ሕይወት በባዕድ ምድር (፪ጴጥ. ፪፥፰)
እንግዲህ እንዲህ አይንቱ አስከፊ ኃጢአት እየተሠራና እየተነገረ ባለበት ጽንፈ ዓለም እየኖርን ነዉ። ለመሆኑ እንደ ጻድቁ ሎጥ ነፍሳችን ተጨንቃ ይሆን ወይስ እንዲያዉ “ሳይበዛ” ማየቱንም መስማቱንም እየወደድነው ይሆን? ግዙፍ መርከብን ለማስጠም ትንሽ ትበቃለች። ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረም “ነገር ሁሉ ያደክማል፤ ሰዉም ይናገረው ዘንድ አይችልም፣ ዓይን በማየት አይጠግብም፣ ጆሮም በመስማት አይሞላም”። መክ ፩፥፰.። እያንዳንዷ ዕለት የጽድቅን ሥራ እንሠራባት ዘንድ እንዲሁ ከፈጣሪያችን የተቸረችን በረከት መሆኗን አዉቅን በመስማት፣ በማየት፣ በመናገር፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት እና በግብር ከመፈጸም ከሚገጥመን ነገር ራሳችንን እየጠበቅን እና ለጽድቅ ተጋድሎ ሰዉነታችንን እያስለመድን ነዉን? ወይስ ምን አለበት፣ የጽድቁ ሥራ ይደርሳል፣ ለብቻ መኖር አይቻል? ማሕበራዊ ኑሮ ስለሆነ ምን እናድርግ፣ አለቃየ እኮ ነዉ እና የመሳስሉትን እያልን ነዉ? ልናስተዉል የሚገባን ነገር ቢኖር የትም ሆነ የት ፈተና የማይቀር መሆኑን ነዉ። ፈተናም በተለያየ ደረጃና ሁናቴ ይመጣል እንጂ አንድ ዓይነት አይደለም።
በመጀመሪያ ከራሳችን የሚመጣ ፈተና አለ። ንዝህላልና ግድየለሽ ሆነን ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄ ምን አለበት ብለን ስንተዉ ፈተና ይገጥመናል። “ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን” መኃል. ፪፡፲፭። የተባለዉ ለዚህ ነዉ ከሥጋ ፈቃድ ፈተና ይመጣል፤ መጾማችን ቅሉ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስግዛት ነዉ እንጂ ሌላ አይደለም። በነፍስና በሥጋ ፈቃዳት መካከል ሁል ጊዜ መጠላላት አለ፤ አንዱ ሌላዉን ማርኮ የራሱ ግብር ተባባሪ ለማድረግ ሁልጊዜ ይቀዋወማሉ(ገላ. ፭፣፲፯-ፍጻ)። የሥጋችንን ፈቃድ ስንፈጽም ፈቃዳተ ነፍስን መፈጸም ይሳነናል። ለዚህም ነዉ የተመሰገነ ሐዋርያ ጳዉሎስ “…የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን…” ኤፌ. ፪፣ ፫ በማለት ከማይገባ ምኞት እንጠበቅ ዘንድ የመከረን።
ሁለተኛ ከሰይጣን የሚመጣብን ፈተና አለ። እርሱ ሁል ጊዜ ተቃዋሚያችን ነው፤ የጽድቅ ጠላቷ የሐሰት አባቷ ነዉ። ስለሆነም ሓጢአት ለማሠራት ይገፋፋናል። በአገልግሎት የተጋን እንደሆነም በትዕቢት ያጠምደናል፣ በጽድቅ ሥራም እንኳ ሳይቀር አለሁበት ይላል። እርሱ ቅሉ ከማስጎምጀት፣ ከማቻኮል፣ አድርጉት አድርጉት የሚል ሃሳብ ከማቅረብ አልፎ አያስገድድም፤ ሲፈትንም ቅሉ ፈቃድ ሳይቀበል አንዳች ማድረግ አይችልም። ስለዚህ የሚጥለን በክፉ መንገዱ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆነን ሲያገኘን ነዉ። እርሱ መቸም መች አይተኛም። ቅ/ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚዉጠዉን ፈልጎ እንደሚያግሣ አንበሳ ይዞራልና፤” ፩ጴጥ. ፭: ፰ና፱። በምንድን ነዉ የምንቃወመዉ? በትህትና፣ በፍቅር ጸንቶ በመመላለስ፤ ጻዲቅ ሎጥን መስሎ በመገኘት ነዋ! የኃጢአት ነቋ ሰይጣን ነዉና ኃጢአትን እንደሎጥ መቃወምና ነፍስን ለጽድቅ ማስጨነቅ ሰይጣንን መቃወም ነዉና።
በመጨረሻም ከምንኖርበት ሀገር ባሕል፣ ልምድ፣ ወግ፣ ከጓደኛ (የትምህርት ቤት፣ የሥራ…) ሊመጣ ይችላል። ቅ/ጳዉሎስ “አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” ፩ቆሮ.፲፭፣፴፫ እንዳለ በማይመች አኳኋን መኖር ከጀመርን መውደቅ ይከተላል። የእናታችን ሔዋን እና የእባብ አይነት ግንኙነት (ዘፍ.፫)፣ የዲናና የሴኬም ግንኙነት (ዘፍ.፴፬)፣ የሶምሶምና የደሊላ አይነት ግንኙነት (መ.መሳ. ፲፬) መጨረሻዉ ዉርደት ይሆናል። ጻዲቅ ሎጥን ለመጨነቅ ያደረሰው የሰዶም ሰዎች የሚሠሩትን ክፉ ግብር ማየቱ ነበር። እኛንም በዋናነት ሊያስጨንቀን የሚገባዉ ይህ ነው። ማየት ወደ ምኞት፣ ምኞትም ኃጢአትን ጸንሶ ወደ መወለድ (በግብር ወደ መፈጸም) ሳያደርስ አይቀርም። የማይገባ እይታ ለከፋ ነገር ማድረሱ አይቀርምና አየሁ እንጂ ምን አደረግሁ አይባልም። አምኖን በወንድሙ ለመገደል ያበቃዉ (፪ሳሙ. ፲፫) በማይገባ እይታ እና ምኞት ተነድቶ እህቱን ትዕማርን ከክብር በማሳነሱ ነዉ። ሔዋን ከ ዕፀ በለስ የበላችዉ በዓይኗ ተመልክታ ከጎመጀች በኋላ ነዉ። አምኖንም ሔዋንም ባልንጀሮቻቸው ያዩትን እንዲፈጽሙ የሚያተጓቸዉ እንጂ ኧረ አይግባም የሚሏቸዉ አልነበሩም፤ ሔዋን አዳምን፣ አሞንም ዳዊትን ቢያማክሩ ኖሮ ያ ሁሉ ዉድቀትና ሞት ባልመጣባቸዉ ነበር።
ምን አልባት በምንኖርበት አካባቢ ባሉ ስዎች ዘንድ ጸያፍ ነገር ማየት እንደ ድንቅ ላይታይ ይችላል፣ ምክንያቱም እነርሱም በዚያ ሕይወት ዉስጥ ነዋሪዎች ስለሆኑ ክፋቱ አይታያቸዉምና። ጻድቅ ሎጥ በእነርሱ ክፉ ሥራ ነፍሱን ሲያስጨንቅ የሰዶም ሰዎች፤ ኖኅም ከጥፋት ዉሃ ለማምለጥ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መርከብ ሲያዘጋጅ ሰብአ ትካት እንደ ሞኝ ይቆጥሯቸው ይስቁባቸዉም እንደነበር ነዉ። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰዉነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰዉነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። ” ማቴ.፮፣፳፪ ማለቱ ለዚህ ነዉ።