ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም
“ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ እና አንድነት ሁላችሁም ትናገራላችሁ፤ እኔም ብመኘውም ብቻዬን ግን አላመጣውም፣ እናንተም እርዱኝ” ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በአውሮፓ አኅጉር በአዲስ መልክ ከተዋቀሩት አራት ሀገረ ስብከቶች አንዱ የሆነው የጣልያን እና አካባቢው (ጣልያን፣ ቤልጅዬም፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ እና ቱርክ) ሀገረ ስብከት የመመሥረቻ ጉባኤውን በጣልያን ዋና ከተማ ሮም አካሄደ። ጉባኤው ጥር 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሰብሳቢነት ተካሂዷል። በጉባዔው ላይ በሀገረ ስብከቱ ስር ከሚገኙ አሥራ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት ከጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅየም፣ ግሪክ እና ከቱርክ የተሰባሰቡ አስተዳዳሪዎች እና የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ተወካዮች ታድመዋል።
ተሳታፊ ካህናት አባቶች እና ተወካዮች የእርስ በርእስ ትውውቅ እና የመጡበትን አጥቢያዎች አጭር የሥራ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሀገረ ስብከቱ በሚገኙት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ችግሮች እና አለመግባባቶችን ያስተናገዱ መሆናቸው ተጠቁሟል። ከእነኚህም በእግዚአብሔር እርዳታ መፍትሔ የተሰጣቸው አጥቢያዎች ሲኖሩ በአሁኑ ወቅት አለመግባባቱ የተባባሰባቸው እንዳሉ ከቀረቡት ሪፖርቶች ለመረዳት ተችሏል። እነኚህን ችግሮች ለመፍታት ሀገረ ስብከቱ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።
የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በየአጥቢያው ያሉትን ችግሮች እንዲሁም ሥርዓትን እና ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልጠበቀ አሠራር ከሀገረ ስብከታቸው እንዲጠፋ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። “ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ እና አንድነት ሁላችሁም ትናገራላችሁ፣ እኔም ብመኘውም ብቻዬን አላመጣውም፣ አናንተም እርዱኝ” በማለት ሰላምን ለማስፈን እንዲቻል የጉባኤተኛውን ቀና ትብብር የጠየቁት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ “ለዓለም ሰላምን የምትሰብክ ቤተክርስቲያ ውስጥ ሆነን፣ የእኛን ችግር ራሳችን መፍታት አቅቶን፣ ገመናችንን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት እና ዳኛ በመውሰድ ከፍተኛ የገንዘብ እና የጉልበት ኪሳራ ላይ ወድቀናል፣ ይህ ገንዘብ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ማበልጸጊያ ይውል ነበር።” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ የተዋቀረው የሀገረ ስብከቱን የተለያዩ ክፍሎች የሚያስተባብሩ እና አገልግሎቱን የሚመሩ ሰባት አባላት ያሉት የአስተዳደር ጉባኤ የተዋቀረ ሲሆን ጉባኤው፣ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍስሐ ድንበሩን (ከፈረንሳይ) የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በማድረግ ሰይሟል። በሌላ በኩል በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በጳጳሱ አቅራቢነት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመድቡ መሆኑ ተገልጿል። ይህ አዲስ የአስተዳደር ጉባኤ በተወከለበት አካባቢ ያለውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ለማሳለጥ በተለይም ከዚህ በፊት ከነበሩት ሙከራዎች በተሻለ መልኩ ዘመኑን የዋጀ፣ ግልጽነት የሰፈነበት፣ እና በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲያመጣ ሓላፊነት ተጥሎበታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በጣልያን ዋና ከተማ በሮም እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን አገልግሎቱን በአስተማማኘነት ለማስቀጠል እንዲቻልም ሁሉም አጥቢያዎች እንደየደረጃቸው የገቢ ፈሰስ እንዲያደረጉ ውሳኔ ተላልፏል።
ሀገረ ስብከቱ በዚህ ጉባኤ በጸደቀለት መመሪያ መሠረት፣ ከጥገኝነት ነጻ የሆነ እና የትኛውም ሊቀ ጳጳስ በተዘዋወረ ጊዜ በሻንጣው ይዞት የሚዞር ዕቃ እንዳይሆን፣ ነገር ግን ራሱን የቻለ የገንዘብ እና የቁሳቁስ አቅም፣ የተጠናከረ ቢሮ እና አስተዳደር እንዲኖረው ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። ለዚህም እንዲረዳ ከአብያተ ክርስቲያናት ከሚሰበስበው ገቢ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ሀገረ ስብከቱን እንዲያጠናክር ለአስተዳደር ጉባኤው ምክር ተችሮታል። በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የካህናት እና አገልጋዮች ምደባ እንዲሁም አጠቃላይ አሠራር ወጥነት ባለው መልኩ እና ከጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመናበብ እንዲያከናውንም ጥሪ ቀርቧል።
ለሁለት ቀናት የተደረገው የምስረታ ጉባኤው በሀገረ ስብከቱ ሊሠሩ ይገባቸዋል ያላቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች በመጠቆም አዲስ ለተቋቋመው የአስተዳደር ጉባኤ የቤት ሥራ ሰጥቷል። ከነዚህም መካከል በሀገረ ስብከቱ ሰላምን እና አንድነትን ማጠናከር፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነትን መፍጠር፣ በጥናት ላይ የተደገፈ አሠራር መዘርጋት፣ በአውሮፓ መልካም አጋጣሚዎችን ማጥናት፣ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ በጥገኝነት ጠያቂዎች ማቆያ ካምፕ አካባቢ ትምህርት መስጠት፣ የአገልጋዮች ስልጠና ማዕከል መከፈት፣ አጥቢያዎች የራሳቸው የሆነ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ማስገኘት፣ እና ሀገረ ስብከቱን ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል።
በጉባኤው መጨረሻ ላይ ታላቅ ሥራን እግዚአብሔር ሠርቷል። ይህም፣ በሮም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና በደብረ ከነዓን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች መካከል ተፈጥሮ ለዓመታት የቆየው አለመግባባት “ድንጋይ ባገኝ፣ ድንጋይ ተሸክሜ ይቅር ይባባሉ ዘንድ በለመንኳቸው” ሲሉ በተደመጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ሕርያቆስ ጸሎት እና በተሳታፊዎች አቀራራቢነት በሁለቱ አጥቢያዎች ካህናት እና ተወካዮቻቻው አማካኝነት እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ ሆኗል። ይህ እርቅ የምሥረታ ጉባኤው ታላቅ ስኬት ሲሆን በሁለቱ አጥቢያዎች የተጀመረው የእርቅ እና የሰላም ጉዞ በአጠቃላይ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት አገልግሎት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ተገልጿል። በሌሎች አጥቢያዎች የሚታዪ አለመግባባቶችም በዚህ መልኩ መፈታት እንደሚኖርባቸው መንፈሳዊ ጥሪ ተላልፏል።