ዓቢይ ጾም

የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

በአባ ዘሚካኤል ሬሳ 

እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ለመጾም አደረሳችሁ!!!

ጌታችን መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ። አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ጾመ። ከዛም ፈታኝ ዲያብሎስ ቀርቦ በስስት፣ በትእቢትና በፍቅረ ነዋይ ፈተነው። ጌታችንም ፈተናዎቹን በጥበበ አምላክነቱ ድል በማድረግ ድልን ለአዳምና ለእኛ ለልጆቹ ሰጠን (ማቴ. 4፡ 1 – 11)

በቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ጾም አስተምህሮ መሰረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾመ ሁዳዴ ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ይህም የቀደመው አዳም በጾም ግድፈት ምክንያት ማለትም አትብላ የተባለውን በመብላት ወድቆ፣ተዋርዶ፣ ኃይሉን አጥቶ፣ ዲያብሎስ ሰልጥኖበት፣ ስጋ ፈቃድ አይሎብት፡ የዓለም አምሮት ማርኮት ሞትና የሞት ሞት ሰልጥኖበት ነበረ። ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ተወልዶ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ፣ ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር አረጋግጦ፣የአዳም ጾም መሻርና የመዋረዱን ክስረት ለመካስ ጌታም ይህን ጾም በመጾም የአዳምን ክብረት መልሶለታል

ሁለተኛም አዳም አትብላ የተባለውን በመብላቱ ዲያብሎስ ተቆራኝቶ ሰልጥኖበት ነበረና ጌታችን በመጾም ለሰው ልጅ ቁራኝነትን አጥፍቶለት ጾምን ኃይል አድርጎ ሰጠው። በመሆኑም ሰው ጾምን ቢጾም ጸሎትን ቢያዘወትር ቁራኛ ጋኔን በጾም በጸሎት ተቀጥቅጦ እንዲለቀውና ከርሱ ተለይቶ ተኖ በኖ እንዲጠፋ መጻሕፍት ያስረዳሉ። ጌታችን በወንጌለ ማቴዎስ(17: 19- 21) እንደተገለጸው “ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርቡና እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ስለምን ነው? …..አሉት ኢየሱስም ይህ አይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም አላቸው” ከዚህ ትምህርት የምንረዳው ጾም ለሰው ልጆች ከአጋንንት ቁራኝነት የሚያላቅቅ መንፈሳዊ ኃይል መሆኑን ነው

ሶስተኛም አዳም አትብላ የተባለውን በመብላቱ የስጋ ዓይኖቹ በመከፈታቸው ፈቃደ ሥጋ አይሎበታል። ጌታችንም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ የሥጋ ፈቃድን በመግዛት ድል ነስቶ ለኛ ኃይል ሆነን ስለ ፈቃደ ሥጋ መነሳሳት መገለጫው በመጀመሪያው የበደል ወራት” … ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከርስዋ ጋር በላ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ። እነርሱም እራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ …” በማለት ሊቀ ነቢያት ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት 3፡  6-7 ገልጾታል። የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ሲል ቀድሞ ምንም አያይም ማለት አይደለም። ማየትማ የገነትን መንፈሳዊ ውበት በገነት ያሉትን እንስሳትንና እጽዋትን ያያል።  በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ ሁለት ላይ አዳም ለያንዳንዱ እንስሳት ስም እያወጣላቸው፣ በየስማቸው ሲጠራቸው እናነባለን ይህም በዓይኖቹ እየተመለከታቸው በቃሉ እያናግራቸው ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ለምን ዳግመኛ የሁለቱ ዓይኖች ተከፈቱ አለ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱን ቀጥሎ ያለው ዓረፍተ ነገር ይጠቁመናል። ይህም “እነርሱም እራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ” የሚለው ነው። አዳምና ሄዋን በገነት እራቁታቸውን ለሰባት ዓመት ሲኖሩ ስለ እርቃን መሆን እውቀት አልነበራቸውም። ወይም እጸበለስን ከመብላታቸው በፊት ሁለቱም በስጋ ፈቃድ ስሜት ውስጥ ሆነው ይተያዩ አልነበረም ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የስጋ ፈቃድን አያውቁዋትም። የሥጋ ፈቃድ በእነርሱ አልሰለጠነችባቸውም ነበር። ስለዚህ አትብሉ የተባሉትን በበሉ ጊዜ የስጋ ፈቃድ በሰውነታቸው ሰለጠለጠነችባቸው። አዳም የራሱንም ሆነ የሄዋንን እርቃን ተመለከተ። በመሆኑም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሥጋ ፈቃድ በሰው ልጅ ሁሉ ሰለጠነ። በዘመነ ሥጋዌው በሰው ልጆች ዘንድ የሰለጠነውን የስጋ ፈቃድ ለማሸነፍ ጌታችን ጾመ። በሰው ልጅ በማየት፣ በመስማት፣ በመብላት፣ በመጠጣት፣ ወዘተ ፈቲው ፈቃደ ሥጋ ሰልጥኖበት አምስት ሺህ አምስት መቶ የኖረውን ጌታም ከድንግል ተወልዶ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ከሰው ተለይቶ ከመብላት ከመጠጣት ወዘተ ተከልክሎ ፈቃደ ሥጋን ረታ። ለሰው ልጆችም በጾም በጸሎት መትጋትን ፈቃደ ሥጋን መርታትን ሰጠ

