የሆላንድ ንዑስ ማዕከል ዓውደ ርዕይ አካሄደ

ሚያዚያ 07 ቀን 2011 ዓ.ም

በሆላንድ ንዑስ ማዕከል

በሆላንድ አምስፎርት ከተማ “ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አስተምሮዋን እንጠንቅቅ፣ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል ርዕስ ዓውደ ርዕይ ተካሄደ፡፡በሐመረ ኖህ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅዳሜ ፳፩ / ፪ሺ፲፩ ዓም የተደረገው ይህ ዐውደ ርእይ ቀድሞ ከተካሄደው አውደ ርእይ ከረጅም ጊዜ በኋላ ቆይቶ የተካሄደ መሆኑን የቆዩ የንዑስ ማዕከሉ አባላት ይናገራሉ። በአራት ክፍል የተዘጋጀው ይህ ዓውደ ርዕይ በምስል ወድምጽ በተደገፈ ገለጻ ቀርቧል።ቤተክርስቲያን ማናት እና አስተምሮዋ በክፍል አንድ ሲቀርብ፤ ሐዋርያዊው ተልእኮ እንዲሁም በተልእኮው  የገጠሙ ተግዳሮቶችና የተደረጉ ተጋድሎዎች በክፍል ሁለትና ሶስት በቅደም ተከተል ቀርበው፤ በመጨረሻም በክፍል አራት የምዕመናን ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚችልም ያመላከተም ነበር።

Image may contain: one or more people, people standing and wedding Image may contain: 1 person, indoor

በአውደ ርእዩ የተሳተፉ ምዕመናንም እንዲህ አይነት ዝግጅት በየዓመቱ ቢደረግ፤ እኛ ያየነውን በሌሎች አጥቢያዎች ያሉ ምዕመናንም እንዲያዩት ቢደረግ በሕብረት ወደ መስራት ያመጣን ይሆናል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ትዕይንት ክፍል ሶስትና አራት የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህችን ቤተክርስቲያን እንዴት እንዳቆዩልንና ዛሬስ ምን እያደረግን እንደሆነ የሚያነጻጽር በመሆኑ፤  ወደ ራሳችን ተመልሰን እራሳችንን እንድመለከት አድርጎናል ብለዋል።

ትዕይንቱን መርቀው የከፈቱት የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ኃይለማርያምም ማኅበሩ ለቤተክርስቲያን ፈርጥ መሆኑን እናውቃለን ግን በሆላንድ ያለው እንቅስቃሴ እኔ በማውቀው ውስን ነው፡አሁን ያየነው መርሐ ግብር በራሱ ትልቅ ለውጥ መሆኑን መመልከት ችያለሁ። ከዚህ ቦኃላም ማኅበሩ ከቤተክርስቲያን የተረከበውን የልጅነት አደራ እንደሚወጣ እገምታለው  ብለዋል፡፡ አያይዘውም ተጀምሮ እስኪያልቅ ምዕመኑ ሳይሰለች እንዲቆይ ያደረገበት የጊዜ አጠቃቀምና አቀራረብ ዘዴ የማኅበሩን ማንነት ያሳየበት ነው ብለው ከ አውደ ርዕዩ ቦኃላ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤው አባላትም በመርሐግብሩ ተደስተው ሌሎች መርሐ ግብራትንም ማኅበሩ በአጥብያቸው እንደሚያደርግ እና ለዚህም የሰበካ ጉባዔው እና ምእመናንም በማንኛዉም ነገር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

Image may contain: one or more people and indoor

የሆላንድ ንዑስ ማዕከል በአውሮጳ ማዕከል ስር ካሉት ንዑስ ማዕከላት አንዱ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ወስብሃት ለእግዚአብሔር         

የጀርመን ንዑስ ማዕከል ሦስተኛውን ዐውደ ርዕይ በሙኒክ ከተማ አካሄደ።

ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

“ቤተ ክርስቲያናችንን እንወቅ አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ” በሚል መሪ ቃል፥ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማኅበሩ ንዑሳን ማዕከላት አስተባባሪነት እየቀረበ የሚገኝ ሲኾን፥ ዋና ዓላማውም ቤተክርስቲያንን ለምዕመናን በማስተዋወቅ አስተምህሮዋንና ኹሉን ዓቀፍ ህልውናዋን ለማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ማንነት፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቷንና በዘመናት የገጠማትን ተጋድሎ፥ እንዲኹም በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ያሉባትን ውስንነቶች ጭምር የሚያስረዳው ዐውደ ርዕይ በጀርመን ቫርያ ግዛት ዋና ማዕከል በኾነችው በሙኒክ ከተማ በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መጋቢት ፳፩ እና ፳፪፥፪፻፲፩ ዓ/ም በጥሩ ሁኔታ ቀርቧል።

ዐውደ ርዕዩ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የምሥራቅ ወለጋ ቄለም ወለጋና ሆሮ ጉድሩ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ቃለ ምዕዳን ተባርኮ የተከፈተ ሲኾን፥ በአካባቢው የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮችም በመክፈቻው ላይ ተገኝተዋል። ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከመክፈቻ ፕሮግራሙ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት በሰማያት ያለውን እግዚአብሔርን የሚገልጥ፥ በሰዎች ፊት የሚበራ መልካም ሥራ ስለኾነ ሊቀጥልና ሊበረታታ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም እነዚህ መንፈሳዊ ጉባዔያት ሰውን ወይም ማኅበራትን ለማክበርና ስምን ለማስጠራት ታስበው የሚደረጉ ሳይኾኑ፥ እግዚአብሔር እንዲመሰገንና ህዝበ ክርስቲያኑ በአምልኮ ጸንቶ መንግስቱን እንዲወርስ የሚያስችሉ ስለኾኑ፥ አሁን ባሉበት ኹነት የእግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር አጉልተው በመግለጥ እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

 

ዐውደ ርዕይውን የተከታተሉት ብዙዎች ምዕመናን በበኩላቸው በዚህ መልኩ የተዘጋጁ መንፈሳዊ ዐውደ ርዕይዎችን ዐይተው እንደማያውቁና በዝግጅቱም ደስተኞች እንደኾኑ ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን ዋጅታ፥ ትውልዱን ለመጠበቅ እየተጋች መኾኑን የሚያሳይ መልካም ጅምር ነው፥ በማለትም ስለ ዐውደ ርዕይው የነበራቸውን ስሜት አካፍለዋል። ወደፊትም እንዲህ በተደራጀ መልኩ ዝግጅቶች በተደጋጋሚ ቢደረጉ መልካም ነው፥ በማለት አዘጋጁን የጀርመንን ንዑስ ማእከልን አሳስበዋል።

ዐውደ ርዕዩ በኹለት ቀን ዝግጅት በዘጠኝ ዙር ተጎብኝትዋል። ከከተማው ውጭ ያሉ ማኅበራትም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው በመምጣት ተሳታፊዎች ሆነዋል። ዐውደ ርዕዩ በሌሎች አካባቢ እንዲቀርብ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ባጭር ጊዜና በተቀናጀ መልኩ በሌሎች የበቫርያ ግዛት በሚገኙ ከተሞች ለማሳየት እቅድ ላይ እንዳለም በንዑስ ማእከሉ ተጠቁማል።

በቦታው ከተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ በተጨማሪ በእለተ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ከ350 በላይ ለሚኾኑ የደብሩ ምዕመናን ማኅበረ ቅዱሳን በ2011 ዓ/ም ሊሠራቸው ካቀዳቸው የፕሮጀክት እቅዶች አምስት ያክሉን በመምረጥ ከአጭር ዘጋቢ ፊልም ጋር ገለጻ ተደረጓል። የፕሮጀክት ገለጻው ዓላማ የማኅበሩን እቅንቅስቃሴ በሐሳብ፥ በጉልበትና በገንዘብ ለመደገፍ ፈቃደኛ የኾኑ አቅም ያላቸው አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማሳወቅ ታስቦ የቀረበ ሲኾን፥ ብዙዎችም በደስታ ተከታትለው፥ ቀና ምላሻቸውንም አሳይተውበታል። በመጨረሻም ዐውደ ርዕዩ እሑድ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ተጠናቋል።

 

የጣልያን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምሥረታ ጉባኤውን አካሄደ

ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም

 

“ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ እና አንድነት ሁላችሁም ትናገራላችሁ፤ እኔም ብመኘውም ብቻዬን ግን አላመጣውም፣ እናንተም እርዱኝ” ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ።

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

በአውሮፓ አኅጉር በአዲስ መልክ ከተዋቀሩት አራት ሀገረ ስብከቶች አንዱ የሆነው የጣልያን እና አካባቢው (ጣልያን፣ ቤልጅዬም፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ እና ቱርክ) ሀገረ ስብከት የመመሥረቻ ጉባኤውን በጣልያን ዋና ከተማ ሮም አካሄደ። ጉባኤው ጥር 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሰብሳቢነት ተካሂዷል። በጉባዔው ላይ በሀገረ ስብከቱ ስር ከሚገኙ አሥራ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት ከጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅየም፣ ግሪክ እና ከቱርክ የተሰባሰቡ አስተዳዳሪዎች እና የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ተወካዮች ታድመዋል።

ተሳታፊ ካህናት አባቶች እና ተወካዮች የእርስ በርእስ ትውውቅ እና የመጡበትን አጥቢያዎች አጭር የሥራ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሀገረ ስብከቱ በሚገኙት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ችግሮች እና አለመግባባቶችን ያስተናገዱ መሆናቸው ተጠቁሟል። ከእነኚህም በእግዚአብሔር እርዳታ መፍትሔ የተሰጣቸው አጥቢያዎች ሲኖሩ በአሁኑ ወቅት አለመግባባቱ የተባባሰባቸው እንዳሉ ከቀረቡት ሪፖርቶች ለመረዳት ተችሏል። እነኚህን ችግሮች ለመፍታት ሀገረ ስብከቱ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በየአጥቢያው ያሉትን ችግሮች እንዲሁም ሥርዓትን እና ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልጠበቀ አሠራር ከሀገረ ስብከታቸው እንዲጠፋ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። “ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ እና አንድነት ሁላችሁም ትናገራላችሁ፣ እኔም ብመኘውም ብቻዬን አላመጣውም፣ አናንተም እርዱኝ” በማለት ሰላምን ለማስፈን እንዲቻል የጉባኤተኛውን ቀና ትብብር የጠየቁት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ “ለዓለም ሰላምን የምትሰብክ ቤተክርስቲያ ውስጥ ሆነን፣ የእኛን ችግር ራሳችን መፍታት አቅቶን፣ ገመናችንን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት እና ዳኛ በመውሰድ ከፍተኛ የገንዘብ እና የጉልበት ኪሳራ ላይ ወድቀናል፣ ይህ ገንዘብ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ማበልጸጊያ ይውል ነበር።” ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ የተዋቀረው የሀገረ ስብከቱን የተለያዩ ክፍሎች የሚያስተባብሩ እና አገልግሎቱን የሚመሩ ሰባት አባላት ያሉት የአስተዳደር ጉባኤ የተዋቀረ ሲሆን ጉባኤው፣ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍስሐ ድንበሩን (ከፈረንሳይ) የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በማድረግ ሰይሟል። በሌላ በኩል በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በጳጳሱ አቅራቢነት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመድቡ መሆኑ ተገልጿል። ይህ አዲስ የአስተዳደር ጉባኤ በተወከለበት አካባቢ ያለውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ለማሳለጥ በተለይም ከዚህ በፊት ከነበሩት ሙከራዎች በተሻለ መልኩ ዘመኑን የዋጀ፣ ግልጽነት የሰፈነበት፣ እና በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲያመጣ ሓላፊነት ተጥሎበታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በጣልያን ዋና ከተማ በሮም እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን አገልግሎቱን በአስተማማኘነት ለማስቀጠል እንዲቻልም ሁሉም አጥቢያዎች እንደየደረጃቸው የገቢ ፈሰስ እንዲያደረጉ ውሳኔ ተላልፏል።

ሀገረ ስብከቱ በዚህ ጉባኤ በጸደቀለት መመሪያ መሠረት፣ ከጥገኝነት ነጻ የሆነ እና የትኛውም ሊቀ ጳጳስ በተዘዋወረ ጊዜ በሻንጣው ይዞት የሚዞር ዕቃ እንዳይሆን፣ ነገር ግን ራሱን የቻለ የገንዘብ እና የቁሳቁስ አቅም፣ የተጠናከረ ቢሮ እና አስተዳደር እንዲኖረው ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። ለዚህም እንዲረዳ ከአብያተ ክርስቲያናት ከሚሰበስበው ገቢ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ሀገረ ስብከቱን እንዲያጠናክር ለአስተዳደር ጉባኤው ምክር ተችሮታል። በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የካህናት እና አገልጋዮች ምደባ እንዲሁም አጠቃላይ አሠራር ወጥነት ባለው መልኩ እና ከጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመናበብ እንዲያከናውንም ጥሪ ቀርቧል።

ለሁለት ቀናት የተደረገው የምስረታ ጉባኤው በሀገረ ስብከቱ ሊሠሩ ይገባቸዋል ያላቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች በመጠቆም አዲስ ለተቋቋመው የአስተዳደር ጉባኤ የቤት ሥራ ሰጥቷል። ከነዚህም መካከል በሀገረ ስብከቱ ሰላምን እና አንድነትን ማጠናከር፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድነትን መፍጠር፣ በጥናት ላይ የተደገፈ አሠራር መዘርጋት፣ በአውሮፓ መልካም አጋጣሚዎችን ማጥናት፣ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ በጥገኝነት ጠያቂዎች ማቆያ ካምፕ አካባቢ ትምህርት መስጠት፣ የአገልጋዮች ስልጠና ማዕከል መከፈት፣ አጥቢያዎች የራሳቸው የሆነ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ማስገኘት፣ እና ሀገረ ስብከቱን ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል።

በጉባኤው መጨረሻ ላይ ታላቅ ሥራን እግዚአብሔር ሠርቷል። ይህም፣ በሮም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና በደብረ ከነዓን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች መካከል ተፈጥሮ ለዓመታት የቆየው አለመግባባት “ድንጋይ ባገኝ፣ ድንጋይ ተሸክሜ ይቅር ይባባሉ ዘንድ በለመንኳቸው” ሲሉ በተደመጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ሕርያቆስ ጸሎት እና በተሳታፊዎች አቀራራቢነት በሁለቱ አጥቢያዎች ካህናት እና ተወካዮቻቻው አማካኝነት እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ ሆኗል። ይህ እርቅ የምሥረታ ጉባኤው ታላቅ ስኬት ሲሆን በሁለቱ አጥቢያዎች የተጀመረው የእርቅ እና የሰላም ጉዞ በአጠቃላይ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት አገልግሎት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ተገልጿል። በሌሎች አጥቢያዎች የሚታዪ አለመግባባቶችም በዚህ መልኩ መፈታት እንደሚኖርባቸው መንፈሳዊ ጥሪ ተላልፏል።  

የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ታኅሣሥ 18 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ለዐራት ተከፍለው በአዲስ መልክ ከተዋቀሩት የአውሮፓ አህጉረ ስብከት አንዱ የሆነው እና በብፅዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የሚመራው የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምሥረታ ጠቅላላ ጉባኤውን በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አካሄደ። ይህ ጀርመንን፣ ስዊዘርላንድን፣ ኦስትሪያን እና ሆላንድን የሚያጠቃልለው ሀገረ ስብከት በቁጥር ከ 30 በላይ የሚሆኑ አጥቢያዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን ለዚህ ጉባኤ ከአብዛኛዎቹ አጥቢያዎች የመጡ የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሰበካ ጉባኤ፣ የካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች በአጠቃላይ ከ 90 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል። 

ጉባኤው በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የአስተናጋጁ የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ አጭር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ “መሰባሰባችንን አንተው“ (ዕብ 10÷ 24-25) በሚል ርእስ ተነስተው ስለሀገረ ስብከቱ አወቃቀር እና በመዋቅር ማገልገል ስላለው ጠቀሜታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “የቤተከርስቲያን አንድነት ከመጣ በኋላ የምናደርገው ጉባኤ በመሆኑ በታላቅ ደስታ እንደመጣችሁ አምናለሁ“ ያሉት ብፁዕነታቸው ይህንን አንድነት ለማጽናት በፍቅርና በአንድነት ልናገለግል እንዲሁም ሀገረ ስብከታችንንም ልናጠናክር ይገባል የሚል መልእክት በአጽንዖት አስተላልፈዋል።

በመቀጠል የነበረው መርሐ ግብር የተሰናባቹ የምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አጭር የሥራ ዘገባ ሲሆን ይህንንም ዘገባ ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ  ናቸው። አስተዳደር ጉባኤው ከተመረጠበት ከነሐሴ 2005 ዓ.ም. ወዲህ ተሰርተው በም/ሥራ አስኪያጁ ከተዘረዘሩት በርካታ ዐበይት ተግባራት መካከል የቅዱስ ሲኖዶስን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነትን መመሪያዎች መፈጸም እና ማስፈጸም፤ የስምንት አዳዲስ አጥቢያዎች መመሥረት፤ የስዊዘርላንድ አጥቢያዎችን ወደ ሀገረ ስብከቱ ማምጣት፤ ኤፍራታ በተባለች ዓመታዊ መጽሔቱ እና በፌስቡክ ገጹ ስብከተ ወንጌለን ማስፋፋት፤ በአድባራት መካካል እና በአድባራት ውስጥ የተከሰቱ አላመግባባቶችን መፍታት፤ ሁለት ዙር የረዳት ሰባክያን ሥልጠና መስጠት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በተከሠተ ጊዜ ከ 20 ሺህ ዩሮ በላይ አሰባስቦ መላክ እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዓመታዊ ፈሰስ ማድረግ የሚሉት ተጠቃሽ ክንውኖች ናቸው። በሌላ በኩል ከሀገር ውጭ በነበረው ሲኖዶስ ሥር የነበረው የመላው አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ ሀገረ ስብከቱ ሲሰራቸው የነበሩትን ዋና ዋና ተግባራት ጠቅለል አድርገው ያቀረቡ ሲሆን ከተለመዱት አድባራትን የመትከል እና ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋ ሥራዎች በተጨማሪ በተለይም ከ 5 በላይ አጥቢያዎች የራሳቸው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለቤቶች ሆነዋል ብለው ያቀረቡት ክንውን የጉባኤውን  ትኩረት የሳበ ስኬት ነበር።

በሦስተኛነት የተያዘው አጀንዳ ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን ማስመረጥ ሲሆን ለዚህም በመጀመሪያ የምርጫው ሂደት ምን መሆን እንዳለበት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በተለይም የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ከዐራቱም ሀገራት የተወጣጡ እንዲሆኑ፤ ቀድሞ የሀገር ውስጥ እና የሀገር ውጭ ሲኖዶስ ይባሉ በነበሩት አህጉረ ስብከት ሥር የነበሩትን እንዲሁም ገለልተኛ ይባሉ የነበሩትን አጥቢያዎች ውክልና የሚሰጥ እንዲሆን፤ እንዲሁም ከካህናት በተጨማሪ የምእመናን ተዋጾኦ እንዲኖርበት የሚሉት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ የምሳ እረፍት ተደርጓል። ከምሳ እረፍት  በኋላ አስመራጭ ኮሚቴው 18 እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን ጉባኤው 9 የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን በድምጽ ብልጫ መርጧል። ከእነዚህ ውስጥም የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ስብሐት ለአብ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በመሆን ተመርጠዋል።

         

የሀገረ ስብከቱ እና የወረዳ ቤተ ክህነቶች ግንኙነት ምን ይምሰል? የሚለው አጀንዳ ሌላው ጉባኤውን ብዙ ያወያየ አጀንዳ ሲሆን ከአጥቢያዎቹ ቁጥር ማነስ እና የሀገራቱን መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወረዳ ቤተ ክህነት ማቋቋም ሀብትን እና  የሰው ሃይልን ከማባከን እና የአሰራር ሰንሰለቱን ከማርዘም የዘለለ ብዙ ጥቅም የለውም ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ወረዳ ቤተ ክህነት ማቋቋም ሳያስፈልግ አጥቢያዎች በቀጥታ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ይገናኙ በማለት ወስኗል።

በመጨረሻም ለተሰናባች የሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አባላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ እና ቃለ ጉባኤው ተነቦ ከጸደቀ በኋላ ብፅዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጉባኤውን ተሳታፊዎች እንዲሁም የአስተናጋጁ የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አስተዳዳሪ እና ምእመናንን አመስግነው ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል።

በሀገረ ጀርመን የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 24 እና 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ ቡራኬ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ። ይህ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምዕመናን ብርቱ ጥረት የተገዛ መሆኑ ታውቋል። በበዓሉም ላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል። Read more

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዐውደ ርእይ ተካሄደ

“ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!” በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል የጀርመን ን/ማዕከል የተዘጋጀ ዐውደ ርእይ ከነሐሴ ፬ እስከ ፮  ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. በጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ ተካሄደ።

ዐውደ ርእዩን በጸሎት የከፈቱት ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የአውሮፓ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ሲሆኑ  በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ እና በአካባቢ የሚገኙ የአብያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ተጋባዥ መምህራን እና እንግዶች ተገኝተዋል። ብፁዕነታቸው ዐውደ ርእዩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልእክት  ስለቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ አስተምህሮ እና ወቅታዊ ችግሮች የሚያስገነዝቡ እንደዚህ ዓይነት መርሐግብራት ሊበረታቱ የሚገባቸው መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም በቅርቡ የተፈጸመውን የቤተክርስቲያን  አስተዳደራዊ አንድነት ለማጽናት ካህናት እና ምእመናን በርትተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው እና ይህንንም በፍቅር እና በመከባበር መንፈስ አብሮ በማገልገል መግለጽ ያስፈልጋል በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ “የቤተ ክርስትያን አስተምህሮ”፣  “የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት”፣ “የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ”፣ “ምን እናድርግ” እና “ማኅበረ ቅዱሳን ማነው” የሚሉ አምስት ዐበይት ከፍሎች የነበሩት ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ከፖስተር ገለጻ በተጨማሪ በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች እና ማብራሪያዎች ቀርበውበታል፡፡  

ከዐውደ ርዕይው በተጨማሪ ጎን ለጎን በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል ።  እንዲሁም በትዕይንቱ ላይ ወይም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ጥያቄ ላላቸውም ማብራርያ ሰጥቷል። ለህጻናት እና ለአዳጊዎችም የሚሆን የትምህርት መርሐ ግብርም ተዘጋጅቶ ነበር።  በሦስቱ ቀናት ውስጥ በአጠቃለይ በግምት ወደ 200 አከባቢ የሚሆኑ ምእመናን በአማርኛ የተዘጋጀውን ትዕይንት እንዲሁም 17 ሰዎች ደግሞ የጀርመንኛው ትዕይንት ተመልክተውታል።

