በመጋቢ ሀዲስ ምስጢረ ስላሴ ማናዬ
መስከረም 16 ቀን 2009 ዓ.ም.
‹‹መስቀል ለእለ ነአምን መድኅን – መስቀል ለምናምን መድኃኒት ነው››። ስለነገረ መስቀሉ ከተናገሩ ሊቃውንት የኢትዮጵያው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ትልቅ ድርሻ አለው። በአምስቱም ድርሰቶቹ በሰፊው ስለ መስቀል ዘምሯል፣ ተናግሯል፣ አመስጥሯል። ከላይ ያነሳነውን ኃይለ ቃል የተናገረውም እርሱ ነው። ምክንያቱም የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ስለ ነገረ ድኅነነት ያጠነጥናሉ። እግዚአብሔር በነገረ ድኅነት ውስጥ ለሰው ልጆች ሁለት የተስፋ መንገዶች ሰጥቷል። አንደኛው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቅዱስ መስቀሉ ነው።
ሁለቱም የተሰጡት የሰው ልጅ ከገነት ሕገ እግዚአብሔርን ጥሶ፣ ትእዛዙን አፍርሶ፣ ዕፀ በለስን በልቶ፣ ከፈጣሪው ተጣልቶ በተሰደደ ጊዜ ነበር። ‹‹በሐሙስ እለት ወበመንፈቃ ለእለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ- በአምስት ቀን ተኩል /አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም/ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀሌና በሞቴ አድንኀለሁ›› ቀሌምንጦስ ከልጅ ልጅህ ያለውን ሊቃውንት ‹‹እንተ ይእቲ ማርያም-ይችውም ማርያም ናት›› ብለው ተርጉመውታል። ስለዚህ ሊቃውንቱ ይህ የተሰጠው የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ በእለተ ጽንስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ተጀመረ፤ በእለተ ዓርብ በቅዱስ መስቀል ተፈጸመ ብለው አስተማሩ። ‹‹ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል – የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ በቀራንዮ መድኃኒት መስቀል ተተከለ›› ብለው ገለጡት። በድርሰታቸው መድኃኒትነቱን ለምናምን መሆኑን ሁላችንም እርግጠኛ መሆን ይገባናል። ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ ወናሁ ተፈጸመ ኩሉ- የሰጠኸኝን ሥራ ጨረስኩ እነሆ ሁሉ ተፈጸመ ።›› (ዮሐ 17፥4) ያለው ለዚህ ነበር። ከዚህ የተነሳ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ መስቀሉን ታከብረዋለች፤ ስለ ክብሩ ትናገራለች።
Read more