ዜና

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዐውደ ርእይ ተካሄደ

“ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!” በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል የጀርመን ን/ማዕከል የተዘጋጀ ዐውደ ርእይ ከነሐሴ ፬ እስከ ፮  ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. በጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ ተካሄደ።

ዐውደ ርእዩን በጸሎት የከፈቱት ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የአውሮፓ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ሲሆኑ  በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ እና በአካባቢ የሚገኙ የአብያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ተጋባዥ መምህራን እና እንግዶች ተገኝተዋል። ብፁዕነታቸው ዐውደ ርእዩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልእክት  ስለቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ አስተምህሮ እና ወቅታዊ ችግሮች የሚያስገነዝቡ እንደዚህ ዓይነት መርሐግብራት ሊበረታቱ የሚገባቸው መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም በቅርቡ የተፈጸመውን የቤተክርስቲያን  አስተዳደራዊ አንድነት ለማጽናት ካህናት እና ምእመናን በርትተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው እና ይህንንም በፍቅር እና በመከባበር መንፈስ አብሮ በማገልገል መግለጽ ያስፈልጋል በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ “የቤተ ክርስትያን አስተምህሮ”፣  “የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት”፣ “የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ”፣ “ምን እናድርግ” እና “ማኅበረ ቅዱሳን ማነው” የሚሉ አምስት ዐበይት ከፍሎች የነበሩት ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ከፖስተር ገለጻ በተጨማሪ በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች እና ማብራሪያዎች ቀርበውበታል፡፡  

ከዐውደ ርዕይው በተጨማሪ ጎን ለጎን በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል ።  እንዲሁም በትዕይንቱ ላይ ወይም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ጥያቄ ላላቸውም ማብራርያ ሰጥቷል። ለህጻናት እና ለአዳጊዎችም የሚሆን የትምህርት መርሐ ግብርም ተዘጋጅቶ ነበር።  በሦስቱ ቀናት ውስጥ በአጠቃለይ በግምት ወደ 200 አከባቢ የሚሆኑ ምእመናን በአማርኛ የተዘጋጀውን ትዕይንት እንዲሁም 17 ሰዎች ደግሞ የጀርመንኛው ትዕይንት ተመልክተውታል።

በመጨረሻም ዐውደ ርዕዩን የተመለከቱ ጎብኚዎች በሰጡት አስጠያየት በዐውደ ርዕይው ሰፊ ትምህርት እንዳገኙ፤ በሌሎች ከተሞችን እንዲካሄድ ያላቸውን ጉጉት እና ለወደፊቱ እነዚህ መሰለል መርሐ ግብሮች ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል። ይህ ዐውደ ርእይ አውሮፓ ላይ ሲካሄድ የመጀመሪያው ሲሆን በቅርቡ በጀርመን ሀገር በርሊን እና ሙኒክ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእንግሊዝ የ2ኛው ዙር ሐዊረ ህይወት ተካሄደ

በዩኬ ንዑስ ማዕከል

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማዕከል የዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማዕከል ያዘጋጀው የ2ኛው ዙር ሐዊረ ሕይወት መርሐግብር ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በታላቋ ብሪታንያ በነቲንግሃም ከተማ በቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ተካሄደ።

በጉባዔው ላይ ከተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች የተሰባሰቡ 50 ያህል ህፃናት እና ከ230 በላይ የሚሆኑ ካህናትና ምዕመናን ተሳትፈዋል። መርሐ ግብሩም በካህናት አባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ የአዉሮፓ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ለሐዊረ ህይወቱ ተሳታፊዎች ሁሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ! መልዕክት አስተላልፈዋል። አያይዘውም ስለማኅበሩ አመሠራረት ፤ ስያሜ፤ እንዲሁም ማኅበሩ ስለሚያደርገው አስተዋፅዖ በአጭሩ አብራርተዋል።

በመቀጠል የዩኬ ን/ማዕከል አባላት መዝሙር ከቀረበ በኋላ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ የሄልሲንኪ ደ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በቤተክርስቲያን ሥርዓትና አገልግሎት ዙሪያ ጥልቅ ትምህርት ተሰጥቷል።  የትምህርት አቀራረብ መሠረታዊ የሆነና የምእመናንን ግንዛቤ ግምት ውስጥ ያስገባ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ትምህርት ነበር። በትምህርቱ ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ፤ የአገልግሎት ሥርዓት፤ የአገልጋይና የተገልጋይ ደንብና ጥንታዊ የሆነ አደረጃጀት እንዳላትና፤ በትውፊትዋ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳት መፃህፍት ያልተደገፈ ወይም ያልተመሳከረ ሥርዓትም ሆነ ልማዳዊ የሆነ አገልግሎት እንደሌላት ግልፅና ጥልቅ የሆነ ማስገንዘቢያ ተሰጥቷል።

ከዚህ በማስቀጠልም ይህንን ሐዊረ ሕይወት ልዩ ካደረጉት መርሐ ግብሮች መካከል በህፃናት ክፍል ተዘጋጅቶ ሕፃናቱ በጋራ መዝሙር ለጉባኤው ማቅረብና የሕጻናት የጥያቄና መልስ ዉድድር ነው። በዉድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ሶስት ኅፃናት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ተሳትፎ ላደረጉ ህፃናት በሙሉ በዩኬ ን/ማዕከል የተዘጋጀ የተሳትፎ ሰርተፍኬት በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው በኩል እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ይህ የህፃናት መርሐ ግብር ከወላጆች መርሐ ግብር በተጓዳኝ መካሄዱ ህፃናት ለቤተክርስቲያን አስተምህሮና አገልግሎት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።

ማኅበረ ቅዱሳን በአገር ቤት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ስለሠራቸው ሥራዎች በተለይም ስብከተወንጌል ባልተስፋፋባቸው የጠረፍ አህጉረ ስብከቶች አካባቢ ስለሚካሄደው የስብከተ ወንጌል ማስፋፍያ መርሐግብር እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት በመግለጽ በቀጣይም ያሉባቸዉን ችግሮች ቀርፈው ራሳቸዉን እንዲችሉ ለማድረግ የተሠሩትን እና እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በምስል በማስደገፍ በንዑስ ማዕከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል አቅርቧል። የዕለቱ ሁለተኛ ትምህርት የሆነዉን “ነገረ ድኅነት” በመጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ሚካኤል ተሰጥቷል። በትምህርቱም ለመዳን መደርግ የሚገባውን ተግባርና የአተገባበር ሥርዓት በጥልቀት ተዳሷል።

በማስከተልም የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ተወካይ ሊቀ ኅሩያን ፍሥሐ ተፈሪ በግል የተሰማቸውን ደስታና የሀገረ ስብከቱን መልዕክት አስተላልፈዋል። ተወካዩ ሀገረስብከቱ ከማህበሩ ጋር እስካሁን ያለውን ቀና ትብብር አስገንዝበው ወደፊትም በመተባበር ሊሠሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንዲሁም በማህበረ ቅዱሳን የታላቋ ብሪታንያ ንዑስ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ለጉባዔዉ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ጉባኤው ላይ ትምህርት ላስተላለፉት አባቶች እንዲሁም በለንደን እና ከለንደን ዉጭ ለሚገኙ በገንዘብ እና በተለያየ መልክ ለረዱ ድርጅቶችና፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ምስጋና አቅርበዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በተሰጡት ትምህርቶች ብዙ እውቀት እንዳገኙበት እና በአጠቃላይ መርሐ ግብሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።  በመጨረሻም  መርሐግብሩ በኣባቶች ጸሎትና ምስጋና ተፈጽሟል።

በፊንላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐዊረ ሕይወት ተካሄደ።

በማኅበረ ቅዱሳን አውሮጳ ማዕከል በፊንላንድ ግንኙነት ጣቢያ አስተባባሪነት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የባህል ማዕከል እሑድ ግንቦት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም  ተካሄደ።  በመርሐ ግብሩ ላይ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ካህናትን እና ተጋባዥ መምህራንን ጨምሮ  የደብሩ ሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከሄልሲንኪ እና ከሌሎችም ከተሞች የመጡ ምእመናን ተሳትፈዋል።

Read more

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብራት በአገረ ኖርዌይ እና በአገረ ጣልያን

በኖርዌይ እና በጣልያን ን/ማዕከላት

ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም.

፪ኛው ዙር የሐዊረ ሕይወት (የሕይወት ጉዞ) መርሐ ግብር በአገረ ኖርዌይ በክርስቲያንሳንድ ከተማ ከሚያዝያ ፲፫ – ፲፬  ፳፻፲ ዓ.ም. (April 21-22, 2018) ተካሄደ፡፡

በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እና በአውሮፓ ማዕከል የኖርዌይ ንዑስ ማዕከል በጋራ በተዘጋጀው በዚሁ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ በአገረ ኖርዌየ ከሚገኙ የቤተከርስቲያን ልጆችና መምህራን በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ተጋባዥ መምህራን ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የመጡ ምዕመናን ወምዕምናት ተሳትፈዋል፡፡

Read more

አምስተኛው ሐዊረ ሕይወት በአገረ ጀርመን ተካሄደ

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም.

