‹‹መስቀል ለእለ ነአምን መድኅን›› ቅዱስ ያሬድ

በመጋቢ ሀዲስ ምስጢረ ስላሴ ማና

መስከረም 16 ቀን 2009 ዓ.ም.

‹‹መስቀል ለእለ ነአምን መድኅን – መስቀል ለምናምን መድኒት ነው››። ስለነገረ መስቀሉ ከተናገሩ ሊቃውንት የኢትዮጵያው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ትልቅ ድርሻ አለው። በአምስቱም ድርሰቶቹ በሰፊው ስለ መስቀል ዘምሯል፣ ተናግሯል፣ አመስጥሯል። ከላይ ያነሳነውን ኃይለ ቃል የተናገረውም እርሱ ነው። ምክንያቱም የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ስለ ነገረ ድኅነነት ያጠነጥናሉ። እግዚአብሔር በነገረ ድኅነት ውስጥ ለሰው ልጆች ሁለት የተስፋ መንገዶች ሰጥቷል። አንደኛው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቅዱስ መስቀሉ ነው።

ሁለቱም የተሰጡት የሰው ልጅ ከገነት ሕገ እግዚአብሔርን ጥሶ፣ ትእዛዙን አፍርሶ፣ ዕፀ በለስን በልቶ፣ ከፈጣሪው ተጣልቶ በተሰደደ ጊዜ ነበር። ‹‹በሐሙስ እለት ወበመንፈቃ ለእለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ- በአምስት ቀን ተኩል /አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም/ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀሌና በሞቴ አድንኀለሁ›› ቀሌምንጦስ ከልጅ ልጅህ ያለውን ሊቃውንት ‹‹እንተ ይእቲ ማርያም-ይችውም ማርያም ናት›› ብለው ተርጉመውታል። ስለዚህ ሊቃውንቱ ይህ የተሰጠው የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ በእለተ ጽንስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ተጀመረ፤ በእለተ ዓርብ በቅዱስ መስቀል ተፈጸመ ብለው አስተማሩ። ‹‹ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል – የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ በቀራንዮ መድኃኒት መስቀል ተተከለ›› ብለው ገለጡት። በድርሰታቸው መድኃኒትነቱን ለምናምን መሆኑን ሁላችንም እርግጠኛ መሆን ይገባናል። ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ ወናሁ ተፈጸመ ኩሉ- የሰጠኸኝን ሥራ ጨረስኩ እነሆ ሁሉ ተፈጸመ ።›› (ዮሐ 17፥4) ያለው ለዚህ ነበር። ከዚህ የተነሳ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ መስቀሉን ታከብረዋለች፤ ስለ ክብሩ ትናገራለች።

ቅዱስ ያሬድ ‹‹በመስቀሉ ገብረ መድኃኒተ በመስቀሉ አርኅወ ገነተ – በመስቀሉ ድኅነትን አደረገ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› እንዳለ። ዳግመኛም ‹‹በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ- በመስቀሉ እና በቃሉ አባቶቻችንን ከፍ አደረጋቸው›› ሲልም ከፍ ማድረግ ከሲኦል ባርነት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሞት ተገዥነት ነው።

መስቀል ከሁሉ አስቀድሞ ዓለምን ለማዳን ምልክት ሆኖ የተሰጠ መሆኑን ነቢያት ሰብከውታል። ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኀኑ ፍቁራኒከ – ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሀቸው ከጠብ ከወቀሳ ከጦር ያመልጡ ዘነድ ወዳጆችህም ይድኑ ዘንድ›› (መዝ 59፥4 ) እንዳለ። ስለዚህ ነው መስቀል ለምናምን መድኃኒት ነው የምንለው የመዳን ምልክት ሆኖ ተሰጥቷልና። ‹‹ወነገረ መስቀሉሰ እበድ ውእቱ በኀበ ህጉላን ወበኀቤነሰ ኃይለ እግዚአብሔር ወጥበበ እግዚአብሔር ወእቱ – የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል እና ጥበብ ነው›› 1ቆር 1፥18።

