ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ
ወላጆች ለወለድናቸው ልጆች ትልቅ አምላካዊ አደራ አለብን፡፡እግዚአብሔርም ልጅን ያህል ትልቅና የደስታ ምንጭ የሆነ ስጦታ ሲሰጠን ደግሞ ከትልቅ ኃላፊነት ጋር ነው፡፡ ከኃላፊነታችን ትልቁ ለልጅ፡- ሃይማኖትን፤ ምግባርና ትሩፋትን በማስተማር ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲበቃ አድርጎ በፈሪሀ እግዚአብሔር ማሳደግ ነው፡፡ «ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም» እንዲል ምሳ. ፳፪፥፮፡፡
በዘመናችን መንፈሳዊ እሴቶች ተሸርሽረው በአብዛኞቹ ወላጆች «ወልጄ አሳድጌ፤ ወግ ማዕረግ አሳይቼ» የሚሉት የሥጋዊውን ፍላጎት ብቻ በመያዝ ነው፡፡ ዋናው የልጆችም ጥቅም፤ የወላጆችም ኃላፊነት ልጆቻችንን ለክብረ መንግሥተ ሰማያት ማብቃት ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ወላጅ «ልጄን ለሲኦል ነው ለመንግሥተ ሰማያት ነው የማሳድገው?» ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡
ማንም ለልጁ ክፉን አይመኝምና ሁሉም ሰው እርሱም ልጆቹም ለክብረ መንግሥቱ እንዲበቁ ይሻል፤ ስለዚህ ልጆች ዛሬ በጥሩ መሠረት ላይ መታነጽ ይኖርባቸዋል፡፡ ልጆች በልጅነታቸው ያልተዘራባቸውን በሕይወታቸው አያፈሩም፡፡አንዳንድ ወላጆች ለዓለማዊ ትምህርት ብቻ ቅድሚያ በመስጠት፤ መንፈሳዊውን ወደ ጎን ይተዋሉ፡፡ መንፈሳዊው ሕይወት ካደጉ በኋላ የሚደርስ ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ወላጆች እኛ ራሳችን የመንፈሳዊ ሕይወት ግንዛቤ ስለሌለን አስፈላጊነቱም እምብዛም አይታየንም ወይንም በሰንበት ቀን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እንገድበዋለን፤ ሁሌ የሚኖሩት ሕይወት መሆኑን አናውቅም፡፡ ይህ ግን ለዚህ ዘመን የልጅ አስተዳደግ አስቸጋሪ ነው፡፡ይህ ዘመን ልጆቻችንን ወስዶ ብኩን የሚያድርጋቸው ብዙ የሕይወት ወጥመድ የሞላበት ነው፡፡ ካደጉ በኋላ በልጅነት የሌላቸውን ለማምጣት ይቸግራል፡፡ «ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፤ መሞቱንም አትሻ» ምሳ. ፲፱፥፲፰
ስለዚህ የልጆቻችን ዕድገት ሁለንተናዊ እንዲሆን ከዓለማዊ ትምህታቸው ባልተናነሰ ወይንም በበለጠ ለመንፈሳዊው ትምህርትና ሕይወታቸው ከፍተኛ ትኩረትና ጥረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?» ማር. ፰፥፴፮፤ ልጆቻችን በአስኳላ (በሳይንስ) ትምህርት ውስጥ ብቻ ቢያልፉ ምዕራባዊ ይሆናሉ፡፡
ምን ማለት ነው?
ዓለማችን በፈጣን ለውጦች ውስጥ እየተጓዘች ነው፡፡ብዙዎች የነሱ ሐሳብ፤እምነት፤ባህልና ሥርዓት በዓለም ላይ እንዲንሰራፋና የዓለም ሕዝብ የነሱ ተከታይ እንዲሆን እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የምዕራቡ ዓለም በዚህ ረገድ ፊታውራሪ ነው፡፡ሉላዊነት ወይንም ግሎባላይዜሽን በመባል የሚታወቀው የዘመናችን ገዢ ርእዮት ምዕራባዊ ባህልን፤የአኗኗር ዘይቤን በዓለም ላይ ለማሥረጽ የተቀረጸ ነው፡፡የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ከምዕራባውያን ሥልጣኔ የተቀዳ ነው፡፡
ለመሆኑ ምዕራባዊነት መገለጫውና ግቡ ምድነው?