በመጨረሻም ዐውደ ርዕዩን የተመለከቱ ጎብኚዎች በሰጡት አስጠያየት በዐውደ ርዕይው ሰፊ ትምህርት እንዳገኙ፤ በሌሎች ከተሞችን እንዲካሄድ ያላቸውን ጉጉት እና ለወደፊቱ እነዚህ መሰለል መርሐ ግብሮች ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል። ይህ ዐውደ ርእይ አውሮፓ ላይ ሲካሄድ የመጀመሪያው ሲሆን በቅርቡ በጀርመን ሀገር በርሊን እና ሙኒክ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእንግሊዝ የ2ኛው ዙር ሐዊረ ህይወት ተካሄደ

በዩኬ ንዑስ ማዕከል

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማዕከል የዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማዕከል ያዘጋጀው የ2ኛው ዙር ሐዊረ ሕይወት መርሐግብር ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በታላቋ ብሪታንያ በነቲንግሃም ከተማ በቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ተካሄደ።

በጉባዔው ላይ ከተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች የተሰባሰቡ 50 ያህል ህፃናት እና ከ230 በላይ የሚሆኑ ካህናትና ምዕመናን ተሳትፈዋል። መርሐ ግብሩም በካህናት አባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ የአዉሮፓ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ለሐዊረ ህይወቱ ተሳታፊዎች ሁሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ! መልዕክት አስተላልፈዋል። አያይዘውም ስለማኅበሩ አመሠራረት ፤ ስያሜ፤ እንዲሁም ማኅበሩ ስለሚያደርገው አስተዋፅዖ በአጭሩ አብራርተዋል።

በመቀጠል የዩኬ ን/ማዕከል አባላት መዝሙር ከቀረበ በኋላ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ የሄልሲንኪ ደ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በቤተክርስቲያን ሥርዓትና አገልግሎት ዙሪያ ጥልቅ ትምህርት ተሰጥቷል።  የትምህርት አቀራረብ መሠረታዊ የሆነና የምእመናንን ግንዛቤ ግምት ውስጥ ያስገባ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ትምህርት ነበር። በትምህርቱ ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ፤ የአገልግሎት ሥርዓት፤ የአገልጋይና የተገልጋይ ደንብና ጥንታዊ የሆነ አደረጃጀት እንዳላትና፤ በትውፊትዋ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳት መፃህፍት ያልተደገፈ ወይም ያልተመሳከረ ሥርዓትም ሆነ ልማዳዊ የሆነ አገልግሎት እንደሌላት ግልፅና ጥልቅ የሆነ ማስገንዘቢያ ተሰጥቷል።

ከዚህ በማስቀጠልም ይህንን ሐዊረ ሕይወት ልዩ ካደረጉት መርሐ ግብሮች መካከል በህፃናት ክፍል ተዘጋጅቶ ሕፃናቱ በጋራ መዝሙር ለጉባኤው ማቅረብና የሕጻናት የጥያቄና መልስ ዉድድር ነው። በዉድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ሶስት ኅፃናት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ተሳትፎ ላደረጉ ህፃናት በሙሉ በዩኬ ን/ማዕከል የተዘጋጀ የተሳትፎ ሰርተፍኬት በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው በኩል እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ይህ የህፃናት መርሐ ግብር ከወላጆች መርሐ ግብር በተጓዳኝ መካሄዱ ህፃናት ለቤተክርስቲያን አስተምህሮና አገልግሎት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።

ማኅበረ ቅዱሳን በአገር ቤት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ስለሠራቸው ሥራዎች በተለይም ስብከተወንጌል ባልተስፋፋባቸው የጠረፍ አህጉረ ስብከቶች አካባቢ ስለሚካሄደው የስብከተ ወንጌል ማስፋፍያ መርሐግብር እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት በመግለጽ በቀጣይም ያሉባቸዉን ችግሮች ቀርፈው ራሳቸዉን እንዲችሉ ለማድረግ የተሠሩትን እና እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በምስል በማስደገፍ በንዑስ ማዕከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል አቅርቧል። የዕለቱ ሁለተኛ ትምህርት የሆነዉን “ነገረ ድኅነት” በመጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ሚካኤል ተሰጥቷል። በትምህርቱም ለመዳን መደርግ የሚገባውን ተግባርና የአተገባበር ሥርዓት በጥልቀት ተዳሷል።