በተጨማሪም መስቀል ኃይላችን ነው እንላለን የክርስቶስ ኃይሉ ተገልጦበታልና። ጠላታችን ዲያብሎስ አፍሮበታል ተዋርዶበታል አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን የሞት ባሪያ የመቃብር ተገዥ ሆኖ የኖረ የሰው ልጅ ነጻነቱን አውጆበታል። የራቁ ቀርበውበታል በኃጢአት የቆሰሉ ተፈውሰውበታልና።

ሰሎሞን እንዲህ ይላል ‹‹ሐረገ ወይን ኮነ መድኃኒትየ ዘእም ሐሲሦን ይትገዘም ወበጎልጎታ ይተከል – የወይን ሐረግ መድኃኒቴ ሆነ ከሐሲሦን ይቆረጣል በጎልጎታም ይተከላል።›› የወይን ሐረግ የተባለው በቀራንዮ የተተከለው፣ የክርስቶስ ደም የቀደሰው፣ ሰው የዳነበት፣ ዕፀ ስርየት ዕፀ መድኃኒት መስቀል ነው። ለምናምን መድኃኒት፣ ለማያምኑ ሞኝነት፣ ለምናምን ድኅነት ለማያምኑ ጥፋት፣ ለሚያምኑ ሕይወት ለማያምኑ ሞት። ከመስቀሉ አጠገብ ቅድስት ድንግል ማርያም ነበረች። ሌሎችም ቅዱሳት አንስት የሚወደውም ደቀ መዝሙር ነበሩ። (ዮሐ 19፥25) መስቀሉን ስንመለከት የዓለሙን ፈጣሪ፣ ቅዱሳን መላእክትንም እናያለ። የጌታችንን መከራውን እና የተደረጉ ድንቅ ተአምራትን እናስታውሳለን። ስለዚህ መስቀልን ማክበር ማለት የእለተ ዓርብን የጌታችንን መከራ ማሰብ ነው፤ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ ነው።

እንደ እመቤታችን እና እንደ ቅዱስ ዮሐንስ በእውነት ለማገልገል ፈጣሪውን ለመከተል ያሰበ መስቀሉን ሊሸከም ግድ ነው። ‹‹ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ – መስቀሌን የማይዝ በኋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ፤ ሊያገለግለኝም አይችልም።›› ( ማቴ 10፥38 ማቴ 16፥24) ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የክርስትና አርማ መስቀሉ መሆኑን ነው። በመሆኑም ሐዋርያት በትምሕርታቸው ትልቅ ስፍራ ሰጥተውታል። ሊቃውንትም ሐዋርያትን መሠረት አድርገው አስተምረዋል። የመስቀሉ ነገር እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም። በነቢያት የተነገረለት በሐዋርያት የተሰበከለት በሊቃውንትም የተመሰከረለት ነው። ቅድስት ቤተክርስቲያንም ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሊቃውንትን ዋቢ አድርጋ ነው መስቀሉን የምታከብረው። በተጨማሪም መስቀል መርገማችን የተሻረበት፣ በደላችን የተደመሰሰበት፣ ዲያብሎስ ድል የተነሳበት፣ ጋሻችን ነው። ‹‹አስተኀፈረ ኃጢአተ በዲበ ምድር ወሰዐረ መርገመ በዲበ ዕፀ መስቀል ወአብጠለ ሞተ በውስተ ሲኦል ወነሰተ ሙስና በውስተ መቃብር – ኃጢአትን በምድር ላይ አሳፈረ- መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ በሲኦል ሞትን አጠፋ ሙስና መቃብርን በመቃብር አፈረሰ›› እንዲል።

ይህ ድንቅ ሥራ የተሠራበት በመሆኑ መስቀልን እናከብረዋለን። መስቀል ኃይላችን እያልን በጸሎታችን መካከል እናነሳለን። ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ይላል ‹‹ኃይልነ ወጸወንነ ወሞገስነ ዝንቱ ውእቱ መስቀል – ይህ መስቀል ኃይላችን መጠጊያችን ሞገሳችን ነው›› ኃይላችን ብቻ ሳይሆን መመኪያችንም ነው፤ መመኪያችን መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል። ‹‹አንሰ ሀሰ ኢይዜሀር ዘእንበለ በመስቀሉ ለእግዚእየ ኢየሱስ – ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።›› (ገላ 6፥14 )