ፍጻሜውም አዳም አትብላ የተባለውን በመብላት የሞት ሞት የተፈረደበት ቢሆንም ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ጾመ አርባን ጾሞ አዳምን ከሞት ሞት አድኖታል። እባብ ለሄዋን በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟልን? የሚል ጥያቄ በጠየቃት ጊዜ: እሷም ከገነት መካከል ካለው ዛፍ “እንዳትሞቱ ከርሱ አትብሉ አትንኩትም” (ዘፍ 3፥3) ብሎናል በማለት መልሳለች።  ከዚህ ዓረፍተ ነገር “እንዳትሞቱ ከርሱ አትብሉ” የሚለው የሚያመለክተው ቢበሉ ሞት እንደሚሰለጥንባቸው ነው ይህም አልቀረም፤ እነሱም በድፍረት በሉ: ጌታችን መጥቶ መብላትን በጾም ረትቶ እስከሚያድናቸው ድረስ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የሞት ሞት ሰለጠነባቸው

እንግዲህ ጾም ለሰው ልጆች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አጋንንትን ድል የምንረታበት ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል ተደርጎ ተሰጥቶናል። ይህም ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ዲያብሎስ ቀርቦ በስስት: በትእቢትና በፍቅረ ነዋይ ፈትኖታል። ጌታችንም ስስትን ሰው በእንጀራ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እንደሚኖር በማረጋገጥ: ትእቢትን እግዚአብሔርን አትፈታተኑ በማለት፣ ፍቅረ ንዋይን ለገንዘብ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ብቻ መገዛት እንዲገባ በጥበበ አምላክነቱ ምላሽ ሰጥቶ ድልን ለአዳምና ለኛ ለልጆቹ ሰጠን። እኛም በዚህ ዘመን ያለን የሰው ልጆች ከላይ እንደተዘረዘረው በአዳም የነበረ የመብላት ፈተና፣ የስጋ ፈቃድ፣ የሰይጣን ጾር፣ ከቀድሞ የበለጠ እየተፈታተነን ስለሆነ በዚህ የዓቢይ ጾም ተሳትፈን በረከትንና ኋይልን እንድናገኝ ቃሉ ግድ ይለናል

ከላይ በዝርዝር እንዳየነው በመብል ምክንያት በአዳም የደረሰ ፈተናን እና ጾምን አለመጾም የሚያመጣውን ጉዳት በእኛ ህይወት መስለን ስናየው፡

