የገና በዓል በቅዱስ ላሊበላ

በቀሲስ መንግስቱ ጎበዜ

ታህሳስ 27 ቀን 2008 ዓ.ም

በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን በድምቀት ከሚከበሩት የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓበይት በዓላት መካከል ገና (የልደት) በዓል አንዱ ነው።ይህ በዓል ሰማይና መሬት የታረቁባት፣ ሰው እና መላእክት በአንድነት የዘመሩበት ከሁሉም በላይ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠበቅ የነበረው የአዳም ተስፋ የተፈፀመበት፣ አምላክ የአምላክ ልጅ በግሩም ተዋህዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደበት ታላቅ የደስታ ቀን ነው።

ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ይህ በዓል በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በብሔራዊ በዓልነቱ ቢታወቁም በጥንቷ ሮሃ በዛሬዋ የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ያለው አከባበር ግን አጅግ የላቀ የደመቀ እና የተለየ ነው።የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 800 ኪሜ ርቀት ገደማ የምትገኝ 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ንግስናንከክህነት አጣምረው ከያዙት አራቱ ቅዱሳን መካከል አንዱ በሆነው በቅዱስ ላሊበላ ስም የተሰየመች፣ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧም ቀይ መሬት በሆነ ኮረብታ የምትታወቅ እና ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሙዚየም ነች

በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ከ800 ዓመት በፊት ድንቅ በሆነ የአሠራር ጥበብ ታንፀዉ በዘመናችን በትንግርት ማዕከልነታቸዉ የሚጠቀሱ ሆነዋል። እንደ ሰንሰለት ተያይዘዉ ከተማዋን ያደመቁት አብያተ ክርስቲያናቱ ዮርዳኖስ ተብሎ በሚጠራዉ አነስተኛ ሸለቆ ተለያይተዉ በሦስት ምድብ ተከፍለዉ ይገኛሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከመሠረት እስከ ጣራ፣ ከመቅደሱ እስከ ቅኔ ማህሌት ድረስ ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለዉ የተሰሩ በልዩ ልዩ ቅርጾች ያጌጡና አንዱ ከሌላዉ ጋር የማይመሳሰሉ ናቸዉ።ከመደበኛዉ የህንፃ አሠራር ሁኔታ በተለየ መሠረታቸዉ የተጣለዉ ከጣራቸዉ ላይ መሆኑ ደግሞ የተለየ አግራሞት የሚፈጥር ነዉ።

lalibela

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን 1520 . በመጎብኘት የመጀመሪያ የሆነዉ አዉሮፓዊ የፖርቱጋል ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ጉብኝቱንእጅግ በጣም አስደናቂ እና ከፍተኛ የጥበብ ችሎታ የሚታይበት ዕፁብ ድንቅ ሥራ በመሆኑ ያየሁትንና የተሰማኝን ነገር ሁሉ ብጽፍ የሚያነኝ ስለማይኖር በእግር ተጉዘዉ ሄደዉ በአይናቸዉ ለሚያዩት ትቻለሁበማለት አጠቃሎታል።የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የአህመድ ግራኝንም የጭካኔ ልብ የሰበሩ የጥበብ መዶሻዎች ናቸዉ።አህመድ ግራኝ 16ኛዉ መቶ / ወረራዉ አብያተ ክርስቲያናቱን አድንቆ ሳይነካቸዉ ትቷቸዉ እንደ ሄደ የጽሑፍ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ ከሌላው አካባቢ በተለየ ሁኔታ የገና በዓል በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የሚከበርበት ዋና ምክንያት ቅዱስ ላሊበላ የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በታህሳስ 29 ቀን በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የዚህ ጻድቅ ንጉስ የልደት ቀን ከጌታችን የልደት ቀን ጋር በመግጠሙ የልደት በዓል በቦታው እንዲከበር ምክንያት ሆነ፡፡ በገድሉም እንደተጻፈው ቅዱስ ላሊበላ የተወለደው ታህሳስ 29 ቀን 1101 . ከአባቱ ከንጉስ ዛም ስዩም እና ከእናቱ ከኪርወርና ነው፡፡ ኪርወርና በጥንቱ የአገውኛ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደሆነም ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ነጫጭ ንቦች ስለከበቡት እናቱ ይህንን አይታ ልጇን ንብ በላው ለማለት በአገውኛ ላል በላ እንዳለችውና በሂደትም ስሙ ላል ይበላ /ላሊበላ/ ተብሎ መጠራት እንደጀመረ በገድሉ ተገልጿል፡፡

ድንቅና ማራኪ የሆነው የገና በዓል ሥርዓት የሚከናወነው በቤተማርያም ቤተክርስቲያን ዙሪያ እንደ አጥር ከቦ ከሚገኘውና በተለምዶ ማሜ ጋራ ተብሎ በሚጠራው ኮረብታማ ዓለት ላይ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ካህናቱ ከላይ ከኮረብታውና ከታች ከቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ሆነው በመላእክትና በእረኛ ምሳሌ የሚያመሰግኑት ‹‹ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ›› የሚለው ዝማሬ ልብን የሚመስጥና 2 ሺህ ዓመት በፊት የተከናወነው መንፈሳዊ ታሪክ በምናብ የሚያስቃኝ ነው፡፡ በገና በዓል ሰሞን የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪው ዓለምበሚመጡ አማኞችና ጎብኚዎች ትጥለቀለቃለች፡፡በመሆኑም እንደ አቢያተክርስቲያናቱ የገና በዓልም የከተማዋ ዋነኛ መታወቂያ ሆኖ ይገኛል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ከተማ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ዳግማዊ ኢየሩሳሌምበመባል ትታወቃለች፡፡የመጀመሪያው ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ለመሳለም ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ሥቃይ ለመቀነስ ቅዱስ ላሊበላ ኢየሩሳሌም በሚገኙ ቅዱሳን መካናት አንፃር በቦታው አብያተ ክርሰቲያናቱን በማነፁ እንደሆነ ይታመናል፡፡ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌም ሄደው የሚያገኙትን መንፈሳዊ በረከት ብዙ ችግር ሳይገጥማቸው አገራቸው ለማግኘት እንዲችሉ ታስቦ አብያተ ክርስቲያኑ እንደታነፁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያንን ተሳልሞ በቀጥታ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሄዶ እንደተሳለመ ይቆጠርለታል በማለት ለቅዱስ ላሊበላ በገድሉ የተሰጠውን ቃል ኪዳን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

በቅዱስ ላሊበላ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የልደት በዓል መንፈሳዊ በረከት የሚታፈስበት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ትእይንት፣ለጭስ አልባው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰፊ ድርሻ ያለው እና ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና የሚጫወት የቅርስ ሀብታችን ነው።ስለሆነም ይህ ለቤተክርስትያናችንም ሆነ ለአገራችን የማይተካ ሚና ያለው መንፈሳዊ ሀብታችን በአግባቡ ተጠብቆና ታውቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ተገቢ ነው

ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በረከትን ያድለንየቅዱስ ላሊበላ ምልጃና ፀሎት ከሁላችን ጋር ይሁንአሜን!

መልካም በዓል