መስቀል ክብር ይግባውና መድኃኔዓለም ለሰው ልጅ ፍቅሩን የገለጠበት የፍቅር ትምሕርት ቤት ነው። በመስቀል ፍቅሩን ብቻ አይደለም ትሕትናውንም ገልጦበታል። ‹‹እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።›› (ፊል.2፥8) ከዚህ ተነስተን መስቀልን ስናከብር ፍቅርን ትሕትናን እንማራለን። የፈጣሪያችንን ቸርነት እንረዳለን በመስቀሉ ከመርገም ዋጅቶናልና ‹‹ወለነሰ ተሳየጠ ክርስቶስ እመርገማ ለኦሪት – እኛንስ ክርስቶስ ከመርገም ዋጀን።›› (ገላ 3፥14) መስቀል መርገማችንን ወደበረከት ሞታችንን ወደ ሕይወት ጥፋታችንን ወደ ድኅነት ውርደታችንን ወደክብር ሞታችን ወደትንሳኤ የለወጠ የሰላማችን ምንጭ ነው። ‹‹ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ እለ ውስተ ሰማይ ወእለ ውስተ ምድር ወዘታሕቴሃ ለምድር እስመ ውእቱ ሰላምነ ዘረሰዮሙ አሐደ ለክልኤሆሙ ወነሰተ አረፍተ ማእከል ወለጽዕል ቀተሎ ቦቱ – በመስቀሉ ሰላምን አደረገ በሰማይና በምድርም ውስጥ ላሉት ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነው ጥልን በመስቀሉ ገድሎ።›› (ኤፌ 2፥16)

በአጠቃላይ መስቀል የሰላም ምልክታችን በመሆኑ እናከብረዋለን። ጠላታችን ድል የተነሳበት ነውና እንሸከመዋለን። ምክንያቱም ጠላቶቻችን አጋንንትን እንወጋበት ዘንድ ከእግዚአብሔር ተሰጥቶናል። ቅዱስ ያሬድ ‹‹ብከ ንወግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ ወበስምከ ነኀስሮሙ ለእለ ቆሙ ላእሌነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ እፀ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ – ዳዊት ትንቢትን በሚገልጥ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለ ጠላቶቻችንን በአንተ እንወጋቸዋለን በሥምህም እናሳፍራቸዋለን ይንንም ያለው የአብ አካላዊ ቃል ስለ ተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ነው›› እንዳለ። በሌላ መልኩ እንደዚህ ይላል ሊቁ ‹‹መስቀል መልዕልተ ኲሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር – ከሁሉም ነገር በላይ የሆነ መስቀል ከጠላት ያድነናል።›› የምናክብረውም ለዚህ ነው። የመስቀል ጠላቶች ከእለተ ዓርብ ጀምሮ የምላስ ጦራቸውን ስለው፣የቅናት እና የምቀኝነት ምላሳቸውን አጠንከረው፣ መስቀልን ከምእመናን ልቡና ለማጥፋት መላ ጊዜያቸውን አጥፍተዋል፤ ሊያጠፉት ግን አልቻሉም ኃይል አለውና። አይሁድ መስቀሉን ለ300 ዓመታት ጥራጊ ደፍተውበታል። እነርሱ የሉም መስቀሉ ግን አለ። ዛሬም የመስቀሉ ጠላቶች ይጠፋሉ እንጂ መስቀሉ እየጎላ ነው የሚሔደው። ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኳችሁ፤ አሁንም እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው አሳባቸው ምድራዊ ነው›› እንዳለ።(ፊል 3፥19)

እኛም ዛሬ በዚሕ በዓላችን እንደ ቅዱስ ያሬድ ‹‹እሌኒ ንግሥት ኀሠሠት መስቀሎ እንባቆም ነቢይ ዘአንከረ ግብሮ – ንግሥት እሌኒ መሰቀሉን ፈለገች ነቢይ እንባቆም ሥራውን አደነቀ›› እያልን መስቀሉን እንደ እሌኒ ልናደንቅ ልናመሰግን ይገባናል።

አምላካችን በሀጹረ መስቀሉ ይጠብቀን

የመስቀሉ በረከት ይደርብን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር