ሐዊረ ሕይወት በሀገረ ጀርመን ተካሄደ
በጀርመን ቀጣና ማእከል
ግንቦት 15 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጣና ማእከል በአውሮፓ የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከግንቦት 8-10, 2006 በክሩፈልባክህ (Kroeffelbach) በሚገኘው የኮፕቲክ ቅዱስ እንጦንስ ገዳም (Sankt-Antonius Kloster) በደማቅ ሁኔታ አካሄደ። በዚህ ከ80 በላይ ምእመናን በተሳተፉበት መርሐ ግብር ላይ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በተለይ ነገረ ድኅነት እና መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የተሰጡት ጥልቅ ትምህርቶች ተሳታፊዎች በጉዳዮቹ ላይ የነበራቸውን እውቀት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደጉ እና ታዳሚው ሐዊረ ሕይወት በቅርቡ ይደገምልን የሚል ጥያቄን እንዲሰነዝር ያነሳሱ ነበሩ። በተጨማሪም መዝሙራት በዘማርያንና በሕብረት የቀረቡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በተለይም በተመረጡ ጠረፍና ገጠር አብያተክርስቲያናት ላይ አቅዶ እያከናወነው ስላለው የስብከት ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ገለጻ ተደርጓል።