በዲን. ብርሃኑ ታደሰ
ግንቦት 1፣ 2004 ዓ.ም.
አባታችን አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ለሚያመልኩ ሁሉ ታላቅ የእምነት አባት ነው። በእርግጥም አምላኩን ፍጥረትን በመመርመር ማግኘቱ፣ አምላኩን ብሎ ቤተሰቡን ተለይቶ መውጣቱ፣ ልጁን ለመሰዋት ፍጹም ፈቃዱን ማሳየቱ ሁሉ ለእምነት አባትነቱ ማሳያዎች ናቸው። ከሁሉ የሚልቀው ከእርሱ አስቀድሞ ከሙታን መካከል የተነሱ ሳይኖሩ፣ ዘርህ በይስሐቅ ይጠራልሃል ከተባለ በኋላ ልጅህን ሰዋልኝ ሲባል፣ እነዚህን ሁለት የሚጣሉ የሚመስሉ ሐሳቦችን በእምነቱ አስታርቆ ማለት ቢሞት እንኳን ያስነሳዋል ብሎ አምኖ ልጁን ሊሰዋ ወደ ተራራ መውጣቱ ነው።(ዕብ11፥19) የሰው ሕሊና ጊዜ ሲያገኝ አንድን ነገር ደጋግሞ ማሰቡ አይቀርም፤ አብርሃም ግን የሦስት ቀን መንገድ ሲሄድ ይህ እምነቱ ንውጽውጽታ አልነበረውም – እፁብ ነው።
እኛ ክርስቲያኖች – የእግዚአብሔር ወልድን ሰው መሆን፣ ለኛ ብሎ መከራ መቀበል፣ በኋላም የቤዛነቱን ሥራ ሲፈጽም በአባቱ ክብር መቀመጡን ስለምናምንና ስለተጠመቅን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል። ይህ ልጅነት በፊት እንደነበረው ከሥጋ የመጣ አይደለም፤ መጽሐፍ – “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ግን መንፈስ ነው።” እንዲል፤ ልጅነታችን በጸጋ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ነው። (ዮሐ3) ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ይህንን ሲያጸናው የተወለድነው ከሚጠፋ ዘር አይደለም ይለናል። (1ጴጥ1፥22)
Read more