«ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።» ሉቃ 18:16

መስቀል (ለሕፃናት)

መስከረም 15 ፣ 2013

ብንያም ፍቅረ ማርያም

ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል።

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በአዲስ ደብተር፣ በአዲስ እስክርቢቶ፣ በአዲስ ልብስ … ስትማሩ ምን ተሰማችሁ? በጣም ያስደስታል አይደል? ይህ ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር አዲስ ዘመን አዲስ ዓመት ስለሰጠን ነው፡፡ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓልም የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፡፡

 የዘወትር ጸሎት በሚጸለይበት ጊዜ ስለመስቀል እንዲህ የሚል አልሰማችሁም “…መስቀል ኃይላችን ነው፤ ኃይላችን መስቀል ነው፤ የሚያጸናን መስቀል ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመንነው እኛ በመስቀሉ እንድናለን፡፡ ድነናልም፡፡ …” እያልን የምንጸልየው እኛ በጉልበታችን፣ በእውቀታችን ባለን ነገር ሁሉ እንዳንመካ፤ ነገር ግን በመስቀሉ እንድንመካ ነው፡፡

 በመስቀል እንመካለን ምክንያቱም መድኀኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ማለትም ከአባታችን አዳም ከእናታችን ሔዋን ጀምሮ እስከ አሁን ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስን እንደ ደካማ በመስቀል ተሰቅሎ /ተቸንክሮ/ ድል ስላደረገው፤ አዳምና ሔዋንን ከሲዖል እስራት ነፃ ስላደረጋቸው ነው፡፡ ለእኛም መስቀሉ መመኪያችን ሆኖ ዲያብሎስ መስቀሉን ሲያይ ይሸሸናልና ነው፡፡

 ልጆች መስከረም 17 የምናከብረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት አይሁድ መስቀሉ የታመሙትን እንደሚፈውስ፣ የሞቱትን እንደሚያስነሣ ባወቁ ጊዜ በክፉ ቅናት ተነሣሥተው በመስቀሉ ክብር እንዳይገኝ ቆፍረው ቀብረውት፣ ቆሻሻ መጣያም አድርገውት ስለነበር እግዚአብሔርም መስቀሉ ተቀብሮ እንዲቀር ስላልፈለገ ንግሥት እሌኒን አስነሥቶ አባ መቃርስ እና አባ ኪራኮስ በሚባሉ አባቶች መሪነት በቦታው በደረሱ ጊዜ ቦታው ከቆሻሻው ክምር የተነሣ ተራራ ሆኖ ስለነበር ትክክለኛው ቦታ የት እንደሆነ ማወቅ አልቻሉም፡፡

 ንግሥት እሌኒም ወደ እግዚአብሔር በመጸለይዋ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላት ደመራ እንድትደምር በዚያም ላይ እጣን እንድትጨምር ስለነገራት አገልጋዮቿን ወታደሮቿን ጠርታ በአካባቢው ደመራ እንዲተክሉ፣ እንዲያቀጣጥሉ፣ እጣንም እንዲጨምሩበት ነገረቻቸው፡፡ በተባሉትም መሠረት አድርገው ጢሱ  ወደሰማይ ከወጣ በኋላ በእግዚአብሔር ኃይል ተመልሶ መስቀሉ ወደ ተቀበረበት ተራራ አመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ንግሥት እሌኒ እና አገልጋዮቿ ደስ አላቸው፡፡

 ከስድስት ወራት ቁፋሮ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ የጌታችን የመድኃኔታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም የታመሙትን ሲፈውስ ሙት ሲያስነሣ በማየታቸው ከሁለቱ መስቀሎች ለመለየት ችለዋል፡፡ ዲያብሎስ በአይሁድ ላይ አድሮ መስቀሉን ቢደብቅም በእግዚአብሔር ኃይል ሊገኝ ችሏል፡፡ ልጆች መስቀላችሁን አትደብቁ እሺ!

ቸር ሰንብቱ፡፡

ጰራቅሊጦስ (ለሕፃናት)

ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. በድጋሚ የተለጠፋ በቤካ ፋንታ

  • እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት/ መዝ 118፥24/

ይህች ታላቅ ዕለት  ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት ሴቶች የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡    እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ  በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡

አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኀይልን ከላይ ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ ልጆችዬ መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡

ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም  ሁኔታ ተከትሎ  ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡

በዓለ ሃምሳ የሚባለውን የአይሁድን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሀገራት የመጡ በጊዜው  የነበሩ ቁጥራቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ  ሰዎች የሐዋርያቱን ታላቅ የዝማሬና የእልልታ ድምፅ ሰሙ፡፡ ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል አንዱ የሆነው  ቅዱስ ጴጥሮስ የተሰበሰቡት ሁሉም እንዲሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፡፡ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቶ ከክፉ ሥራ ተመለሱ፣ ኀጢአትን አታድርጉ፣ በቅድስና ኑሩ፣ ወደ እኔም ተመለሱ ቢላችሁ፤ እናንተ ግን ምንም በደል ሳይኖርበት ገረፋችሁት፣ አንገላታችሁት፣ በመስቀል ላይም ሰቀላችሁት፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሔር ነውና ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ እርሱ ግን አሁንም ይቅር ባይ ነውና ከኀጢአታችሁ ተመለሱ ንስሐም ግቡ ፡፡” በማለት አስተማራቸው፡፡

የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያት በፊት የሚያውቁት አንድ ቋንቋ ብቻ ነበረ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ሰባ ሁለት ቋንቋን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ለሁሉም በየቋንቋቸው አስተማሯቸው፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር ከተመለከቱት ብዙዎች እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ወደ ሐዋርያትም ቀርበው “አባቶቻችን እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁና ምከሩን፡፡ እንደ እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆንና በቅድስና እንድንኖር ምን እናድርግ?”በማለት ጠየቁ፡ በዚያች ቀን ቁጥራቸው  ሦስት ሺ ያህል ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው  ክርስቲያን ለመሆን ቀረቡ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፡፡ “እነሆ ሁላችሁም ንስሐ ግቡ፡፡ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምናችሁ ተጠመቁ፡፡” አላቸው በዚያው ዕለትም ሦስት ሺ ሰዎች ወደ ሐዋርያት በመቅረብ ኀጢአታቸውን ተናገሩ፤ ሐዋርያትም እግዚአብሔር ይፍታችሁ እያሉ ልጅነትን የሚያሰጣቸውን ጥምቀት አጠመቁዋቸው፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮም በየዓመቱ ይህችን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የምትባለውን በዓለ ጰራቅሊጦስን ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና ምሥጋና እናከብራታለን፡፡ እናንተም ልጆችዬ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ መዝሙር በመዘመር እና በመጸለይ ይህችን ታላቅ በዓል ልታከብሯት ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን፡፡

ሆሣዕና (ለሕፃናት)

በቤካ ፋንታ

03.08.2012

በኢየሩሳሌም በምትገኝ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ከተወለድኩ አምስት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ በዕለተ ሰንበት በቤት ውስጥ እየተጫወትሁ፣ እናቴም በጓዳ ሥራ እየሠራች ሳለን በድንገት የብዙ ሰዎች የዕልልታ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ ሰማን፡፡ እናቴም በፍጥነት ከጓዳ ሮጣ ወጥታ ‹‹ልጄ! ልጄ! ነይ እንሒድ!›› ብላ አዝላኝ እየሮጠች ከቤት ወጣች፡፡ በኹኔታው ተገርሜአለሁ፡፡

በሰፈር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ዅሉ በእናቶቻቸው ጀርባና በአባቶቻቸው ትከሻ ላይ ኾነው ከወላጆቻቸው ጋር በደስታ ዕልል ይላሉ፡፡ የሕፃናቶቹን ብዛት ሳይ ይበልጥ ተደሰትሁ፡፡ የሚያለቅስ አንድም ልጅ የለም፡፡ ‹‹ዛሬ የሕፃናት የደስታ እና የዝማሬ ቀን ነው›› ብሎ ልቤ በደስታ ፈነደቀ፡፡ ወላጆቻችን ዅሉ የዘንባባ ዝንጣፊ እየቈረጡ ያዙ፤ ለእኛም ሰጡን፡፡ ከዚያ ዕልል እያልን በደስታ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጥን፡፡

በመንገድ ላይ በጣም ብዙ ሕዝብ አየሁ፤ እነርሱም ዘንባባ ይዘው ደስ ብሏቸው እንደኛ ወደ ቤተ መቅደስ ይሮጣሉ፡፡ በመካከላቸው አንድ ትልቅ አህያ አየሁኝ፣ ከአህያይቱም ጋር ውርንጫዋ (ልጇ) አለች፡፡ የሚያማምር ልብስ በአህያዎቹ ጀርባ ላይ ተነጥፏል፡፡ በውርንጫዋም ላይ የዅላችን ፈጣሪ፣ ንጉሣችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ስመለከት በደስታ ዘለልሁኝ፡፡

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኾን በጣም ያስደስታል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛ ሕፃናትን እቅፍ አድርጎ ስሞን በጉልበቱ ላይ ቁጭ አድርጎ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡ በዙሪያውም ላሉት ሰዎች ‹‹እንደነዚህ ሕፃናት ንጹሓን ኹኑ፤ ኃጢአት አትሥሩ፤›› እያለ ይመክራቸዋል፡፡

ከዚያ ዕልል እያለ የሚያመሰግነው ሕዝብ፣ እንደዚሁም በእናትና በአባቶቻችን እቅፍ ውስጥ ያለን ሕፃናት በአንድነት ኾነን ጮክ ብለን የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለብን መዝሙር መዘመር ጀመርን፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፡፡›› የመዝሙሩ ድምፅ በኢየሩሳሌም ከተማ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ደግሞ የእኛ የሕፃናቱ ድምፅ ከትልልቆቹ በልጦ መሰማቱ ነው፡፡

ጌታችንን በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ባየሁት ጊዜ ትዝ ያለኝን አባዬ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ያስተማረኝን ታሪክ ልንገራችሁ፤ ታሪኩም፡- ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ ዕልል በዪ! እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾ በአህያ፣ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› የሚል ነው (ትንቢተ ዘካርያስ ፱፥፱)፡፡

የዝማሬውን ድምፅ ሲሰሙ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱት በከተማው ውስጥ ያሉ ጨካኝ ሰዎች ወደ እኛ መጡ፡፡ ሰዎቹም ሕዝቡ ዅሉ ደስ ብሏቸው እየዘመሩ፣ ዕልል እያሉ፣ የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለቡ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እያመሰገኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲሔዱ በተመለከቱ ጊዜ ተናደው ሕዝቡን ‹‹ዝም በሉ!›› ብለው ተቈጧቸው፡፡ ሕዝቡም ፈርትው ዝም አሉ፡፡

እኔና ጓደኞቼ ግን በእናታችን ጀርባ ላይ ካሉት ሕፃናት ጋር አብረን ኾነን ጮክ ብለን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚለውን መዝሙር ሳናቋርጥ እንዘምር ነበር፡፡ የገረመኝ ደግሞ ከእኔ የሚያንሱ ሕፃናትም መዝሙሩን ጮክ ብለው ሲዘምሩት መስማቴ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ መናገር የማንችለውን እኛን እንድንዘምርልህ ስለፈቀድህልን ተመስገን!›› ብዬ አምላኬን አመስግኜ መዝሙሩን መዘመር ቀጠልሁኝ፤ ‹‹ሆሣዕና፣ ሆሣዕና፣ ሆሣዕና በአርያም …፡፡››