ምዕራባዊነት በተለይ ልጆችና ታዳጊዎች በሰፊው ተደራሽ በሚሆኑባቸው ፊልም፤ዘፈን፤ የትምህርት ሥዓታችን ወዘተ. በሰፊው የሚሰብክ ሲሆን
፩. ከመንፈሳዊነት ይልቅ ቁሳዊነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ
፪. ቋሚ የሕይወት ዕሴት የሌለው እንደ ጊዜው የሚለዋወጥ ሰብእና፤ ዓለማዊነትን፤ ግብረ-ሰዶማዊነትን፤ ጾታ መቀየርን፤ የኮንትራት
(በውል በተገደበ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ) ትዳርን ወዘተ
፫. ሃይማኖት የለሽነትን ወይንም ፕሮቴስታንትነትን ግብ አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡
ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ይኸው ሕይወት ከፍ ያለና የሚያስቀና አስመስሎ በቁሳቁስ አጅቦ በማቅረብ የብዙ ወጣቶችን እና ታዳጊዎችን ቀልብ የሚማርክ ሆኗል፡፡ በዚህም አብዛኛው በተለይ የከተማው ወጣት ልቡ መማረኩ በአለባበሱ፤ በምኞቱና በአኗኗሩ ሁሉ የሚታይ ነው፡፡
ምዕራባውያኑ ይህን ዓይነቱን ሁኔታ ለመፍጠር የሚተጉት ለምንድነው? ልብ በሉ! አንድ ማኅበረሰብ የእኛን አኗኗር የሚከተል ከሆነ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ቢያንስ በዘላቂነት የእኛን ምርቶች ይጠቀማል፤ በየጊዜው የምናመጣውን አዳዲስ ነገር ይገዛል፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሆነ የገበያ ዕድል ባህላችንን በመሸጥ ብቻ እናገኛለን ማለት ነው፡፡ ይህ የምዕራባውያኑ አንዱ ግብ ሲሆን፤ በፖለቲካ፤ በሃይማኖትና በሌላም መስኮች የዓለም ቁንጮ ሆኖ የመምራትንና ለፈጠራዎቻቸው ሁሉ ተቀባይነትን ያስገኝላቸዋል ማለት ነው፡፡
ምን እናድርግ?
በመሠረቱ ልጆቻችን ላይ የተሠጠንን ኃላፊነት መወጣት የሚገባን ከምዕራባዊነት ልንታደጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ማንነታቸውን በትክክል አውቀው፤ በምድርም በሰማይም ተስፋ ያላቸው፤ ሥጋዊም መንፈሳዊም ዕድገትና ስኬት ያላቸው መሆን ይችሉ ዘንድ ነው፡ ፡
ክረምት
በተለይ ይህ ወቅት ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች ብሎም ወጣቶቻች ከመደበኛው ትምህርት በአንጻሩም ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በታች ይህን ጊዜያቸውን ሊያውሉበት ይገባል ብለን ያቀረብናቸው ምክረ-ሐሳቦችም በእርግጥ በክረምቱ ጊዜ የበለጠ ቢተገበሩም በበጋውም ቢሆን መዘንጋት የሌለባቸው ነገሮች ናቸው፡፡
ኦርቶዶክሳውያን ልጆች በዚህ ክረምት የበለጠ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጎልበት ላይ በማተኮር፤ እግረ መንገዱን ደግሞ ለዘላቂው የክርስትና ሕይወታቸው ስንቅ የሚሆኑ እውቀትና ክህሎቶችን የሚያስጨብጧቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ እንደ ምሳሌም
፩. የአብነት ትምህርቶችን ቢከታተሉ
በየደብሩ የአብነትን ትምህርት ከጠቃሚ የአባቶች የሕይወት ምክሮችና ግብረ-ገብ ጋር ጨምረው የሚያስተምሩ ካህናት አሉ፡፡ ልጆች እነዚህን መማራቸው ለጸሎትና አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከመጥቀሙም ባሻገር በነገዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአገልግሎት ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል፤ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን ለምትመኘው በሁለት በኩል የተሳለ አገልጋይ ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በአገልግሎት ውስጥ መኖር ደግሞ ለሌሎች ከመትረፍም ባሻገር ለራስ መጠበቅ የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡
፪. በሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብሮች ላይ ቢሳተፉ
እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ልጅ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ በጋውንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምትታደግበት አንዱ መዋቅር ነው፡፡ በክረምት ደግሞ በርካታ በአማራጭ የተዘጋጁ መርሐ-ግብሮች ስላሉ ሕፃናት ብዙ ያተርፉባቸዋል፡፡
፫. መንፈሳዊ የዜማ መሣርያዎችን ቢማሩ
በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ቤቶችና በአንዳንድ ሰንበት ትምህት ቤቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዜማ መሣርያዎች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም በገና፤ መሰንቆ፤ ከበሮና ዋሽንት ናቸው፡፡ ልጆች እነዚህን በዚህ ክረምት ቢማሩ እያደጉ በሄዱ ጊዜ ደግሞ የበለጠ ልምድ ስለሚሆናቸው ባለሙያ ይሆናሉ፡፡ይህም ለአገልግሎት ሕይወትም በር ይከፍትላቸዋል፡፡
፬. መንፈሳዊ ፊልሞችን፤መንፈሳዊ ታሪክና ትምህርት የያዙ የልጆች መጻሕፍትን፤ የሕፃናት መዝሙራትን ወዘተ. መመልከትና ማንበብ ቢችሉ የበለጠ ጠቃሚ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚያውም እነዚህን ነገሮች ልምድ እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ወላጆች ልጆቻቸው በእነዚህ መንገዶች ራሳቸውን በራሳቸው ስለሚያስተምሩ ብዙ ይረዳቸዋል፡፡
እነዚህን ቢያደርጉና በዘላቂነትም ገንዘብ ማድረግ ቢችሉ ለአጠቃላይ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ባሻገር ወላጆችም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን በጎ ሥራዎች በማድረጋቸው ዋጋ ያገኙበታል፡፡
በመጨረሻም መዘንጋት የሌለበት ልጆች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጥሩ ሲሆኑ፤ በአስኳላ ትምህርታቸውም የበለጠ ብርቱዎች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በታችኞቹ ደረጃዎች ሳይወሰን ዛሬ በየዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማቶቻቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሥጦታ የሚያበረክቱ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን መመልከት በቂ ማስረጃ ነው፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!