ሕይወት በባዕድ ምድር (፪ጴጥ. ፪፥፰)
እንግዲህ ፈተና ባንድም በሌላም መንገድ መምጣቱ የማይቀር ከሆነ ራሳችንን ጠብቀን ለመኖር እና እናንተ ያባቴ ቡሩካን ኑ (ማቴ. ፳፭፣፴፬) ብሎ ከሚያከብራቸው ቅዱሳን ጋር ለመደመር ምን እናድርግ? ከረጅሙ ባጭሩ ወስደን ከብዙ በከፊሉ ጨልፈን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክር፦
- በሕገ እግዚአብሔር መኖር፦ የሰው ልጅ ከእግዚአአብሔር የተቀበለውን ሁሉ ዋጋ መክፈል የሚችለው ትዕዛዛቱን በመፈጸምና ምስጋናን በማቅረብ ብቻ ነው። አምልኮተ እግዚአብሔርን በትክክል ለመፈጸም ሕገ እግዚአብሔርን መማር ይኖርብናል። በፍፁም ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ነግሮናልና። የእግዚአብሔር ለመሆናችን መታወቂያዉ በትእዛዙ መኖር ነው፤ ሕግጋቱንና ትእዛዛቱን በመጠበቃችን የእርሱ መሆናችን ይታወቃል። በየትኛውም ሀገር ብንሰደድ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የማይለወጠው እግዚአብሔር አብሮን እንዳለ መርሳት የለብንም። በሀገራችን ስንሆን ሕጉን የምንጠብቅ ከሀገራችን ውጭ በማይመች ሁኔታ ስንሆን ከሕገ እግዚአብሔር ውጭ እንድንሆን አልተፈቀደልንም። የክርስቲያን መልኩ አንድ ነው፣ በየተግኛዉም አጽናፈ ዓለም ቢኖር አካሄዱ ይገልጠዋል። ሁልጊዜም ሕይወቱ በቃለ እግዚአብሔር የተቃኘ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ ባነጋገሩ፣ ባኗኗሩ ይታወቃል። “ቃሉን ስበክ በጊዜዉም አለጊዜዉም ጽና”፪ጢሞ.፬፣፪ ፤ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር” ፪ጢሞ. ፫፣፲፬፤ “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይግኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ዉስጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልኛል።” ዕንባ. ፫፣፲፯ና ፲፰። ይልቁንም ዕለት ዕለት ሕጉንና ትዕዛዙን በመጠበቅ መኖር ይገባናል። አባቶቻችን አካሄዳቸውን ሁሉ በሕገ እግዚአብሔር መሰረት ማድረጋቸውን ነብዩ ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው”። መዝ ፻፲፰፣፻፭ በማለት ያስተምረናል።
- ሥጋዊ ምኞትን አለመከተል/አለማስቀደም እና ምሳሌ መሆን፦ ከፍ ብሎ ለመግልጽ እንደተሞከረዉ ፈቃደ ሥጋን መከተል ነፍስ ፈቃዳቷን እንዳትፈጽም ያደርጋታል። በመንፈስ ጀምረዉ በሥጋ የሚጨርሱ ሰዎች ትንሽ የሚባሉ አይደሉም፤ እኔ አገልጋይ ነበርኩ፣ አስቀዳሽ ነበርኩ፣ ጿሚ፣ ለሕገ እግዚአብሔር ቀናዒ ነበርኩ የሚሉ አሁን ግን በዓለም አምሮት ተዉጠዉ ያሉ ብዙ ናቸው። የአስቆሮቱ ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር፤ ዴማስ የቅዱስ ጳዉሎስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም ግን ይሁዳ በሠላሳ ብር ጌታዉን አሳልፎ በመስጠት፣ ዴማስም በተሰሎንቄ ከተማ ተማርኮ ከቅዱስ ወንጌል አግልግሎት ተለይተው ተጎዱ። የሁለቱም ከተቀደሰዉ ሕይወት መራቅ ምክንያቱ በፍቅረ ዓለም መሳብና ሥጋዊ ምኞትን ማስቀደማቸዉ ነዉ። ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን በመግታት በጀመርነዉ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ይገባናል። በሰብአ ትካት መካከል ኖኅ ና ቤተ ሰዎቹ፣ በሰዶም መካከልም ሎጥና ቤተ ሰዎቹ ነበሩ፣ ግን ከጽድቅ መንገድ አልወጡም። ክርስትናን በዓለም ያስፋፉት ክብር ምስጋና ይግባዉና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ የተማሩ 120 ቤተ ሰዎች ናቸዉ። በዙሪያቸው የነበረው ሕዝብ ሁሉ እነርሱንና አምላካቸው ኢየሱስ ክርስቶስን የሚጠላ የሚገድላቸውም ነበረ። እነርሱ ግን ከሥጋዊ ምኞት በመራቅ ሁልጊዜ ምሳሌ በመሆን ክርስትናን በዓለም ሁሉ ሰበኩ፤ ጠላቶቻቸውንም ሳይቀር የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኙ ዘንድ አጠመቋቸው። ስለዚህም ከአባቶቻችን የምንማረው ምንጊዜም በተማርነውና በተረዳነው ሕግና ሥርዓት መሠረት መኖር እንደሚገባን ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንዲህ ሲል ጽፎልናል፤ “የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ከሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች፣ ደካሞችም እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ።”