አውሮፓ ማዕከል ፲፫ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሔደ

ሐምሌ ፲፩ ቀን  ፳፻፭ .ም.

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ማኀበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ፲፫ኛ ጠቅላላጉባኤውን ከሐምሌ ፭ እስከ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ አካሔደ። በጉባኤው ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የመጡ የማኀበሩ አባላት፣ ካህናትና የማኅበሩን አግልግሎት በተለያየ መንገድ የሚደግፉ ምእመናንተሳተፉ ሲሆን ከዋናዉ ማዕከል ደግሞ ሁለት ልዑካን ተገኝተዋል። 

 GA2005 participants

የ፲፫ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል

 

ጉባዔው በማእከሉ የ፳፻፭ ዓ.ም. አገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ዉይይት አድርጓል። በዉይይቱም ወቅት የማዕከሉ የአንድ አመት ጠንካራና ደካማ ጎኖችና ተግዳሮቶቹ ቀርበዉ በተሳታፊዎች አስተያየት ከተሰጠባቸው በኋላ ሪፖረቱን አጽድቋል። 

EC members

የማዕከሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የ፳፻፭ ዓ.ም. የአገልግሎት አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ

 

ማዕከሉ በስብከተ ወንጌል፣ በአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ዙሪያ የተጠበቀበትን መስራቱ እንደ ጠንካራ ጎን ሲነሳ ካለዉ መጠነ ሰፊ አገልግሎት አንጻር የአባላት በቁጥር ማነስ እንዲሁም በህትመት ስርጭት ዙሪያ የታዩ ችግሮች ዋነኛ ድክመቶች ሆነዉ በተሳታፊዎች ተጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዋናው ማዕከል እየተተገበረ ስላለው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ሪፖርትና ቀጣይ ስራዎች፤ የማኅበረ ቅዱሳን ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭትና ቀጣይ ተግባራት፤ በአዉሮፓ ማዕከል የተደገፉ ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች  ዘገባ የቀረበ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በገዳማት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ለሚገኘው በኦስሎ የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማኅበር በተወካዩ አማካይነት ስጦታ ተበርክቶለታል። 

 

እንዲሁም ቅድስት ቤተክርስቲያን በውጭ አገር ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የማኅበሩ አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት የሚጠቁም ጥናታዊ ጽሑፍ  የቀረበ ሲሆን የጉባኤው ተሳታፊዎች ጥናቱ የአባላትን የግንዛቤ አቅም ከማሳደግና አቅጣጫዎችን ከመቀየስ አንጻር በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በመግለጽ እና ተጨማሪ አስተያየቶችን በማከል ጥናቱ በተሟላ መልክ እንዲቀጥል ሃሳብ ሰጥተዋል።

 

በማስከተልም ጉባኤው የአገር ውስጥ ማዕከላት እና ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ኃላፊ በዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል የቀረበለትን የዋናው ማእከል የአገልግሎት ሪፖርትና መልዕክት በዝርዝር አዳምጦ ውይይት አድርጎበታል።

 

በመጨረሻም ጉባኤው በ፳፻፮ ዓ.ም. የማእከሉ ዕቅድና በጀት ላይ በመወያየት ማሻሻያዎችን በማድረግ አጽድቆ፤ በ፳፻፭ ዓ.ም. የታዩት ድክመቶች በ፳፻፮ ዓ.ም. እንዲስተካከሉ በማሳሰብ የተጓደሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን በመምረጥ ጉባኤውን አጠናቋል።

 

የአውሮፓ ማዕከል ፲፫ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተሳካ ይሆን ዘንድ የኖርዌይ ግኑኝነት ጣቢያ አባላት እና ምእመናን ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ከተሳታፊዎች በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋና ተችሯቸዋል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።