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለ፭ተኛ ጊዜ በጀርመን አገር ፍራንክፈርት ከተማ አቅራቢያ በክሮፍልባህ የግብፅ ቅዱስ እንጦስ ገዳም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ፭÷፲፮) በሚል መሪ ቃል ተካሄደ። በዚህውም ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሚሻኤል የቅዱስ እንጦንስ ገዳም የበላይ ጠባቂ፣ በጀርመን የኢ/ኦ/ቤ/ክ አስተዳዳሪዎች እና የሀገረ ስብከቱ ካህናትና ዲያቆናት፣ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አውሮፓ ሀገራት ተጋባዥ መምህራን እንዲሁም ዘማሪያን ተገኝተዋል። በተጨማሪም 400 የሚሆኑ ምዕመናን በጉዞው ላይ ተሳትፈዋል። Read more

በጀርመን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተመሰረተ።

በጀርመን ን/ማእከል 

ጥር  13 ቀን 2010 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በም/ም/ደ/አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ አስተባባሪነት በጀርመን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተመሰረተ።

በሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ ኃላፊ መልአከ ኃይል አባ ዘድንግል አስተባባሪነት ከሰ/ት/ቤቶች አመራሮች ጋር በተካሄደው የመነሻ ስብሰባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለመመስረት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውን አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ የተመረጠ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መተዳደሪያ ደንቡን ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ የተሠራውን መሠረት በማድረግና ህገ ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ አርቅቆ የማቅረብና የማጸደቅ፥ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ተወካዮች ሰብስቦ የማወያየት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አባላትን ስለ አንድነቱ ዓላማ እንዲረዱ የማድረግ ተግባራትን በኃላፊነት እንዲመራ ለኮሚቴውም ተስጥቶት ነበር። Read more

በአውሮፓ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ሥርዓተ ትምህርት ተመረቀ

በእንግሊዝ ንዑስ ማእከል

ኅዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም.

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና ካህናት በከፊል

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና ካህናት በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ሕፃናት እና ታዳጊዎችን ለማስተማር የሚያግዝ ሥርዓተ ትምህርት በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ በደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተመረቀ፡፡ Read more

በጀርመን ኑረንበርግ ዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ

በጀርመን ማእከል

ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም.

በደቡባዊቷ የጀርመን ከተማ ኑረንበርግ ጥቅምት 11 እና 12 2010 ዓ.ም “አብረን እንሥራ ለውጥ እናመጣለን” በሚል መሪ ቃል የዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ። ይህንን በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል  የጀርመን ንዑስ ማእከል ከኑረንበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ፍኖተ ቤተከርስቲያን ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች እና  ማኅበረ ቅዱሳን የሚሉ ሦስት ትዕይንቶች የተከፋፈለውን ዐውደ ርእይ  ከ150 በላይ ምእመናን ጎብኝተውታል። በተለይም የዐውደ ርእዩ ዋና ጉዳይ በሆነው የኢትዮጵያ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለእምነትና ለታሪክ መጠበቅ እና  ለዕውቀት፣ ትውፊትና ባሕል ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለው አስተዋኦ  እንዲሁም አሁን ያሉበት ወቅታዊ ችግሮቻቸው ላይ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። በተጨማሪም ችግሮቹን ለመፍታት በመላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ ያሉ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት አስተዋፅዖ እያደረጉባቸው ያሉትን  በርካታ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎች በቪዲዮ በታገዘ ማብራሪያ ለተመልካች ቀርበዋል። በሁለቱ ቀናት በነበረው የስብከተ ወንጌል መርሐግብርም በመርጌታ ይቻለዋል ጎሽሜ እና በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም አገልግሎትን የተመለከቱ ትምህርቶች ሰጥተዋል። Read more

በኮፐንሀገን የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ዐቢይ የአዲስ ዓመት መንፈሳዊ ጉባኤ አካሄደ።

በዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ

መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም.

ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 6 እና እሑድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. (September 16 and 17 /2017) በዴንማርክ ኮፐንሀገን የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ደብር የአዲሱን ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ዐቢይ የርእሰ አውደ ዓመት ጉባኤ አድርጓል። የጉባኤውም መሠረታዊ ዓላማ በሥራ፣ በትምህርት እና በተለያዩ የኑሮ ሁኔታዎች ከአገር ርቀው ያሉ “ዝርዋን ምዕመናንን” ሀገራቸውን ባህላቸውን ይልቁንም ሃይማኖታቸውን በቤተክርስቲያናቸው በኩል እንዲያውቁ ለማስቻል እና በቋሚነት ሊገለገሉ የሚችሉበትን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መፍትሄም ለመፈለግ ጭምር መሆኑ ተገልጿል። Read more

ሀገረ ስብከቱ ፬ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ።

በጀርመን ንዑስ ማእከል

መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ፬ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን  ዓርብ ነሐሴ 26 እና ቅዳሜ ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ/ም የሀገረ ስብከቱ መቀመጫ በሆነችው በጀርመኗ ሮሰልስሀይም ከተማ አካሄደ። በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ ሓላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ጉባኤው በዋናነት በሀገረ ስብከቱ፣ በአጥቢያዎች እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል የሥራ ክንውን፣ የሂሳብ ዘገባ እና የ2010 ዓ/ም የሥራ ዕቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።   Read more