፩ጴጥ ፪፥፲፩ “ክፉ ከምትሰሩ ይልቅ መልካም ሥራ እየሰራችሁ፣ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ እየተከተላችሁ መከራ ብትቀበሉ ያሻላልና።” ብሏል። ፩ጴጥ ፫፥፲፯
- ትዕግሥት፦ ከሥጋዊ ምኞት ለመራቅ በምናደርገው ጥረት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። እንዲያውም አንዳንዴ ሕግህን ስላከበርኩ ይህን ያህል መከራ ሊጸናብኝ አይገባም ብለው የሚመጻደቁ ሰዎችም አይጠፉም። ከሓጢአት ጋር ተላምደዉ፣ ካለማመን እና ከክሕደት ጋር ተዛምደዉ፣ ከክፉ ልማድና ከክፋት መንገድ ጋር ተጣብቀዉ በአመጽ እየኖሩ የጎደለባቸዉ ነገር የለም፣ እኔ ግን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ለማግኘት ከሀገር ወጥቼ በባዕድ ሀገር መኖርና መንገላታት አገኘኝ የሚል ሃሳብ ሊመጣብን ይችላል። እንዲሁም ለሥጋዊ ሕይወት የሚያስፈልገዉን ሁሉ ለማግኘት አግባብ ባልሆነ መንገድ መሄድና ብኩን ሕይወት መምራትን እንደ መልካም ቆጥረን እንድንገፋበት የሚያበረታቱን ነገሮች በዙሪያችን ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እንዲህ አይነት አሳብ ሲመጣብን መጠራት እኮ ለማመን ብቻ አይደለም ልንል ይገባል። የቅዱስ እግዚአብሔር የሆኑት ቀደምት አበዉ እና እማት እጅግ የከፋ መከራ ተቀብለዋል፣ ስለ ርትእት እምነት ደማቸዉን አፍሰዋል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ጀርባቸውን ለግርፋት ሰጥተዋል። ይህ አሁን የምንኖርበት ዓለም ወደ ቀደመ አለመኖሩ የሚመለስበት ጊዜ ይመጣል። ስለዚህ ያለንበትን ሁናቴ እና የሚደርስብንን መከራ በኋላ ከሚጠብቀን ሕይወት አንጻር ስናየዉ እጅግ ያነሰ መሆኑን መገንዘብ ይግባናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ማንም ያልተቀበለዉን ስቃይ ተቀብሏል። ወርቅንና ብርን፣ ሹመትንና መንግሥትን፣ የሰብአ ነገሥት ሽልማትንና የዚህ ዓለም ክብር በነፋስ ተገፍቶ እንደሚጠፋ ደመና ቆጠረዉ፡፤ ለሰባት ዓመት ጽኑዕ ተጋድሎዉም ሰባት አክሊላትን ተቀበለ። መከራዉ ከተቀበለዉ ክብር ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር አይገባም። ትዕግሥት ሊኖረን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ትዕግሥትን የመልካምነት ዘዉድ ይላታል። ቅዱስ ያዕቆብም “ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። … ልባችሁንም አጽኑ ጌታ መምጫዉ ቀርቦአልና።” ሲል ይመክረናል። ያዕ.፭፣፯-፲፩። አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እስከ መጨረሻዉ የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል ማቴ. ፳፬፣፲፫ ብሎ በማይታበል ቃሉ ነግሮናል። የሚገጥመንን ፈተና በትዕሥት ስንወጣ ያኔ ክብር ይጠብቀናል። ጻድቅ ኢዮብ ፈተናዉን በመታገሡ ለትዕግሥት አብነት ሆኗል። ስሙም ተለዉጦ ኢዮባብ ተብሏል። ቅዱስ ጳዉሎስ በዕብራዉያን መልዕክቱ ምዕራፍ 11 የዘረዘራቸው ቅዱሳን ሁሉም የሚገጥማቸዉን ፈተና በትዕግሥት ተቀብለዉ ጽኑዕ ተጋድሎን ተጋድለው ፈጽመው በማሸነፋቸው ነዉ። መከራ ያለብን መሆኑንም ራሱ አምላካችን “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ. ፲፮፣፴፫ ብሎ ነግሮናል።