በኋላ ግን እነዚያ ጨካኞቹ ሰዎች ስላስፈራሯቸው ወላጆቻችን ዝም አስባሉን፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋ ውርንጫ (በትንሿ አህያ) ላይ ቁጭ ብሎ ለጨካኞቹ ሰዎች ‹‹ከሕፃናት ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራሴ አዘጋጅቻለሁ፡፡ የእነርሱንም አፍ ይዛችሁ ዝም ብታስብሏቸው በዙሪያዬ ያሉት ድንጋዮች ያመሰግኑኛል፤›› አላቸው፡፡

ከዚያም ጌታችን፡- ‹‹የፈጠርኋችሁ ድንጋዮች ሆይ! ሕፃናት እንደ ዘመሩ እናንተም በመዝሙር አመስግኑኝ፤›› በማለት በታላቅ ድምፅ ሲናገር ግዙፍ ድንጋዮች ከመሬት ወደ ላይ እየተነሡ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን …›› እያሉ በሚያስደስት ድምፅ እየመዘመሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ጨካኞቹ ሰዎች አፍረውና ፈርትው ተመለሱ፡፡

እኛ ሕፃናት፣ ወላጆቻችንና በዙሪያችን የነበሩ ድንጋዮችም አምላካችንን ከበን በዕልልታ እየዘመርን፤ ለአህያዎቹ መርገጫ ልብሳችንንና የዘንባባውን ዝንጣፊ እያነጠፍን ወደ ቤተ መቅደስ ገባን፡፡ በዚያም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚል ትምህርት አስተማረን፡፡

በመጨረሻም ‹‹ሆሣዕና›› ብለን ምስጋና ላቀረብነውና በቤተ መቅደስ ተገኝተን ቃሉን ለምንሰማው ሕፃናት ጌታችን እንዲህ ብሎ መከረን፤ ‹‹ልጆቼ በመዝሙራችሁ ተደስቻለሁ፡፡ ዅል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣችሁ ዘምሩልኝ፡፡ በአንደበታችሁ በመዝሙር አግዚአብሔርን አመስግኑበት እንጂ ዘፈን እንዳትዘፍኑበት፡፡ ዘፈን ኃጢአት ነው፡፡››

ትምህርቱን ተከታትለን ከእናቴ ጋር ደስ እያለን ወደ ቤታችን ተመለስን፡፡ ታዲያ ዅል ጊዜ ይህችን የሆሣዕናን በዓል በውስጤ አስባታለሁ፤ መዝሙሩን መዘመር በጣም ያስደስተኛል፡፡ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የመከረኝንም ምክር ጠብቄ ዘፈን የሚባል በአፌ ሳልዘፍን በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ አደጌአለሁ፡፡

ልጆችዬ! ዛሬ የምታነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፮ እና የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፯ ያለው ትምህርት ነው፡፡

‹‹ሆሣዕና በአርያም›› ብለን እንድናመሰግነው የፈቀደልን፤ ኃይሉን ጥበቡን የሰጠን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የቤተልሔም እንስሳት

ታኅሣሥ 2003 , ስምዐ ጽድቅ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች

ልጆች ቤተልሔምን ታውቋታላችሁ?ቤተልሔም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ከተማ ናት። እና ልጆች የቤተልሔም እንስሳት ጌታችን መወለዱን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው “ምን ይዘን እንሂድ? ምንስ እናበርክት?”በማለት በሬዎች፥በጎች፥ጥጃዎች፥ህያዎችና ሌሎች እንስሳት ተሰብስበው መወያየት ጀመሩ።


ፀሐይ ልጆቿን ጨረቃንና ከዋክብትን ጠርታ “ልጆቼ ሆይ ዛሬ ታላቅ ደስታ በኢየሩሳሌም ሀገር በቤተልሔም ከተማ ተፈጽሟል።የዓለም ፈጣሪ ጌታችን ተወልዷልና ፍጥረታት ሁሉ በደስታ የምንዘምርበት ቀን ነው።እና ልጆቼ የጥበብ ሰዎች /ሰበዓ ሰገል / ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን ሰምተው ከሩቅ ሀገር ተነስተው መምጣት ፈልገዋልና ከእናንተ መኻከል ማነው ጎበዝ እነዚህን ክቡር እንግዶች ፈጥኖ ይዟቸው የሚመጣው?” ስትል ጠየቀቻቸው። ሁሉም ‘እኔ ልላክ እኔ ልላክ”እያሉ ሲያስቸግሯት እናታቸው ፀሐይ ዕጣ አውጥታ ለአንዷ ኮከብ ደረሳት። ዕጣ የወጣላት ኮከብ ከደስታዋ ብዛት በሰፊው ሰማይ ላይ ክብልል እያለች እየበረረች እንግዶቹ ዘንድ ደረሰች።እንግዶቹም ለታላቁ ጌታችን የምናበረክተው ስጦታ ብለው ዕጣን፥ ወርቅ፥ከርቤ ይዘውለት ሲመጡ አገኘቻቸው።ኮከቧ በጣም ደስ አላትና ቦግ ብላ በራች።ወደ ቤተልሔምም እየመራቻቸው ሔደች።


ጌታችን በተወለደባት ሌሊት በቤተ ልሔም ከተማ አካባቢ ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ።የጌታ መልአክ ወደእነርሱ ቀረበ። ወዲያውም ያሉበት ቦታ በብርሃን ተጥለቀለቀ። በዚህ ጨለማ የምን ብርሃን ነው የምናየው? ብለው ፈርተው ሊሸሹ ሲሉ የእግዚአብሔር መልአክ “አይዟችሁ ልጆች፥እነሆ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል።ህፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ ተኝቶ ታገኛላችሁ።” አላቸው። ብዙ የሰማይ ሰራዊትከመለኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፍቃድ።” አሉ። ልጆች ይገርማችኋል የዚያን እለት አበባዎች በደስታ አበቡ።እፅዋት ለመለሙ።ንቦችም ማራቸውን ሰጡ። የቤተልሕውም እንስሳት እኛስ ምን እንስጥ እያሉ ግራ ገባቸው። በመጨረሻ አህያ ከሁሉም የበለጠ አሳብ አመጣች። “ጌታችን የተወለደው በበረት ነው አይደል?” ስትል ጠየቀቻቸው። “አዎን” አሏት። “ታዲያ እኮ ልብስ የለውም።ደግሞም እንደምታዩት ጊዜው ብርድ የበዛበት ነው።” አለች። “እና አህያ ምናችን ልብስ ይሆነዋል ብለሽ አሰብሽ?” አሏት “ለምን ትንፋሻችንን አንሰጥም?”አለች። ሁሉም በጣም ደስ አላቸው።እንስሳቱ ትንፋሻቸውን ሊያበረክቱለት ጌታችን ወደተወለደበት በረት እየሮጡ ሄዱ። ልጆች እናንተም ደስ ካላቸው ጋር አብራችሁ ደስተኞች እንድትሆኑ ባላችሁ ነገር ሁሉ
ስስታም አትሁኑ። እሺ ልጆች።


++++++
ምንጭ፥ ጥበበኛው ሕፃን
የሸዋ ወርቅ ወልደ ገብርኤል

ሁለቱ እንስሶች

በአስናቀች ታመነ

ምንጭ: ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ 16 – 30/ 2011 ዓ.ም. ዕትም

ሰላም ልጆች እንደምን አላችሁ? ደኅና ናችሁ ለዚህ ቀን ያደረሰን እግዚአብሔር ይመስገን! አሜን! ልጆች ዛሬ ከሌላው ቀናት የተለየ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል። ጽሑፉን ከማንበባችሁ በፊት አስቀድማችሁ እስቲ ገምቱ ስለምን ይመስላችኋል፧ ስለቅዱሳን ሰዎች ካላችሁ እንደዛ አይደለም። ስለምን እንደሆነ ልንገራችሁ ስለ እንስሳት ነው። ስለየትኞቹ እንስሳት ካላችሁኝ ስለ አያ አንበሶ እና የሚጣፍጥ ማር ስለምትሰጠን ስለ ንብ ነው።

አያ አንበሶ

ከእለታት አንድ ቀን በቅድስት ማርያም ገዳም የንግሥ በዓል ይሆንና ብዙ ምእመናን በዓሉን ለማክበር ወደ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ይመጣሉ። በንግሥ በዓሉ ላይ የተገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ያለውን ሁሉ በደስታ ይሰጥ ጀመር። አንድአንዱ ገንዘቡን ፣ አንድአንዱ ደግሞ የአንገት ጌጡን ፣ ሌላው ደግሞ የእጅ ወርቁን ፣ ልብስ ፣ ጧፍ ፣ ሻማ ፣ ዕጣን ይሰጣል። ይህን የተመለከተ አንድ ሰው ፍቅረ ነዋይ ያድርበትና ይህን ብርና ወርቅ በኋላ ላይ መጥቼ እወስደዋለው አለ። የንግሥ በዓሉ በመዝሙርና በጸሎት ተጠናቀቀ።

እናም ይህ ክፋት ያደረበት ሰው ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ቤቱ ሔዶ ሲያልቅ ወደ ቤተክርስቲያኑ ለመሔድ በልቡ አሰበ። እርሱ ያሰበው ”ሰው ሳያየኝ ሔጄ ዘርፌ ሀብታም እሆናለው” ብሎ ነበር። ነገር ግን ከሰዓት ሰው ሁሉ ከሔደ በኋላ እየተጣደፈ ከኋላው ሰው አለ የለም እያለ መገስገስ ጀመረ። ከዚያም እንደምንም ብሎ ከገዳሙ ደረሰ። ከደረሰም በኋላ በጠዋት ከሕዝበ ክርስቲያኑ ሲሰበሰብ የዋለውን ስጦታ በድፍረት ሊሰርቅ ሲል ከየት መጣ ሳይባል አያ አንበሶ ከተፍ አለና ”ለእመቤታችን የተበረከትውን ስጦታ ልትወስድ መጣህን” ብሎ በሰው ቋንቋ ሲያናግረው ሰውየው በጣም ደነገጠ።

ድንጋጤው በሦስት ምክንያት ነበር። የመጀመሪያው አያ አንበሶን ማየቱ ፣ ሁለተኛው አያ አንበሶ በሰው ቋንቋ መናገሩና ሦስተኛው ደግሞ የእራሱ ሕሊና በፈጠረበት ጭንቀት ነበር። በጣም ከመደንገጡ የተነሣ መንቀጥቀጥ እና መንዘፍዘፍ ጀመረ። አያ አንበሶ ለሁለተኛ ጊዜ ”አንተ ሰው የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የተባለውን ቃል አስታውስ እንጂ” አለው።

ሰውየው ይበልጥ በመደንገጥ አምላኬ ይቅር በለኝ እያለ ከቅጥረ ቤተክርስቲያኑ ወጥቶ ፈረጠጠ። ልጆች እግዚአብሔር ቤቱን በእንስሳትም እንደሚጠብቅ ተመለከታችሁ። ልጆች እግዚአብሔርን እንጂ ሰውንም ሆነ ሌላውን ተደብቆ ክፋት ማድረግ ኃጥያት መሆኑን መረዳት አለባችሁ። እግዚአብሔርን ማሳዘን ጥሩ አይደለም ፣ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ሥራዎች በሙሉ መጥፎ መሆናቸውን መረዳት አለባችሁ።  

ንብ

ከእለታት አንድ ቀን የማያምኑ ሰዎች ቤተክርስቲያናችንን ለማጥፋት ያስቡና ለመስረቅ የሚመች ሰዓት እስከሚያገኙ ድረስ ይጠብቁ ነበር። ነገር ግን በቤተክርስቲያኑ አጸድ ውስጥ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ንቦች ይኖሩ ነበር። መጥፎ የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ከቤተክርስቲያን ያባርራሉ። ይህን ድርጊት ማንም አያውቅም ነበር። ከዚያም ከዕለታት አንድ ቀን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ተጠራርተው ቤተክርስቲያን ማፍረሻ አካፋ ፣ ዶማ እና ሌሎችም መሳሪያዎች ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን መሔድ ጀመሩ። ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲጠጉ ንቦቹ አንድ ጊዜ ወጥተው እየነደፉ አባረሯቸው። ንቦቹ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከአረማውያን ጠበቁ ማለት ነው። ልጆች ክፋትን የሚያስቡ ሰዎች በእግዚአብሔር የሚታዘዝ ቁጣ እንደሚደርስባቸው ተረዳችሁ? ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመጡ በቅን ልቦና በንጹሕ ሕሊና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ለመፈጸም መሔድ እንዳለባቸው መረዳት ይገባችኋል።


የቴክኖሎጂ ውጤቶች ና የሉላዊነት ጫና በልጆች አስተዳደግ

በላቸው ጨከነ ተስፋ (ዶ/ር)

መግቢያ

“ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። ” (መዝ፻፳፮፥፫)  ከእግዚአብሔር የተሰጡንን በረከት በሚገባው ተንከባክቦ፣ አስተምሮ  እና ጠብቆ ማሳደግ የወላጆች ትልቅ ሥራ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው። በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም አጫውቷቸው። እርሷንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳ 11፥18) እንዳለ ልጆችን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ማሳደግ የወላጆች ትልቁ ድርሻ ነው።

ዛሬ በተለይ  ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ መሆን፣ ከልጆች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር፣ ከቤተ ዘመድ መራቅ፣ የሥራ ጫና እና የጊዜ እጥረት፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጫና እና ዕለት ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማያገኙ  የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሃይማኖትና በግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል። በዚህ አጭር ጽሑፍ  የቴክኖሎጂ ውጤቶች በልጆች አስተዳደግ ላይ የፈጠሩትን  ችግሮች እና የመፍቴሔ ሐሳቦች ለውላጆች ግንዛቤ ከመፍጠረ አንጻር ቀረበዋል።

የዘመኑን የልጆች አስተዳደግ ውስብስብና አስቸጋሪ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት የሚተላለፉ መልክቶች ናቸው። ቴክኖሎጂ የራቀውን በማቅረብ የተወሳሰበውን በማቅለል ሕይወትን የተሻለች ማድረጉ አሌ የማይባል ቢሆንም የጎንዮሽ ውጤቱም ደግሞ በተለይ ለልጆች የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። በአግባቡ እስካልተጠቀምንበት ድረስ። ክፉና ደጉን በአግባቡ ባለየው በልጆች አዕምሮ ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ደግሞ የከፋ ነው። በአዳጊነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ነፍስ ካወቁ በኋላ ከትምህርታቸው የሚያዘናጋቸው፣ ከእንቅልፍ፣ ከማኅበራዊ መስተጋብር ያራራቀቸው፣ ቁምነገር እንዳይሠሩ የሚያዘናጋቸው አየሆነ ነው። የተክኖሎጂ ውጤቶች ብለን የምንመድባቸው የቪዲዮ ጌም መጫወት፣  ፊልሞች ማየት፣ የቴሌቪዥን መረሐ ግብሮች፣ ኢንተርኔት በተለይም የፌስ ቡክ ቻት፣ ዘፈን ማድመጥ፣ የተለያዩ ጨዋታዎች መመልከት የመሳሰሉት ናቸው።

የአንተርኔት እና የቴሌቪዥን ለልጆች ያለው ጉዳት  

ልጆች ከሕፃንነት ጀምሮ አስቸጋሪ ሱስ የሚሆንባቸው የቴሌቪዥን ሥርጭት በተለይም ፊልም መመልከት ነው። ዕድሜ ሳይለዩ የሚለቀቁ የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን ያለ ከልካይ የሚመለከቱ ሕፃናት ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጠርባቸዋል። የተፅዕኖው ውጤትም አፍራሽ ወይም ገንቢ ሊሆን ይችላል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ያለ ገደብ እንዲመለከቱ መፍቀድ ወይም ፍጹም ቴሌቪዥን እንዳይመለከቱ መከልከል ተገቢ አይደለም። ሁለቱም ጽንፎች የየራሳቸው የጎንዮሽ/ጎጂ/ ውጤት አላቸው።

ልጆች በኮምፒውተሮቻቸው እና በስልካቸው ለእነርሱ የማያስፈልጉ ነገሮች ይደርሳቸዋል ከማያውቁት ጓደኛ ወይም ከማያውቁት ሰው ሊደርሳቸው ይችላል። ሌላው የኢንተርኔት ችግር ልጆች በሳይበር አባላጊዎች (አማጋጮች) የተጋለጡ ይሆናሉ። ድምጻቸውን በመቅረጽ ለሌሎች አዳኞች ያስተላልፋሉ፤ ይሸጣሉ። ልጆችን የእነርሱ ባሪዎች በመሆን የተጠየቁትን በሙሉ እንዲፈጽሙ አለበለዘያ የያዙትን ምስል እና ድምፅ ለወላጅ፣ ለጓደኛ አና ለትምህርት ቤት አንደሚሰጡ በመግለጽ ያስፈራራሉ። ልጆችም በዚህ ምክንያት ራሳቸውን እስከ ማጥፋት፣ ለጭንቀት እና ለአደንዛዥ እፅች መጋለጥ ይደርሳሉ። ልጆች በሳይበር ዝሙት እስከ መፈጸም ይደርሳሉ። የተለያዩ ማስተዋቂያዎችን ያያሉ፤ ያለ አቅማቸው የተለያዩ ነገሮችን ይገዛሉ። አላስፈላጊ የሆኑ ፋይሎች፣ ቫይረሶች ወደ ኮምፒውተር ሊወርዱ ይችላሉ።

በዘረፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን አብዛኛ ጊዚያቸውን በእንተርኔት እና በቴሌቪዥን የሚያሳልፉ ልጆች የሚከተሉት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል ይሉናል፦

  • የጥናት ጊዜያቸውን በመሻማት ትምህርታቸው ላይ ጫና ይፈጥራል። ከአሰቡበት ሳይደረሱ ሊቀሩ ይችላሉ።
  • በሚዲያ የሚያዩትን እና በንግድ የሚተዋወቁ ነገሮችን በማየት አቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ ለማግኘት ይመኛሉ፤ በብልጭልጭ ነገር እንዲታለሉ ይሆናሉ።
  • በፊልም የሚያቸውን ወንጀሎች እየተለማመዱ ወደ ማከናውን ይመጣሉ (ለምሳሌ ስርቆት፣ ሃሺሽ መጠቀም፣ መደባደብ) በሚዲያ የሚተዋወቁ የመንገድ ላይ ምግቦች (fast foods) በማየት ለምግቦች ልዩ ፍቅር ይኖርቸዋል። ይህም ሰውነታቸው ከመጠን በላይ እንዲሆን ስለሚያደርግ የጤና መታወክ ያስከትልባቸዋል።
  • አብዛኛውን ጊዜያቸውን ብቻቸውን ከሚዲያ ጋር ስለሚያሳልፉ ከቤተሰብ እና ከማኅበርሰቡ ጋር እንዳይገናኙ በማድርግ ምናባዊ (virtual) ዓለምን እንዲኖሩ የብችኝነትን/ግለኝነት/ ሕይወት ያለማምዳል።
  • የንባብ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ይሆናል፤ ከንባብ ከሚገኘው በረከትም ተቋዳሽ አይሆኑም።
  • አካላዊ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ቁጭ ብለው ስለሚውሉ ጥንካሬ አይኖራቸውም።
  • የትኩረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል፣ ለፈጠራና ለምርምር ጊዜ አይኖራቸውም።
  • በዕድሜያቸው መጫወት ያለባቸውን ያህል አይጫወቱም። ከእህት እና ወንድማቸው ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጫወቱበት ጊዜ አያገኙም።
  • ሕይወትን በቴሌቪዥን መስኮት ሽው እልም ስትል እያዩ ቀላል አድርገው ያስቧትና ሲጋፈጧት ከባድ ትሆንባቸዋለች።
  • ልጆች ብዙ ክሂሎችን የሚያዳብሩት በማየት ሳይሆን በመሥራት ነውና የሥራ ጊዜያቸውን ይሻማሉ።
  • ከአካባቢያቸው ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር የተወሰነና ዝቅተኛ ይሆናል። አካባቢያቸውንም በደንብ እንዳያውቁት እንቅፋት ይሆንባቸዋል።
  • እየበሉ ሳይንቀሳቀሱ ስለሚቆዩ በዘመኑ አሳሳቢ ለሆነው ውፍረት (obesity) ይጋለጣሉ፤ በዚህ ሳቢያ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ።
  • ለወደፊት ለጾታ ግንኑኝነት ያለቸው አመለካከት የተዛባ ይሆናሉ፤ ተጨባጩን ዓለም ሳይሆን ሰው ሠራሹን ዓለም ናፋቂ ይሆናሉ፤ ሁል ጊዜ አዲስ ነገር ናፋቂዎች ይሆናሉ።
  • የሥነ ልቦና ጫና ያደርግባቸዋል፤ በትምህርት ቤት አና በቤተሰብ ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። ራሳቸውን እሰከ ማጥፋት ይደርሳሉ። ሱስ ስለሚሆንባቸው ሁልጊዜ ያያሉ። ሌሎችንም ወደ እዚህ ይመራሉ።
  • እራሳቸውን በደንብ ስለማይጠብቁ በመልካቸው፣ በአለባበሳቸው እና በቤተሰባቸው ማንጓጠጥ (bullying) ይደርስባቸዋል።

የመርጃ ቴክኖሎጂውን ለልጆቻን አንዴት አንጠቀም?

በአደጉ ሀገሮች ይህን ችግር ለመቆጣጠር በመንግሥት፣ የኢንተርኔት መስመር አከራዮች እና በትምህርት ቤት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ወላጆችም በቤት የወላጅ መቆጣጠሪያ (Parental control) ይጠቀማሉ። ለቤተሰቡ ሁሉ የየራሱ መግቢያ እና ማለፊያ ይኖረዋል፤ ወላጅ ብቻ የሚጠቀምባቸውን ፋይሎች እና ሌሎች መረጃዎችን ልጆች እንዳያይዋቸው ይረዳል። ወላጅ የሚፈልጉትን ድረ ገጾች ብቻ መምረጥ እና ሌሎችን በኮምፒውተሩ እንዳይከፍቱ ማድረግ ይችላል። ወይም ወላጅ መክፈት የሌለባቸውን ድረ ገጾች ወሳኝ ቃላቶችን በመጠቀም መከላከል ይቻላል። የተወሰኑት ሶፍቴዎሮች ልጆች የድምፅ እና የምስል መልእክት ኮምፒዊተሮችን ተጠቅመው እንዳያሰተላልፉ ይረዳል። የልጆችን አጠቃላይ በኢንተርኔት ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ሪፖርት ያደርጋል። ምን ድረ ገጽ እንደጎበኙ፣ ለምን ያህል ሰዓት፣ ከማን ጋር አንደተገናኙ ያሳያል። ወላጆች ለልጆቻቸው ለምን ያህል ጊዜ ኮምፒውተር ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው ገደብ ለማድረግ ይረዳል፤ ልጆች ከተፈቀደላቸው በላይ ሲጠቀሙ ለወላጆች መልእክት ይሰጣል። እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች ችግሩን ቢያቀሉትም ፈጽሞ እንዳይከሰት ማድረግ አልቻሉም።

