የቅድስት ማርያም ዘር ነኝ

በዲን. ብርሃኑ ታደሰ

ግንቦት 1፣ 2004 ዓ.ም.

አባታችን አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ለሚያመልኩ ሁሉ ታላቅ የእምነት አባት ነው። በእርግጥም አምላኩን ፍጥረትን በመመርመር ማግኘቱ፣ አምላኩን ብሎ ቤተሰቡን ተለይቶ መውጣቱ፣ ልጁን ለመሰዋት ፍጹም ፈቃዱን ማሳየቱ ሁሉ ለእምነት አባትነቱ ማሳያዎች ናቸው። ከሁሉ የሚልቀው ከእርሱ አስቀድሞ ከሙታን መካከል የተነሱ ሳይኖሩ፣ ዘርህ በይስሐቅ ይጠራልሃል ከተባለ በኋላ ልጅህን ሰዋልኝ ሲባል፣ እነዚህን ሁለት የሚጣሉ የሚመስሉ ሐሳቦችን በእምነቱ አስታርቆ ማለት ቢሞት እንኳን ያስነሳዋል ብሎ አምኖ ልጁን ሊሰዋ ወደ ተራራ መውጣቱ ነው።(ዕብ11፥19) የሰው ሕሊና ጊዜ ሲያገኝ አንድን ነገር ደጋግሞ ማሰቡ አይቀርም፤ አብርሃም ግን የሦስት ቀን መንገድ ሲሄድ ይህ እምነቱ ንውጽውጽታ አልነበረውም – እፁብ ነው።Lideta_Le_Mariam_1

እኛ ክርስቲያኖች – የእግዚአብሔር ወልድን ሰው መሆን፣ ለኛ ብሎ መከራ መቀበል፣ በኋላም የቤዛነቱን ሥራ ሲፈጽም በአባቱ ክብር መቀመጡን ስለምናምንና ስለተጠመቅን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል። ይህ ልጅነት በፊት እንደነበረው ከሥጋ የመጣ አይደለም፤ መጽሐፍ – “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ግን መንፈስ ነው።” እንዲል፤ ልጅነታችን በጸጋ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ነው። (ዮሐ3) ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ይህንን ሲያጸናው የተወለድነው ከሚጠፋ ዘር አይደለም ይለናል። (1ጴጥ1፥22)

ክርስቲያኖች የመሆናችን ምንጭ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ደግሞ የተወለደው ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ነው። ከድንግል ማርያም የተወለደው እርሱ እኛን በጸጋ ልጆች የምንባልበትን ስልጣን ሰጠን፤ ስለዚህም እናታችን ማርያም እንላለን፣ በሙሉ ጥብዐትም የቅድስት ማርያም ዘር ነን እንላለን። እንግዲህ ሰው የትኛውን ይጠራጠራል? በክርስቶስ ክርስቲያን መሰኘቱን ነው ወይስ ክርስቶስ ከቅድስት ማርያም መወለዱን? ወይንስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጡን? በአንድ ስፍራ ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋው ለሁሉም እንደተሰጠና የሚሰጥበትን ምክንያት ሲገልጽ “እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ (ለአሕዛብ) ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” ይላል። (ሐዋ11፥17) ዳግመኛም “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ።” ይላል።(ሉቃ1፥30) በሌላም ስፍራ “ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” ይላል። (1ዮሐ4፥3) ስለዚህ ተጠራጣሪ አይኑር ይመን እንጂ።

አቡቀለምሲስ ወይም ባለ ራዕይ የሚባለው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ካያቸው ራእዮች መካከል አንዱ የክርስቲያኖች እናት እና መመኪያ ስለሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ነው። ይህንንም በአስራ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ አስቀምጦታል። የሚጀምረውም ስለክብሯ፣ ከዚያም ስለወለደችው ልጅ፣ በዚህም ምክንያት ስለመጣባት መከራ፣ መከራውም ወደ ዘሮቿ እንደዞረ ያስረዳል። ስለክብሯ፦ “ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።”(ቁጥ 1) ይላል። ስለወለደችው ልጅም፦ “አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች” (ቁጥ 5) ይላል። አሕዛብን ሁሉ የሚገዛ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱን የወለደች ደግሞ ቅድስትና ድንግል ማርያም ናት። ስለዚህም ምክንያት “ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።” (ቁጥ 13) ይለናል – ወደ ግብጽ ስለመሰደዷ። በመጨረሻም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚጠብቁትን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች የሆኑትን እንደሚያሳድድ ሲገልጽ፦ “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤” ከዘርዋ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሴቲቱን ዘር ነው፤ ይህች ደግሞ የመመኪያችን ዘውድ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ዘርዋ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች የሆኑትን ነው። ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም፦ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” ብሎ፣ በእርሱዋ የደረሰ በዘሮቿም እንደሚደርስ አስረግጦ ተናግሯል። (2ጢሞ3፥12)

በአብርሃም ልጅ በይስሐቅ ደም ዓለም እንደማይድን ተነገረ፤ በእመ አምላክ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ግን ክብርን አገኘን። በሥጋ ተወልደው የአብርሃም ዘር የሆኑት ከነዓንን ለመውረስ ተስፋ አደረጉ፤ እኛ በመንፈስ ከአብርሃም ተወልደን የድንግል ማርያም ዘር የሆንነው ደግሞ መንግስተ ሰማያትን ተስፋ እናደርጋለን። እነርሱ ከነዓንን ለመውረስ ብዙ ሰልፍ አደረጉ፤ እኛ መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ መንፈሳዊ ውጊያ እናደርጋለን። እነርሱ በመገረዛቸው ይመካሉ፤ እኛ ግን በጥምቀት ባገኘነው የጸጋ ልጅነት እና የድንግል ልጅ በመስቀል ላይ ባደረገልን ውለታ እንመካለን። እነርሱ ማመን ለሥጋ ዘመዶቻቸው ብቻ እንደሆነ ያስባሉ፤ እኛ መዳን ለሁሉ እንደተሰጠ እናምናለን። እነርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት መሲህ ወደ ዓለም አልመጣም ይላሉ፤ እኛ የነቢያት እውነተኝነት ይገለጽ ዘንድ ሰውን ለማዳን የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ድንግል ማርያም ወልዳልናለች ብለን እንመሰክራለን። እነርሱ በሥጋ የአብርሃም ዘር ነን እያሉ ይመካሉ፤ እኛ በመንፈስ የአብርሃም ልጆች፣ የድንግል ማርያም ዘር በመሆናችን እንመካለን።

እናታችን ማርያም ሆይ ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አሜን።