- ማንነትን ማስታወስና የተጠሩበትን ማወቅ፦ በስደት ስንኖር የራሳችን እምነት፣ አምልኮ፣ ባሕልና ትውፊት እንደሌለን ሁሉ የባይታዋርነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች እጅግ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜም የማንነታችን መገለጫ የሆኑትን ነገሮች ሰዎች ሲያፌዙባቸውና ሲሳለቁባቸው ተስፋ የሚያስቆርጥ የሚመስል ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል። በዚህ ጊዜ ግን ማንነታችንን ማስታወስ ይገባናል። የትም ብንሄድ የአምልኮት መልካችን ሊቀየር አይገባውም። ይህንንም ነብዩ ኤርምያስ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” በማለት የአምልኮት መልካችን መቼምና የትም መቀየር የማይችል መሆኑን ያስገነዝበናል። ኤር. ፲፫፣፳፫:: እስራኤላውያንን ማርከው የወሰዷቸው አሕዛብ የጽዮንን ዝማሬ እስኪ ዘምሩልን ብለው በጠየቋቸው ጊዜ በገናዎቻቸውን ዛፍ ላይ በመስቀል ያ የጽዮን ዝማሬ በኢየሩሳሌም ምን ዓይነት ክብር ያለው እንደ ነበር በማስታወስ አንዘምርም አሉ። ልበ አምላክ ዳዊትም ማንነቱን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር “ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ” በማለት ቃልኪዳኑን ሲያከብር እንማራለን። መዝ. ፻፴፮፣፭:: ፈሪሃ እግዚአብሔር አጥር፣ ሃልዎተ ፈጣሪ ከለላ፣ ሕገ እግዚአብሔር ብርሃን ሊሆነን ይገባል። ዮሴፍን ማሰብ፣ ሠለስቱ ደቂቅንም ማስታወስ ይገባል። ዮሴፍ በባርነት፣ ሠለስቱ ደቂቅም በምርኮ እያሉ በፊታቸው እግዚአብሔርን አድርገው ከባእድ ሰዎች ጋር መተባበር፣ አማልክቶቻቸውንም መከተልን እምቢ አሉ። ሃይማኖት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፤ ለመኖር ሲባል የሚል ቋንቋ በሃይማኖት ቦታ የለዉም። ተዋሕዶተ ቃልን (ሥጋዌዉን) የማያምን ርጉም ነው፣ የአርዮስ ዉላጅ ስለሆነ ከእርሱ ፈጥኖ መለየት ይገባል። በግ በግን እንጂ ፍየልን ወይም ተኩላን መሆን አይቻላትም፣ ጠባዩአ እና ግብሯ ከነሳቸዉ የተለየ ስለሆነ። ከዚሁም ጋር ለምን ከሀገር እንደወጣንም ማሰብ ተገቢ ነዉ። ከሀገር መዉጣታችንን ከዱባ ተክል ጋር ማነጻጸር እንችላለን። የዱባ ፍሬ ከበቀለች በኋላ እየተሳበች ትሄዳለች። ዱባ ፍሬ ለማፍራት የምትሄድ ከሆነ የእኛም ከሀገር መዉጣታችን እንዲሁ ፍሬ ለማፍራት ነዉ። ዓላማ ሳይኖረዉ የወጣ መኖሩ ያጠራጥራል። እግዚአብሔር ከሀገር እንድንወጣ የረዳን መሆኑን በአንድም በሌላም መንገድ ተናግረናል። ስለዚህ ይሕን ቃላችንን እናስታዉስና ለምን እንድወጣ ፈቀደልኝ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ስንወጣ የሎጥን ሚስት አስቧት የሚል ስንቅ አስቋጥሮን እንጂ እንዲሁ አይደለም። ወደ ኢትዮጵያ አትመልከቱ አይደለም፣ ወደ ቀደመ የሓጢአት ኑሮ አትመለሱ የምትሄዱበት ጽንፈ ዓለም ሓጢአት የነገሠበት ስለሆነ መጠራታችሁን አስታዉሱ የሚል ነዉ እንጂ። የሎጥ ሚስት ማንነቷን ረስታ፣ የመልአኩን ቃል ዘንግታ “ወይ አገሬ ሰዶም እግዚአብሔር ባላወቀ ፈርዶ አደረገሽ ባዶ” አለች፤ መጨረሻዋ ግን የጨው ሐዉልት መሆን ነው። ሰዉ ማንነቱን ከረሳ የጠላቶቹ (ሓጢአት፣ ሰይጣን) መፈንጫ እና መራገጫ መሆኑ አይቀርም። በዓላማችን ስንጸና ግን ያሰብነዉን ማሳካት እና ረጅም ጉዞ መጓዝ እንችላለን።
- በጸሎትና በአገልግሎት መትጋት፣ እርስ በራስም መተሳሰብ፦ ሰዉ ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር የሚገናኘው በጸሎት ነዉ። ጸሎት ሰዉን ከፈጣሪዉ ጋር የሚያገናኘው ረቂቅ ዓምደ ብርሃን በመሆኑ የክርስቲያኖች ሕይወት ከጸሎት ጋር ተለይቶ አይታሰብም። ከጠላት ፍላጻ ለመጠበቅ ጸሎት ፍቱን ነዉ። በአገልግሎት ያለ ሰዉ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ መንጋዉ መጨነቅ እና መጸለይ ይኖርበታል። ፈተናን በድል ለመወጣት አዘዉትረን መጸለይ ይገባናል። ቅዱስ ጳዉሎስ “የሰይጣንን ተንኮል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ። ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ግዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነዉ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ። እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ … በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፣” ኤፌ.፮፣፲፩- ፲፰ ሲል እንደመክረን።