በማስከተልም የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ተወካይ ሊቀ ኅሩያን ፍሥሐ ተፈሪ በግል የተሰማቸውን ደስታና የሀገረ ስብከቱን መልዕክት አስተላልፈዋል። ተወካዩ ሀገረስብከቱ ከማህበሩ ጋር እስካሁን ያለውን ቀና ትብብር አስገንዝበው ወደፊትም በመተባበር ሊሠሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንዲሁም በማህበረ ቅዱሳን የታላቋ ብሪታንያ ንዑስ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ለጉባዔዉ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ጉባኤው ላይ ትምህርት ላስተላለፉት አባቶች እንዲሁም በለንደን እና ከለንደን ዉጭ ለሚገኙ በገንዘብ እና በተለያየ መልክ ለረዱ ድርጅቶችና፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ምስጋና አቅርበዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በተሰጡት ትምህርቶች ብዙ እውቀት እንዳገኙበት እና በአጠቃላይ መርሐ ግብሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።  በመጨረሻም  መርሐግብሩ በኣባቶች ጸሎትና ምስጋና ተፈጽሟል።

በፊንላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐዊረ ሕይወት ተካሄደ።

በማኅበረ ቅዱሳን አውሮጳ ማዕከል በፊንላንድ ግንኙነት ጣቢያ አስተባባሪነት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የባህል ማዕከል እሑድ ግንቦት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም  ተካሄደ።  በመርሐ ግብሩ ላይ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ካህናትን እና ተጋባዥ መምህራንን ጨምሮ  የደብሩ ሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከሄልሲንኪ እና ከሌሎችም ከተሞች የመጡ ምእመናን ተሳትፈዋል።

Read more

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብራት በአገረ ኖርዌይ እና በአገረ ጣልያን

በኖርዌይ እና በጣልያን ን/ማዕከላት

ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም.

፪ኛው ዙር የሐዊረ ሕይወት (የሕይወት ጉዞ) መርሐ ግብር በአገረ ኖርዌይ በክርስቲያንሳንድ ከተማ ከሚያዝያ ፲፫ – ፲፬  ፳፻፲ ዓ.ም. (April 21-22, 2018) ተካሄደ፡፡

በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እና በአውሮፓ ማዕከል የኖርዌይ ንዑስ ማዕከል በጋራ በተዘጋጀው በዚሁ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ በአገረ ኖርዌየ ከሚገኙ የቤተከርስቲያን ልጆችና መምህራን በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ተጋባዥ መምህራን ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የመጡ ምዕመናን ወምዕምናት ተሳትፈዋል፡፡

Read more

አምስተኛው ሐዊረ ሕይወት በአገረ ጀርመን ተካሄደ

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም.

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለ፭ተኛ ጊዜ በጀርመን አገር ፍራንክፈርት ከተማ አቅራቢያ በክሮፍልባህ የግብፅ ቅዱስ እንጦስ ገዳም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ፭÷፲፮) በሚል መሪ ቃል ተካሄደ። በዚህውም ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሚሻኤል የቅዱስ እንጦንስ ገዳም የበላይ ጠባቂ፣ በጀርመን የኢ/ኦ/ቤ/ክ አስተዳዳሪዎች እና የሀገረ ስብከቱ ካህናትና ዲያቆናት፣ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አውሮፓ ሀገራት ተጋባዥ መምህራን እንዲሁም ዘማሪያን ተገኝተዋል። በተጨማሪም 400 የሚሆኑ ምዕመናን በጉዞው ላይ ተሳትፈዋል። Read more