የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ?’ ብሎም ጠየቃቸው። እነርሱም እንደቀበሯት ነገሩት። ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ይህ እንዴት ይሆናል? አላቸው። እነርሱም መጠራጠር ልማድህ ነው እያሉ መቃብሯን ሊያሳዩ ወሰዱት። ሲደርሱም መቃብሯ ባዶ ሆኖ አገኙት ፣ እጅግም ደነገጡ። ቶማስም አትደንግጡ እመቤታችን ከሙታን ተነሥታ በውዳሴ መላእክት፣ በክብር ስታርግ አግኝቻታለሁ። እንዲያውም የተከፈነችበትን ሰበን ሰጥታኛለች ሲል ከእመቤታችን እጅ የተቀበለውን ሰበን አሳያቸው። ቅዱሳን ሐዋርያትም በሆነው ሁሉ ተደነቁ። በቶማስ እጅ ያለውንም የእመቤታችንን ሰበንዋን ለበረከት ተከፋፈሉት። በሰበኑም ሙት ያስነሱበት፣ ድውይ ይፈውሱበት፣ አጋንንትን ያርቁበት ነበር። ዛሬም ድረስ ያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ አርፎበት የነበረው መቃብር በምዕመናን ይጎበኛል።

ቅዱሳን ሐዋርያት ሐዋርያው ቶማስ ያየውን የእመቤታችንን የትንሳኤዋንና እርገቷን ክብር ያዩ ዘንድ በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ደግመው ሱባኤ ገቡ። በ16ኛው ቀን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረች እናቱ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ተገለጠላቸው። እመቤታችንን መንበር፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ዋና ዲያቆን አድርጎ እርሱም ገባሬ ሰናይ ካህን ሆኖ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። የቅዱሳን ሐዋርያቱም ሱባኤ ሰምሮላቸዋል።

በዚሁ መሰረት የከበረች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ምዕመናን ቅዱሳን ሐዋርያቱን አብነት በማድረግ እነርሱ በዚህ ታላቅ ሱባኤ እመቤታችንን እንዳገኙ፣ የማያልቅ የእናትነት በረከቷን ለማግኘት፣ በተወደደ አማላጅነትዋም የልጇን ይቅርታና ምህረት ለማግኘት፣ በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን። ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅዱሳን ሐዋርያት ተባርኮ በተሰጠን በዚህ ጾመ ፍልሰታ ሌሊቱን በሰዓታት፣ ነግሁን በኪዳን እና በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ከቅዱስ ኤፍሬምና ከአባ ሕርያቆስ በፈቃደ እግዚአብሔር የተገኙትን የእመቤታችንን ምስጋናዎች የውዳሴዋን እና የቅዳሴዋን ትርጓሜ በማሰማት ቅዱስ ወንጌሉ ተሰብኮ በከበረ ቅዳሴ የመድኃኔዓለምን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ታቀብላለች።

ይህ ምስጢር የተረዳቸው በርካታ ምዕመናን ሱባኤውን በታላላቅ ገዳማት ተወስነው ሲያሳልፉ እጅግ ብዙዎች ደግሞ በያሉበት ደብር ሥርዓተ ቅዳሴውን እያስቀደሱና በጸሎት እየተማጸኑ ይጠቀሙበታል። እንግዲህ በያለንበት ቦታ በዚህ ሱባኤ በንስሐ በታጠበ ሕይወት በረከተ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማግኘት እንድንተጋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታሰማለች።

የእግዚአብሔር አብ ጸጋ ፣የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን።

ምንጭ

1 የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

2 ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