በብዙኀን መገናኛ እና ቴክኖሎጅ አገልግሎት ክፍል
ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር «ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ» በሚል መሪ ቃል እያካሄደ ያለው ጉባኤ እንደቀጠለ ነው። ከማዕከሉ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በሰኔ ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በስዊዘርላድ ሀገር በርን ከተማ ከጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር፤ እንዲሁም ከሰኔ ፲፫ – ፲፬ ቀን ፪፲፻፯ ዓ.ም በግሪክ የአቴና ምክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ጉባኤያትን አካሂዷል።
በጉባኤያቱ ላይ «ፍኖተ ቤተክርስቲያን፣ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን» በሚሉ ሶስት ትእይንቶች የተከፋፈለ ዐውደ ርዕይ ተካሂዷል። እንዲሁም ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በመጡት ልዑካን ሰፊ የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍም የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በስዊዘርላንድ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከ፹ በላይ ምዕመናን እና ካህናት የተሳትፉበት ሲሆን በግሪክ ከ፫፻፶ በላይ ምዕመናን በጉባኤው እንደተሳተፉ ለመረዳት ችለናል።
በአቴና ከተማ የተካሄደውን ጉባኤ የኪዳን ጸሎት አድርሰው ባርከው የከፈቱት ቀሲስ ዶ/ር አየለ ወ/ጻድቅ፣ ቀሲስ ሰሎሞን ገ/መድህን እና መሪጌታ ዶ/ር መርዓዊ መለሰ ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው አገልግሎት እንዲተጉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
በስዊዘርላንድ የተካሄደውን ጉባኤ በጸሎት ባርከው የጀመሩት በስዊዘርላንድ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ይህ መርሐግብር አንዲሳካ ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነው ምዕመናንም ገዳማትን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው አንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ማእከሉ ሁሉም ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄዱ አስተዋጽኦ ላደረጉት በስዊዘርላንድ የጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እና በግሪክ የአቴና ምክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ሰባካ አስተዳደር ጉባኤዎች እንዲሁም በጉባኤው ላይ በመገኘት ድጋፋቸውን ላደረጉ ምዕመናን ሁሉ ምስናጋውን ያቀርባል።