  1. አዳም ተታሎ አትብላ የተባለውን ህግ ጥሷል። ይህም እንዳሰብው ወይም በዲያብሎስ እንደተነገረው በእውቀት ከፍ ከፍ አላደረገውም ይልቁኑ ለውርደት አብቅቶታል። በተነጻጻሪም ይበልጡኑ በዚህ ዘመን በተለይ ሰለጠን በሚሉት ዘንድ ላለመጾም የተለያየ ምክንያት እየተረደረ ጹሙ የተባለውን ማፍረስ ገኖ ያየለበት ጊዜ ነው። ጹሙ ከሚለው ይልቅ የአትጹሙ አማካሪው ብዛት ቁጥር አያሌ ሁኗል። አንዳንድ የዚህ ዘመንም አማካሪዎች ጹሙ የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል እየሻሩ አትጹሙ ብለው የእባብን የዲያብሎስን ስራ ሲሰሩ ይታያል። ከነዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ ጓደኛ: ጎረቤት: ሀኪም ወዘተ እና አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሳይቀሩ ለጾም አድልዎ ሳይሆን ለመብላትና ለማስበላት ዘብ የቆሙ ይመስላሉ። ነገር ግን ጹሙ ማለት ጹሙ እንጂ ላለመጾም ምክንያት ደርድሩ ማለት አይደለም። ሰው ቢጾም ኃይልና በረከትን ያገኛል። ጹሙ የተባለውን ንቆ ባይጾም ያለምንም ጥርጥር እንደ አዳም ከበረከት እና ከመንፈሳዊ ኃይል ይለያል። ለስህተቱ አዳም ሄዋን ናት: ሄዋን እባብ ነው፣ ለዚህ ያበቃኝ በማለት ምክንያት በመደርደር ከፍርድ እንዳላመለጡ ሁሉ ማንም በምክንያት ድርደራ ከፍርድ አምልጦ በረከትና ኃይል ሊያገኝ አይችልም። ስለዚህ ይህ አቢይ ጾም አዳም በመብላት ያጣውን በረከትና ኃይል ጌታችን በመጾም መልሶለታል። ከዚህም ጾም የተሳተፈ ሁሉ መንፈሳዊ በረከትና ኃይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል።
  2. አዳም ህግን ጥሶ አትብላ የተባለውን ቢበላ የእግዚአብሔር ጸጋ ተለይቶት ዲያብሎስ ተቆራኝቶት ነበር። ዛሬም ዓቢይ ጾምን እና ሌሎችን አጽዋማት የማይጾሙና የማያምኑባቸው ከጸጋ እግዚአብሔር ይልቅ ሰይጣን ይቆራኛቸዋል። ሰው ከመጾም ይልቅ ለመብላት ሲያደላ የስስት መንፈስ ይጸናወተዋል፤ ሰይጣን ይቆራኘዋል። ጌታችን በጾመ ጊዜ ፈታኝ ቀርቦ ይህን ድንጋይ ዳቦ አድርግና እንብላ ነበር ያለው። ቀድሞ አዳምን በመብላት ውድቀት ድል ነስቶት እንደተቀቆራኘው ጌታችንንም በለመደው ፈተና ሊያጠምደው ሽቶ ያንኑ የማጥመጃ ጥያቄ አቀረበለት። ጌታ ግን ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በማለት ረታው። ዛሬም ዲያብሎስ በመብል ሊቆራኘን ሽቶ በየምክንያቱ የመብል ወጥመድን ሲሰረጋብን ወጥመዱን ጌታችን በሰጠን መንገድ ተጠቅመን በጾም ልንሰብረው ይገባል
  3. አዳም እጸ በለስ በመብላቱ ፍትወተ ስጋ እንደሰለጠነበት ሁሉ ክርስቲያንም በጾም ሰውነቱ እንዲገዛ ካላደረገው የዓለም ፍቅር: ፍትወተ ስጋ ያይልበታል። መብል መጠጥ የፍትወተ ሥጋ ምንጭ ናቸው። ለዘህም አቢይ ጾምን መጾም ፈቲውን ጋብ እንዲል ያደርገዋል። 

በአጠቃላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአቢይ ጾም አማካኝነት በሰው ልጆች ላይ በመብል የሚመጣውን የሰይጣን ፈተና ድል በማድረግ ክርቲያኖች በጾም ቢተጉ የእግዚአብሔርን ህግ ጠብቀው ለመኖር አእምሮአቸው ማስተዋልን፣ህይወታቸው ከሰይጣን ቁራኛ ነጻነትን፣ ሰውነታቸው እና የሥጋ ብልቶቻቸው ከፍትወተ ሥጋ ማእበል መገታትን ያጎናጽፎአቸዋል። በመሆኑም ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ጌታችን የጾመው ድኅነት እንድናገኝበት ስለሆነ ጾሙን በፍቅር ጾመን ድኅነት፣ በረከትና ፈውስ እንድናገኝ የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን፡ አሜን። ጾመን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ያሳድርብን አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!