ከእነዚህ መፍትሔዎች ጋር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ወላጆች ከልጆች ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ምንም ከወላጅ የተደበቀ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ልጆችን ከወላጅ በላይ ማንም ሊረዳቸው እና ሊግባባቸው አይችልም። የተከሰቱትን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት የተከሰተውን ነገር ልጆች በግልጽነት እንዲያወያዩን ማድረግ ከዚህ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔ ይሆናል። ልጆች ስለሚነግሩን ነገር ለመረዳት ስለ ኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ልጆች 13 (አሥራ ሦስት) ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሶሻል ሚድያ (ፌስ ቡክ፣ ትዊተር) መጠቀም እንደማይችሉ ማስረዳት። ልጆች ከእኛ በላይ እንዲሚያውቁ ሆነው ሊሰማቸው አይገባም። ወላጆች ልጆች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ላይ ሳይሆን ቴክኖሎጀውን በመሥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ልጆችን በተላያየ ቦታ የሚዘጋጁ ሳይንስ ነክ የሆኑ ዓውደ ርዕይዎችን እንዲዩ  ማደረግ ይገባል።

በአግባቡ እየመረጡ የልጆች ተሌቪዥን ሥርጭት እና የተመረጡ ፊልሞች እንዲመለከቱ ቢደረግ በርካታ ቁምነገሮች ሊቀስሙ፣ መልካም የሚባል ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እሴቶችን ሊያዳብሩ ይችላሉ። ውጤታማ የቴሌቪዥን አጠቃቀም የሚከተሉትን ተግባራት ይጠይቃል:-

  • ልጆች ምን ማየት እንዳለባቸው መለየት (አመፅ፣ ድብደባ፣ የአዋቂዎችን ጉዳይ እንዳይመለከቱ መጠንቀቅ)።
  • ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ እና በሕፃናት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እና የሚያተኩሩ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማበረታት።
  • ተፈጥሮን ማወቅ፣ ማድነቅ የሚችሉባቸውን፣ ተፈጥሮን የሚያስቃኙ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማገዝ።
  • በቀን ውስጥ ቴሌቪዥን የሚመለከቱበትን የሰዓት ገደብ መወሰን፣ ጥሩ ነገር ሲሠሩ እንደ ሽልማት እንዲሆናቸው ማድረግ።
  • አብሮ እየተመለከቱ ስለሚተላለፈው ነገር አንዳንድ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሚያዩትን ነገር መረዳታቸውን መገምገም።
  • በሚያዩት ነገር እና በእውኑ ዓለም መካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት።
  • ልጆች የግል መረጃዎችን (ኢሜይል፣ ስልክ፣ የቤት አዳራሻ) ለማያውቁት ሰው መቼም መስጠት የለባቸውም።
  • መቼም ልጆች የግል ማለፊያዎችን (Password) ለማንም መስጠት የለባቸውም። ማለፊያዎችን (Password) በየጊዜው መቀየር መቻል አለባቸው።
  • በሶሻል ሚድያ የሚለቋቸው ጽሑፎች፣ ፎቶግራፎች ሰውን የሚያናዳዱ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ፤ የሌሎችንም ፎቶግራፍ ባሌቤቱን ሳይስፈቅዱ አለማስቀመጥ።
  • ከማን እንደተላከ የማይታወቅ የኢሜይል መልእክት ልጆች መክፈት የለባቸውም።
  • የገንዘብ ነክ መረጃዎችን ልጆች ከወላጆች ጋር ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ለባንኮች ክፍያ ለመጠቀም ልጆች የማያውቁት ተጨማሪ ማለፊያ መጠቀም።
  • በኢንተርኔት ጓደኝነት የሚጠይቁ ሰዎችን የሚያውቋቸውን ብቻ ማድረግ።
  • ልጆች በኢንተርኔት ብቻ ጊዜያቸውን እንዳያጠፉ ሌሎች በኮምፒውተር የሚሠሩ ነግሮችን ማዘጋጀት።
  • ሰለ ቤተሰብእ የእረፍት ጉዞ፣ በቤት ስለሚዘጋጅ ዝግጅት፣ አብረው ሰለሚኖሩ ስዎች መረጃ በሶሻል ሚዲያ ማውጣት የለባቸውም።

ማጠቃለያ

ለልጆች የሰውነት ቅመምን፣ የሕይወትን ጣዕምና ትርጉምን እንዲሁም የስኬትን መንገድ የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጅ ድርሻ መሆኑን ወላጆችም፣ ልጆችም፣ ባለሙያችም የሚያሰምሩበት ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ ልጆች በተጠመዱባችው ሱሶች አማካይነት ጸያፍ ንግግሮችን፣ ደባል ሱሶችን፣ አመፅን፣ ልቅ ወሲባዊ  ድርጊቶችን፣ ኢ-ሥነ ምግባራዊ ተግባሮችን ይማራሉ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ልማዶች ወረዋቸው በዕድሜያቸው ሊሠሯቸው የሚገቧቸውን ሥራዎች እንዳይሠሩ ይከለክሏቸዋል። ከመደበኛው ትምህርታችው ያዘናጋቸዋል። እነዚህን የቴክኖሎጂ አፍራሽ ተፅዕኖዎች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከነዚህ ነገሮች ለመታደግ ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፤ በጊዜያቸው በሕይወታቸው በማንነታቸው እና በውጤታቸው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ውጤት ከግምት በማስገባት የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ ማበጀት፣ ልምድ ማካፈል፣ ዕድሜያቸውን ያላገናዘቡ መልእክቶችን እንዳይታደሙ መጠንቀቅ፣ ከሚመለከቷቸው ነገሮች ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ብቻ እየመረጡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤያቸውን ማዳበር፣ የራሳቸውን ማንነትና የማኅበረሰባቸውን ማኅበራዊ እሴቶች እንዲያውቁ ማድረግ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መከታተል፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተላቸውን መገምገም ወዘተ የወላጆች ሓላፊነት ሊሆን ይገባዋል።

