ደብረ ዘይት
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
መጋቢት 24 ቀን 2008 ዓ.ም.
ደብረዘይት የዓቢይ ጾም እኩሌታ ነው ። በእለቱም ስለ ዳግም ምጽአት ይነገራል። ስለ ምጽአት ነቢዩ ዘካርያስ «በዚያን ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ…አምላኬ እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይመጣል…አንድ ቀን ይሆናል…. በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይወርዳል።» (ዘካ ፲፬ ፥ ፬–፰) በማለት አስቅድሞ ትንቢት ተናግሯል። አምላክ በዚህ ትንቢት እና በሌሎች ነቢያት ያናገረውን ፣ እርሱ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ላይ የዳግም ምጽአት ምልክቶችን እና አመጣጡን ከፍርዱ ሂደት ጋር በግልጽ አስተምሯል። ይህንንም ሁሉ የተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት ስትዘከረው ኖራ በምጽአት ቀን ተስፋዋን መንግሥተ ሰማያትን ትረከባለች:: በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደተለመደው በዚህ የደብረ ዘይት ሳምንት ጽሑፍ ስለ ደብረ ዘይት ፣ ስለምጽአት ምልክቶች ፣ ስለምጽአት እና ተስፋው እንዘከራለን ።