* ፈሰሴ ገብረሐና ፣ በላቸው ጨከነ – የልጆች አስተዳደግ በዚህ ዘመን ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች። ሎንዶን ፳፻፮ ዓ.ም. ከታተመው መጽሐፍ ለዚህ መጽሔት የተዘጋጀ
** ይህ ጽሑፍ በኢ/ኦ/ተ/ቤት ክርስቲያን በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀገር ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደበረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በ፳፻፲ ዓ.ም. ባሳተመው መጽሔት ላይ የወጣ ነው።

የልጆች አስተዳደግ በውጭው ዓለም*

በላቸው ጨከነ (ዶ/ር)

የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

ልጆች ብዙ ተባዙ” ሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ከእግዚአብሔር የሚገኘ በረከቶች ናቸው ቅዱስ ዳዊት ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናችው(መዝ ፻፳፮) እንዳለ። ቅዱሳን ጻድቃን፣ ጳጳሳት ካህናት፣ ነገሥታት እና መሣፍንት የሚገኙት ከዚሁ አምላካዊ በረከት ነው። በአለንበት ዘመን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ፣ የኑሮ ጫና እና የዓለም መቀራረብ የልጆችን አስተዳደግ ለሁሉም ወላጆች እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ፈታኝ አድርገውታል። በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ ስለሚሆኑ ከቤተ ዘመድ ስለሚርቁ ፣ የስራ ጫና እና የጊዜ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው የዓለም ነጋዴዎች ልጆችን ከሃይማኖትና ከሥነ ምግባር የሚያስወጡ ተለዋዋጭ ሸቀጦችን ስለሚያጐርፉና እለት እለት ለመሳለም የሚሿት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማትገኝ የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሀይማኖትና ግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል።በዚህ ጽሑፍ የቀደሙ ወላጆችን የልጅ አስተዳደግ ከቅዱሳት መጻሕፍት ለአብነት አይተን በስደት ስንኖር ልጆቻንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን በሰፊው እንዳስሳለን።

Read more

አቤልና ቃየል (ለልጆች) (ዘፍ.4፣1-15)

 

በአውሮፓ ማዕከል ትም/ እና ሐዋሪያዊ አገልግሎት ክፍል

ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም. 

አዳም እና ሔዋን በመጀመሪያ ቃየልን እና አቤልን ወለዱ። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየል ምድርን የሚያርስ ነበረ። ሁለቱም ካላቸው ነገር ለእግዚአብሔር ስጦታ ወይም መሥዋዕት አቀረቡ። ቃየል ክፉ ልብ ነበረውና እግዚአብሔር አይበላው ብሎ ከአመረተው እህል ጥሩዉን ሳይሆን መጥፎዉ የማይረባውን መናኛውን እህል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። አቤል ልቡ ንፁህ ነበርና እግዚአብሔር ንጹሐ ባህርይ ማለት ነው ሲል ያላረጀውን በግ ፣ ጥርሱ ያልዘረዘረውን ንጹህ የአንድ አመት ጠቦት በግ ለእግዚአብሔር ንፁህ መሥዋዕት አቀረበ።

ልጆች እግዚአብሔር ጥሩ ሥራን ስለሚወድ ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ። ነገር ግን ቃየል ጥሩ ሥራ ስላልሰራ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ አልተመለከተም። በዚህም ምክንያት ቃየል እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። እግዚአብሔርም ቃየል አለው ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት ንብል፣ ቅጣትም ይጠብቅሃል

Read more

አዳም እና ሔዋን (ለልጆች) (ዘፍ 1፣2፣3)

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች?

በአለፈው በቀረበው ክፍለ ትምህርት እግዚአብሔር ለፈጠራቸው ፍጥረታት እንዳነበባችሁና እንደተረዳችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ እግዚአብሔር በስድስተኛው ቀን ለፈጠራቸው አዳም እና ሔዋን እንደሚከተለው ቀርቦላችኋል።

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከፈጠረለት በኋላ በስድስተኛው ቀን ዐርብ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ፈጠረ። እግዚአብሔር ሲፈጥረውም በእራሱ መልክ እና ምሳሌ ፈጠረው፤ በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ገዢ አደረገው። እግዚአብሔርምአዳም ብቻውን በመሆኑ ከጎኑ አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠራት። በተፈጠሩበት ምድር አዳም አርባ ቀን ፣ ሔዋን ደግሞ ሰማንያ ቀን ከቆዩ በኋላ ወደ ኤዶም ገነት አስገባቸው። ይህን መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወንዶች በተወለዱ በአርባ ቀናቸው ፣ ሴቶች በተወለዱ በሰማንያ ቀናቸው ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ታደርጋለች።

Read more

ሥነ-ፍጥረት/ለልጆች

ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. 

ልጆች እግዚአብሔር አምልካችን ሰማይ እና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው የሚኖሩትን ፍጥረታትን መቼ እንደፈጠራቸው ታውቃላችሁ? በዚህ ጽሁፍ ስለ ሥነ-ፍጥረት ትማራላችሁ።

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ካለመኖር ወደመኖር ያመጣ የሁሉ ፈጣሪ ነው። እግዚአብሔርም በሳምንት ውስጥ ካሉ ሰባት ቀናት (ዕለታት) በመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት የተለያዩ ፍጥረታትን ፈጠረ።

     kids1

Read more